የተለያዩ አገራት አትሌቶች ከቶኪዮ ወደ አገራቸው ሲመለሱ የሚጠብቋቸው አስደናቂ ሽልማቶች

የፊሊፒንሷ ስፖርተኛ ሂዲለያን ዲያዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የፊሊፒንሷ ስፖርተኛ ሂዲለያን ዲያዝ

በኦሊምፒክ መድረክ አገርን ወክሎ አሸናፊ መሆን ከሚያስገኘው ትልቅ ሐሴት፣ ክብርና ታዋቂነት በተጨማሪ በርካታ አይነት ሽልማቶችም ይዞ ይመጣል።

የተለያዩ አገራትም በኦሊምፒክ ተሳትፎ ያደረጉ ተወዳዳሪዎችን የተለያዩ አይነት ሽልማት ይሰጣሉ።

ነገር ግን አንዳንድ አገራት ለስፖርተኞቹ ከሚሰጡት ማበረታቻዎች መካከል ከገንዘብ እስከ መኖሪያ ቤት፤ አንዳንዴ ደግሞ ከብት ጭምር ይበረከታል።

በኢትዮጵያም ቢሆን መጠኑ ይለያይ እንጂ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ውጤት ላስመዘገቡ ስፖርተኞች ሽልማት ሲበረከት ቆይቷል።

በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ አትሌቶች በመሳተፋቸው ብቻ ዓለማ አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚሰጣቸው ገንዘብ ባይኖርም በርካታ አገራት ግን ባንዲራቸውን ላውለበለቡላቸው ስፖርተኞች ጠቀም ያለ ገንዘብና ማበረታቻ ይሰጣሉ።

በዚህም መሠረት በቶክዮ ኦሊምፒክ ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች በአገራቸው የሚያገኙትን ሽልማትና ማበረታቻ እናስቃኛችሁ።

ሁለት ድንቅ መኖሪያ ቤቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የፊሊፒንሷ ስፖርተኛ ሂዲለያን ዲያዝ

የፊሊፒንሷ ስፖርተኛ ዲያዝ በሴቶች 55 ኪሎግራም ክብደት ማንሳት ማሸነፏን ተከትሎ በአገሪቱ እንደ ጀግና እየተሞካሸች ነው። መሞካሸት ብቻ አይደለም ሕይወቷን የሚቀይሩ ሽልማቶችና ማበረታቻዎች እየጎረፉላት ይገኛሉ።

የፊሊፒንስ ስፖርት ኮሚሽን እና የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በጥምረት ገንዘብ በማዋጣት ለዚህች ስፖርተኛ 600ሺህ የአሜሪካ ዶላር (27 ሚሊየን ብር አካባቢ ማለት ነው) እንደሚሰጧት ቃል ግበተውላታል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሁለት እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተሰጥተዋታል።

የፊሊፒንስ አየር ኃይል ውስጥ በወር 500 ዶላር እየተከፈላት ታገለግል የነበረችው ዲያዝ እነዚህ ሽልማቶች ሕይወቷን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀይሩትና ብርታት እንደሚሰጣት መገመት ከባድ አይሆንም።

ይህች ስፖርተኛ በሚያስገርም ሁኔታ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ስትዘጋጅ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከል ውስጥ እንኳን የመሰልጠን እድል አላገኘችም ነበር። እንደውም በአካባቢዋ ያገኘቻቸውን ብረቶች እንዲመቻት አድርጋ ነበር ክብደት ማንሳት ስትለማመድ የቆየችው።

የገንዘብ ሽልማት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ማሌዢያ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ለሚያመጡ አትሌቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እሸልማለሁ ብላለች። [የማሌዢያ አትሌቶች ባድሜንተን ውድድር የብር ሜዳሊያ አጊንተዋል]።

የገንዘብ ሽልማት መጠን ከአገር አገር ይለያያል።

በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የሚታወቁትና አትሌቶቻቸውን እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ማዕከላት የሚያሰለጥኑ አገራት ለስፖርተኞቹ የሚሰጡት ቀጥተኛ ሽልማት ብዙ ጊዜ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አንዳንዴም አትሌቶች ምንም ሽልማት ላያገኙ ይችላሉ።

ነገር ግን በስንት ጊዜ አንዴ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የሚገቡ አገራት አልያም በውስን የውድድር አይነቶች ብቻ ሜዳሊያ የሚያሰገኙ አገራት ስፖርተኞቻቸውን ለማበረታታት ጠቀም ያለ ገንዘብ በሽልማትነት ያቀርቡላቸዋል።

ለምሳሌ ማሌዢያ በ13 የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ማግኘት የቻለችው 11 ሜዳሊያዎችን ብቻ ሲሆን በቶክዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ለሚያመጣ ስፖርተኛ 241 ሺህ ዶላር፣ ነሐስ ለሚያመጣ ደግሞ 150 ሺህ ዶላር እንዲሁም ብር ለሚያመጣ ስፖርተኛ ደግሞ 24 ሺህ ዶላር እንደምትሸልም አስታውቃለች።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ማሌዢያ በወንዶች የጥንድ ባድሜንተን ውድድር የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ለሚገቡ አትሌቶቻቸውን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ከሚሰጡ አገራት መካከል የተወሰኑት። ሽልማቱ በአሜሪካን ዶላር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቻይና እና ሩሲያ ሜዳሊያ ለሚያስገኝ አትሌት አዲስ እና ዘመናዊ መኪኖችን እንሸልማለን ብለዋል።

አንጸባራቂ ውድ እና አዲስ መኪናዎች

ቻይና እና ሩሲያ ደግሞ በሜዳሊያ ከሚጥለቀለቁት አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

አገራቱ ለስፖርተኞቻቸውን ጠቀም ካለ የገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ በአዳዲስ መኪኖች ያንበሸብሿቸዋል።

ለምሳሌ ሩሲያ በኦሊምፒክ መድረክ የአገራቸውን ባንዲራ ማውለብለብ ለቻሉ ስፖርተኞች በጣም ውድ የሚባሉ መኪናዎችን እና ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ታበረክታለች።

ከብቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ከብቶችን በሽልማት መልክ የተቀበሉ አትሌቶችም አሉ

አንዳንድ ሽልማቶች ደግሞ ለየት ያሉና አስገራሚም ናቸው።

ደቡብ አፍሪካውያኑ ሲዝዌ ንዶቩ፣ ማቲው ብሪቴይን፣ ጆን ስሚዝ እና ጄምስ ቶምሰን በወንዶች ቀላል ክብደት በአውሮፓውያኑ 2012 ለንደን ኦሊምፒክ ላይ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ምርጥ ላሞች በሽልማት መልክ ተበርክቶላቸው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የሕንዷ ክብደት ማንሳት ተወዳዳሪ ሚራቢ ቻኑ የምትሰራበት መስሪያ ቤት የደረጃ እድገትና የደሞዝ ጭማሪ ቃል ገብቶላታል።

የተሻለ ሥራ እና ከአስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ነጻ መሆን

በአንዳንድ አገራት ደግሞ በኦሊምፒክ አሸናፊ መሆን የተሻለ ሥራና የተሻለ ክፍያ የሚያስገኝ ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ከአስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት እስከመቅረትም ያደርሳል።

የሕንዷ ክብደት ማንሳት ተወዳዳሪ ሚራቢ ቻኑ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ 350 ሺህ ዶላር ሽልማት የተበረከተላት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የምትሰራበት መስሪያ ቤት የሆነው 'ኢንዲያን ሬልዌይ ሰርቪስ' የደረጃ እድገትና የደሞዝ ጭማሪ ቃል ገብቶላታል።

በደቡብ ኮሪያ ደግሞ ሜዳሊያ ማምጣት የቻሉ ስፖርተኞች ጠቀም ያለ የገንዘብ ሽልማት የሚሰጣቸው ሲሆን ዋነኛው ሽልማታቸው ግን ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የአገሬው ዜጎች መቅረት የማይችሉበት የ18 ወራት ወታደራዊ አገልግሎት እንዲቀርላቸው መደረጉ ነው።

ነገር ግን ለበርካታ አትሌቶች በመንግሥታቸው የሚሰጣቸው ገንዘብና ማበረታቻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ስፖርተኞች በቂ የሆነ ስልጠና ለማግኘት እንኳን የሚያስችላቸው የገንዘብ አቅም የላቸውም።

ለምሳሌ ሳትጠበቅ በኦሊምፒክ መድረክ በሴቶች ጂምናስቲክስ ሁለት ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ የቻለችው ብራዚላዊት ሬቤካ አርናልዴ በብራዚል መንግሥት ድጎማ ነበር የምትኖረው።

ባለፈው ኅዳር ወር አንድ ዓለመ አቀፍ የጥናት ተቋም ከ48 አገራት የተወጣጡ 500 የሚሆኑ ትልልቅ አትሌቶችን በማነጋገር በሰበሰበው መረጃ መሠረት 60 በመቶ የሚሆኑት በገንዘብ እራሳቸውን መደገፍ እንደማይችሉ ገልጸዋል።

አንዳንድ አትሌቶች እንደውም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ገንዘብ ለማግኘት 'ጎ ፈንድ ሚ' ላይ ጭምር በመሄድ እርዳታ ሲያሰባስቡ ነበር።

ታዲያ እንዲህ ባሉ አስቸጋሪ ጊዜያት አገራት ለስፖርተኞቻቸው መሰል የገንዘብ፣ መኖሪያ ቤት፣ መኪና አንዳንዴም ከብቶች መሸለማቸው በርካታ ታዳጊዎች ለወደፊት መነሳሳትን እንደሚፈጥርባቸው ይታመናል።