የአሜሪካ አቃብያነ ህግ በሩሲያ እንደተፈፀመ በሚጠረጠር የመረጃ ጠለፋ ኢላማ ሆኑ

በኒውዮርክ የሚገኘው አቃቤ ህግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

30 የሚጠጉ ከፍተኛ የአሜሪካ ዓቃብያነ ህግ የመረጃ መንታፊዎች ኢላማ እንደሆኑ የፍትህ መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። የአቃብያነ ህጉ ኢ-ሜይል እንደተመዘበረ የገለፀው መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ጥሰትም ነው ብሎታል።

በሶላርዊንድስ ሶፍትዌር ተጠቃሚዎች ላይ የደረሰው የሳይበር ጥቃት ሩሲያን ጥፋተኛ ያደረገችው አሜሪካ በመንግሥቷም ላይ የከፋ የሳይበር ስለላ ጥቃትም ነው ስትል ፈርጃዋለች።

መስሪያ ቤቱ እንደሚለው ቢያንስ የ27 ጠበቆች አንደኛው ኮምፒውተራቸው ተጠልፏል።

ይህም ሁኔታ ለአሜሪካ መንግሥት መረጃን በመስጠት የሚሰሩ ሰዎችን ጨምሮ ያልተገቡ መረጃዎችን አግኝተዋል የሚልም ፍራቻ ነግሷል።

የቀድሞው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጊል ሶፈር ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል።

የዐቃብያነ -ሕግ ኢሜይሎች "ለሌሎች መተላለፍ የሌለባቸውና ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ የሆኑ ሚስጥራዊ መረጃ" ይይዛሉ ብለዋል።

ጠላፊዎቹ ምስጢራዊ መረጃ ሰጭዎችን ማንነት ካወቁ መረጃውን ተጠቅመው "ሽፋናቸውን ሊያጋልጡ" ይችላሉ ብለዋል።

18 ሺህ ያህል የመንግሥትና የግል የኮምፒውተር ኔትወርኮችን በሳይበር ወንጀለኞች መጠለፉ ይፋ የሆነው በታህሳስ ወር ነበር።

የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል በአገሪቱ ውስጥ በጣም ዝነኛ የሆኑን አንዳንድ የክስ ሂደቶች የሚይዙ በአራቱ የኒው ዮርክ ጠበቃ ቢሮዎች ውስጥ ሠራተኞች የሚጠቀሙባቸውን 80 በመቶ የማይክሮሶፍት ኢሜይሎች ያጠቃልላል።

የቀድሞው የፌዴራል አቃቤ ሕግ ሬናቶ ማሪዮቲ እንዳሉት "በእነዚህ መስሪያ ቤቶች ውስጥ በጣም ሚስጥራዊ ምርመራዎች አሉ" ብለዋል።

ከዚህም ውስጥ ከፍተኛ የፋይናንስ ምርመራዎች ይገኙባቸዋል ይህ ማለት በጠለፋው የተገኘው መረጃ ለጥቆማ ወይም ለዝርፊያ ሊያገለግል ይችላል ብለዋል።

መስሪያ ቤቱ እንደሚለው ጠላፊዎች እስከ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ድረስ ያለውን መረጃ መዝብረው ሊሆን ይችላል ይህም ማለት የሶላር ዊንድስ ጠለፋ ይፋ ከመደረጉ ሰባት ወራት በፊት ያለውን ነው።

መስሪያ ቤቱ የጠለፋው ሁሉንም ተጎጂዎች ማሳወቃቸውን እና በጠለፋው የተከሰተውን "የአሠራር ፣ የደህንነት እና የግላዊነት አደጋዎችን" ለማቃለል እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

ሆኖም ግን በጠለፋው ምን ዓይነት መረጃ እንደተወሰደ አልተገለጸም።

በሚያዝያ ወር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለሶላር ዊንድስ ጥሰት እና ለሌሎች የሳይበር ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።

ሩሲያ ምንም አይነት ጥሰት አልፈፀምኩም ስትል አስተባብላለች።

ነገር ግን ማሪዮቲ እንደሚሉት የትኛውም የውጭ መንግሥት ሚስጥራዊ የሆኑ የሕግ ፋይሎችን ከያዘ በህዝብ ላይ ወይም በምርጫዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሊጠቀምባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

"የውጭ መንግሥታት እንዲህ ዓይነቱን መረጃ ማግኘት የሚፈልግበት ሁሉም ዓይነት ምክንያቶች አሉ" ብለዋል።