በዩኬ ወጣቶች እንዲከተቡ ለማበረታታት የታክሲ እና የምግብ ቅናሽ እየቀረበላቸው ነው

በእንግሊዝ እየተከተበች ያለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወጣቶች የኮቪድ ክትባት እንዲከተቡ ለማበረታታት እና የክትባት መርኃ ግብሩን ለማስፋፋት በማሰብ የታክሲ እና የምግብ ቅናሽ እንደሚቀርቡላቸው የእንግሊዝ መንግሥት ገልጿል።

ኡበር፣ ቦልት፣ ዴሊቬሮ እና ፒዛ ፒልግሪሞች ጨምሮ የምግብ አቅራቢዎች እና የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ዜጎቻቸው ክትባት እንዲከተቡ ማበረታቻዎችን ይሰጣሉ።

የጤና እና የማሕበራዊ እንክብካቤ መምሪያ ተጨማሪ የማበረታቻ ዝርዝር "በቅርቡ" እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

በእንግሊዝ ከ 18 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት የመጀመሪያውን የክትባት ወስደዋል።

ከ 72 በመቶ በላይ የእንግሊዝ አዋቂዎች እስካሁን ሁለቱን ክትባት የወሰዱ ሲሆን 88.5 በመቶዎቹ ደግሞ አንድ ጊዜ ተከትበዋል።

የታክሲ አገልግሎት የሚሰጠው ኡበር ኩባንያ ለሁሉም ደንበኞቹ ክትባቱን እንዲከተቡ በነሐሴ ወር ማስታወሻዎችን ይልካል።

ክትባቱን ለወሰዱ ወጣቶች ጉዞዎች እና በምግብ ማቅረቢያው ኡበር ኢትስ ላይ ቅናሽ ያደርጋል።

ቦልት የተባለው ሌላ የታክሲ ኩባንያ ወደ ክትባት ማዕከላት "ነጻ ጉዞ" ይሰጣል። የምግብ አቅርቦት ድርጅቱ ዴሊቬሮ ደግሞ ለተከተቡ ወጣቶች የመመገቢያ ቲኬት ይሰጣል።

የጤና እና ማህበራዊ እንክብካቤ መምሪያ (ዲኤችኤስሲ) "በክትባት ጣቢያዎች ለሚገኙ እና በኤንችኤስ ለሚመዘገቡ የቅናሽ ኮድ ይሰጣል። የማህበራዊ ሚዲያ ውድድሮች እና የምግብ ቤቶች የማስተዋወቂያ ቅናሾች ይካተታሉ።"

አክለውም ኩባንያዎች ለማበረታቻ መርሃግብሩ ማንኛውንም የጤና መረጃ አይጠይቁም ወይም አይሰበስቡም ተብሏል።

የጤና ሚኒስትሩ ሳጂድ ጃቪድ የክትባቱን መስፋፋት ለማገዝ ኩባንያዎች "ስላደረጉት ድጋፍ" አመስግነው ማህበረሰቡ "ቅናሾቹን እንዲጠቀሙ" አሳስበዋል።

ማበረታቻው የመጣው መንግሥት የክትባት እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት በመላው የእንግሊዝ የክትባት ጣቢያዎችን በሳምንቱ መጨረሻ መከፈታቸውን ተከትሎ ነው።

እስከ ሰኞ የሚዘልቅ የቀጥታ ሙዚቃ እና ነጻ ምግብ በክትባት ክሊኒኮች ውስጥ ለአራት ቀናት በሚቆይ ፌስቲቫል በምሥራቅ ለንደን እየተካሄደ ነው።