ኢራን በነዳጅ ማመላለሻ መርከብ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ስትል እስራኤል ከሰሰች

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ያይር ላፒድ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ያይር ላፒድ

እስራኤል በነዳጅ ማመላለሻ መርከብ ላይ ኢራን ጥቃት ሰንዝራለች ስትል ከሰሰች።

መርከቡ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ሁለት የእንግሊዝ እና አንድ የሮማንያ ዜጎች ተገድለዋል።

ለንደን በሚገኘው ዞዲያክ ማሪታይም በተባለው ድርጅት የሚመራው መርከብ በኦማን የባሕር ዳርቻ አካባቢ ሳለ ነበር ሐሙስ ጥቃቱ የደረሰበት።

የድርጅቱ ባለቤት የእስራኤሉ አይል ኦፈር የሚባል የመርከብ ተቋም ነው። ይህ የእስራኤል ድርጅት ባለፈው ሐሙስ የደረሰውን ጥቃት እየመረመረ እንደሆነ ቢናገርም፤ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ግን ጥቃቱን የሰነዘረችው ኢራን ናት ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ያይር ላፒድ ትላንት በሰጡት ማብራሪያ ጥቃቱ "የኢራን የሽብር ድርጊት ነው" ብለዋል።

አያይዘውም "ኢራን የእስራኤል ብቻ ችግር አይደለችም። ዓለም ዝም ሊል አይገባም" ሲሉ ተናግረዋል።

መርከቡ ላይ ስለደረሰው ጥቃት ገና ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም። ኢራንም ስለቀረበባት ክስ ምንም ምላሽ አልሰጠችም።

ይህ ጥቃት በቀጠናው ያለውን ውጥረት የሚያባብስ ነው። አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ለጥቃቱ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቅም ላይ ሳይውል አልቀረም።

የዩናይትድ ኪንግደም ቃል አቀባይ ባወጣው መግለጫ "እውነታው ላይ ለመድረስ አፋጣኝ ምርመራ እያደረግን ነው። በጥቃቱ የሚወዷቸውን ሰዎች ላጡ ሰዎች መጽናናቱን እንመኛለን" ተብሏል።

መርከቦች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው መከበር እንዳለበትም ተገልጿል።

የመርከቡ አስተዳዳሪ የሆነው ዞዲያክ ማሪታይም እንዳለው፤ ከተገደሉት ሰዎች ውጭ ሌላ ጉዳት የደረሰባቸው የሉም።

መርከቡ አሁን መደበኛ ጉዞውን እንደቀጠለና በተያዘለት እቅድ መሠረት አሜሪካ እንደሚያርፍ ድርጅቱ አስታውቋል።

በይፋ "ጦርነት" ያልተባለው የእስራኤል እና የኢራን እሰጣ ገባ እየተካረረ መጥቷል።

በኢራን እንዲሁም በእስራኤል መርከቦች ላይም ባለፉት ወራት ጥቃት ሲሰነዘር ነበር። ሁለቱም አገሮች ቢካሰሱም ማናቸውም ውንጀላውን አይቀበሉም።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ነገሩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት እንወስደዋለን ብለዋል።

ኢራን ውስጥ የሚተላለፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ ምንጭ ሳይጠቅስ እንደዘገበው፤ መርከቡ ላይ የደረሰው ጥቃት እስራኤል በሶርያ አውሮፕላን ማረፊያ ለሰነዘረችው ጥቃት በቀል ነው።

ስማቸው ያልተጠቀሰ የእስራኤል ባለሥልጣን እስራኤል ይህንን ጥቃት በቀላሉ እንደማታልፈው መናገራቸውም ተዘግቧል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር "የደረሰው ጥቃት አሳስቦናል። በቅርበት እየተከታተልነው ነው" ብለዋል።

ነዳጅ የጫነው መርከብ በሕንድ ውቅያኖስ ሰሜናዊ ክፍል በኩል ከታንዛኒያ፣ ዳሬ ሰላም ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሲጓዝ ነበር።