በሩዋንዳ ኃይል የሚታገዘው የሞዛምቢክ ጦር ቁልፍ የወደብ ከተማን ከታጣቂዎች ነጠቀ

ሩዋንዳ ከአንድ ወር በፊት 1000 ወታደሮቿን ወደ ሞዛምቢክ ልካ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ሩዋንዳ ከአንድ ወር በፊት 1000 ወታደሮቿን ወደ ሞዛምቢክ ልካ ነበር።

የሩዋንዳ እና የሞዛምቢክ ጥምር ጦር በሰሜናዊ ሞዛምቢክ ቁልፍ ከሆነች የወደብ ከተማ እስላማዊ ታጣቂዎችን ማስወጣቱን የሩዋንዳ ጦር አስታወቀ።

ሞሲምቦአ ዳ ፕራያ የተሰኘችው ይህች የወደብ ከተማ የታጣቂዎቹ የመጨረሻ ምሽግ ነበረች ሲልም ጦሩ አስታውቋል።

ይህች የወደብ ከተማ የምትገኘው በአፍሪካ ትልቁ የጋዝ ክምችት በሚገኝበት በካቦ ዴልጋዶ ግዛት ውስጥ ነው።

ታጣቂዎቹ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሩዋንዳ ከአራት ዓመት በፊት የትጥቅ ትግል የጀመሩትን ታጣቂዎችን ለመዋጋት 1,000 ወታደሮችን ወደ ሞዛምቢክ ልካለች።

ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ3000 በላይ ሰዎች ሲገደሉ 820 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

የሞዛምቢክ መንግሥት ጦር መላ ግዛቲቱን እንደገና በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ እየተዋጋ ይገኛል።

የሩዋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሮናልድ ሪቫቫንጋ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል "የወደብ ከተማው የሽብርተኞቹ የመጨረሻ ምሽግ ነው። ይህ የፀረ-ሽብርተኝነት ሥራዎች የመጀመሪያ ምዕራፍ ማብቂያ ነው'' ብለዋል።

እነዚህን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለማረጋጋት የፀጥታ ሥራዎች ማከናወናችንን እንቀጥላለን ያሉት ቃል አቀባዩ የተፈናቀሉ ሰዎች በቅርቡ ወደ መኖሪያቸው እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የሩዋንዳ ጦር ወደ ሞዛምቢክ ከዘመተ ገና አንድ ወር ብቻ የሆነው ሲሆን ለጊዜውም ቢሆን ጦሩ የሚፈልገውን እያሳካ ነው ተብሏል።

በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነው እና የጦር ሥነ-ምግባር ያለው የሩዋንዳ ጦር የሞዛምቢክ መንግሥት ወታደሮች ለአራት ዓመታት መፈጸም ያልቻሉትን በአንድ ወር ውስጥ ማሳካት ችሏል።

ከሩዋንዳ በተጨማሪ የሌሎች አገራት ወታደሮችም የሞዛምቢክን መንግሥት ለመደገፍ ጦራቸውን ለማዝመት በዝግጅት ላይ ናቸው።

እነዚህን አክራሪ ኃይሎችን መዋጋት ቀላል እንደማይሆን የተነገረ ሲሆን አክራሪው ቡድን ጠንቅቆ ወደሚያውቁት ተራራማ የሞዛምቢክ ስፍራዎች ሸሽቶ እራሱን በአዲስ መልክ አደራጅቶ ዳግም ጥቃት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ትገልጻለች።