የኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት በቻይና ግዛቶች እየተስፋፋ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቻይናዋ ዉሃን ከተሰራጨ ወዲህ ባልታየ ፍጥነት ቫይረሱ በቅርቡ በአምስት የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ መስፋፋቱ ተነገረ።
ከቻይናው ናንዢንግ ከተማ አንስቶ መዲናዋ ቤይጂንግን ጨምሮ በአምስት ግዛቶች ቫይረሱ የተስፋፋበት ፍጥነት ከዉሃን ወዲህ ከፍተኛው የስርጭት መጠን ነው ተብሏል።
የቻይና መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት፤ ቫይረሱ በናንዢንግ አውሮፕላን ማረፊያ ሐምሌ 20 ከተገኘ ወዲህ ወደ 200 ሰዎች ተይዘዋል።
ከናንዢንግ የሚነሱ በረራዎች በአጠቃላይ እስከ ነሐሴ 11 ታግደዋል። የከተማ አስተዳድር ትችት ከተሰነዘረበት በኋላ በጅምላ ምርመራ ለማድረግ ውሳኔ አሳልፏል።
ስለዚህም 9.3 ሚሊዮን የከተማው ነዋሪዎች ይመረመራሉ ሲል ዢንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ምስሎች ነዋሪዎች ረዥም ሰልፍ ይዘው ለመመርመር ሲጠብቁ ያሳያሉ። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርጉ፣ አካላዊ ርቀት እንዲጠብቁም ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።
በከፍተኛ ፍጥነት የሚሰራጨው ዴልታ የተባለው የቫይረሱ ዝርያ ለወረርሽኙ ስርጭት ምክንያት እንደሆነ ባለሥልጣኖች ጠቁመዋል።
ቫይረሱ የተገኘበት አውሮፕላን ማረፊያ ብዙ ሰዎችን የሚያስተናግድ በመሆኑ ቫይረሱ በአምስት ግዛቶች እንደተሰራጨም ይታመናል።
የናንዢንግ ከተማ የጤና ኃላፊ ዲንግ ጄይ እንዳሉት፤ ቫይረሱ በብዛት የተገኘባቸው ሰዎች ከሩሲያ ተነስቶ ሐምሌ 10 ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የደረሰን አውሮፕላን ያጸዱ ሠራተኞች ናቸው።
ዢንዋ እንደዘገበው ከሆነ እነዚህ የጽዳት ሠራተኞች ተገቢውን የቫይረሱን መከላከያ መንገድ አልተከተሉም።
የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ የአውሮፕላን ማረፊያው ኃላፊ አስፈላጊውን የጥንቃቄ መመሪያን ባለመከተላቸው እንዲቀጡ ማድረጉም ተዘግቧል።
ቫይረሱ ዋና ከተማን ቤይጂንግን ጨምሮ ቢያንስ በ13 ከተሞች ታይቷል ተብሏል።
ግሎባል ታይምስ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመቆጣጠር አልረፈደም ብለዋል።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል ሰባቱ በጽኑ መታመማቸው የተነገረ ሲሆን፤ የቻይና ክትባት አዲሱን የዴልታ ዝርያ መከላከል ይችላል የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ሆኗል።
በእርግጥ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ክትባቱን ይውሰዱ አይውሰዱ አልታወቀም።