ከውድድር የታገዱ ናይጄርያዊያን አትሌቶች በቶኪዮ ሰልፍ አደረጉ

ስፕሪንተር ብለሲንግ ኦካግባሬ
የምስሉ መግለጫ,

ስፕሪንተር ብለሲንግ ኦካግባሬ

በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለመወዳደር ብቁ አይደላችሁም የተባሉ ናይጄርያዊያን ስፖርተኞች በጃፓን፣ ቶኪዮ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

የኦሎምፒክ የአትሌቲክስ የሥነ ምግባር መከታተያ ቡድን 10 ናይጄርያዊያን ስፖርተኞችን ጨምሮ 20 ተወዳዳሪዎች ከውድድር በፊት የአበረታች መድኃኒት መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው ከውድድር አግዷቸዋል።

አትሌቶቹ "በሌላ ሰው ቸልተኝነት እኛ ለምን እንሰቃያለን'' የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ባለሥልጣናቱን እና ውሳኔያቸውን ነቅፈዋል።

ሰልፍ ካካሄዱት ናይጄርያዊያን ስፖርተኞች በተጨማሪም አርብ እለት በተደረገው 100 ሜትር ማጣሪያ ውድድር ላይ በአንደኝነት ያጠናቀቀችው ስፕሪንተር ብለሲንግ ኦካግባሬ በተመሳሳይ መታገዷ ታውቋል።

የ32 ዓመቷ አትሌት ከውድድር በኋላ በተደረገላት ምርመራ ሰው ሠራሽ ሆርሞን እንደተገኘባት ተገልጿል። በቤጂንግ ኦሎምፒክ በረዥም ዝላይ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረችው አትሌቷ ከውድድሩ በግዜያዊነት መታገዷ ዛሬ ቅዳሜ ተገልጾላታል።

ትላንት በተደረገው ማጣሪያ ውድድር 11.5 ሰከንዶች ያስመዘገበች ሲሆን በግማሽ ፍጻሜው ከእንግሊዛዊቷ አሸር-ስሚዝ እና ከጃማይካዊቷ ኢሌን ቶምፕሰን-ሄራት ጋር ትወዳደር ነበር።

አትሌቷ ሌሎች 10 ናይጄርያዊያን አትሌቶች በአበረታች መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ውጪ ከሆኑ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው መታገዷ የተሰማው።