እየሰፋ የመጣው ጦርነት ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳት ይሆን?

  • ቢቢሲ
  • ሞኒተሪንግ
የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለህወሓት ታማኝ የሆኑት የትግራይ ኃይሎች ታሪካዊቷን ከተማን መያዛቸው ከስምንት ወራት በፊት 'ተገባዷል' የተባለውን የትግራይ ጦርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረው ይመስላል።

ቢቢሲ የህወሓት አማጺያን ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን መያዛቸውን የከተማዋን ምክትል ከንቲባ ማንደፍሮ ታደሰን እና ነዋሪዎችን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።

ላሊበላ ኢትዮጵያ ካሏት ጥንታዊ ቅርሶች እጅግ ዝነኛውና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። በተለይም የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በብዙኃኑ የኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ቦታ ነው።

አማጺያኑ የላሊበላ ከተማ በእጃቸው መውደቋ ትልቅ ድል ሆኖላቸዋል። አማጺያኑ ከተማዋን መያዛቸው በይበልጥ ወደ ሌሎች የአማራ አካባቢዎችም ዘልቀው ለመግባት ዕድል ይሰጣቸዋል እየተባለ ነው።

ይህም በአፋር በኩል ከከፈቱት ጥቃት ጋር ሲደመር አዲስና ዋነኛ የጦርነት ግንባር ሊያደርገው ይችላል።

አማጺያ ከትግራይ ውጭ ለምን ሄዱ?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ጦርነት ተጠናቋል ብለው ካወጁ ከስምንት ወራት በላይ ተቆጥረዋል። ይህም የሆነው ኅዳር ወር አካባቢ አገር መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክልል ዋና ከተማን በተቆጣጠረበት ወቅት ነበር።

ከሰባት ወራት በፊት መንግሥት በጦርነቱ መልሶ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት ጀመረው ነበር።

ሰኔ ማብቂያ ላይ መንግሥት የተናጥል የተኩስ አቁም ማወጁን ይፋ አደረገ። ይህም የእርሻ ወቅት በመሆኑ ከሰብአዊነት የመነጨ ውሳኔ መሆኑን አስገነዘበ መንግሥት አስገነዘበ። በማግስቱ አንድ የጦሩ ጄኔራል መቀለ ለሠራዊቱ ሸክም እየሆነች መምጣቷን የሚያመላክት ንግግር አደረጉ።

የተናጥል የተኩስ አቁሙ ከታወጀ በኋላ አማጺያኑ መቀለን መልሰው መቆጣጠር የቻሉ ሲሆን፤ ኋላ ላይ ደግሞ አማጺያኑ በሠራዊቱ ላይ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸማቸው ተሰማ።

አሁን ህወሓት የተናጥል የተኩስ አቁሙን ለመቀበል ቅድመ ሁኔታዎችን ደርድሯል። ትግራይን በምዕራብና በምሥራቅ በሚያዋስኑት አማራና በአፋር ክልሎችም ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

መንግሥት አማጺያኑ በአፋር በኩል በመቶዎች የሚገመቱ የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ መኪኖች ላይ ጥቃት ፈጽሟል በማለት ይከሳል።

ተንታኞች በበኩላቸው የአማጺያኑ በአፋር ክልል ጥቃት የመሰንዘር ዋንኛ ግብ ለወጪ ገቢ ንግድ ሁነኛ መተላለፍያ የሆነውን የጂቡቲ አዲስ አበባ መስመር ለመያዝ እንደሆነ ይስማማሉ።

ይህ ጎዳና የአገሪቱን 85 ከመቶ ወጪ ገቢ ቁሳቁስን የሚያስተላልፍ ቁልፍ መስመር ነው።

አማጺያኑ በአማራ በኩል የሚሰነዝሩት ጥቃት ደግሞ ትግራይ በኃይል ተይዘውብኛል የምትላቸውን አካባቢዎች ለማስመለስ ነው ይላሉ።

እነዚህ አካባቢዎች ከ1980ዎቹ ጀምሮ ህወሓት መራሹ ኃይል አገሪቱን በብሔር ፌዴራሊዝም ከፋፍሎ ማስተዳደር ከጀመረበት ወዲህ የይገባኛል ጥያቄዎች ሲነሳባቸው ቆይቷል።

አማጺያኑ ከትግራይ ውጭ እያደረጉት ያለው ግስጋሴ ሌሎች ክልሎች ሠራዊት እንዲያዋጡ ምክንያት ሆኗል።

በሺህ የሚቆጠሩ 'ፈቃደኛ' ወጣቶች የፌዴራል ሠራዊቱን ለመቀላቀል ለስልጠና ካምፕ ገብተዋል። ይህም የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገር አቀፍ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አገኘሁ ተሻገርም በተመሳሳይ የክልሉ ወጣት ልዩ ኃይሉን እንዲቀላቀል ጥሪ አድርገዋል።

ይህ አገር አቀፍ ንቅናቄ በሌሎች አንዳንድ ክልሎች የፀጥታ ኃይል ክፍተት እንዳይፈጥር ግን ስጋት አለ።

ለምሳሌ በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሶማሌና በአፋር በርካታ ግጭቶች በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተከስተው እንደነበር ግምት ውስጥ ሲገባ የጸጥታ አስከባሪ ኃይል ክፍተት እንዳይፈጥር ስጋት ቢፈጠር አስገራሚ አይሆንም።

ሠራዊቱ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ሰሜኑ ጦርነት ማድረጉ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ራሳቸውን ላደራጁ አማጺያን ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንላቸው ይችላል። አዲስ ጥቃት ሊሰነዝሩም እንደሚችሉ ይገመታል።

በሰብአዊ ድጋፍ በኩል ምን እየሆነ ነው?

ይህ ትኩስ ጦርነት በድጋሚ ሲከፈት ከኢትዮጵያ ዋንኛ የክረም ወቅት ጋር ተገጣጥሟል። ይህም ብዙ አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራቸውን የሚያስተጓጉል ነው የሚሆነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በትግራይ ብቻ ከአምስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ይፈልጋል።

የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ሌሎች ተራድኦ ድርጅቶች እንደሚሰጉት እርዳታ በአፋጣኝ ካልደረሰ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ የከፋ ረሀብ ሊያጋጥመው ይችላል። የፌዴራል መንግሥት ግን ይህን ስጋት አይቀበለውም።

ሰኔ 17 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቴሌቪዥን ቀርበው ይህን ስጋት "ፖሮፓጋንዳ" ሲሉ አጣጥለውታል።

መንግሥት አማጺያኑን ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ሕዝብ እንዳይደርስ አሻጥር ይሰራሉ ሲል ይከሳቸዋል።

ሐምሌ መጨረሻ ላይ መንግሥት 150 ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ ከባድ ተሸከርካሪዎች መቀለ መድረሳቸውን ይፋ አድርጓል። ከዚያ ቀን ጀምሮም ከ157 ተሸከርካሪዎች መቀለ መግባታቸው ተነግሯል።

"ተሸከርካሪዎቹ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ቁሳቁሶች ከዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ከተባበሩት መንግሥታት ኤጄንሲዎች፣ ከዩኒሴፍ እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለገሱ የእርዳታ ቁሶች ይዘዋል" ይላል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፋክት ቼክ በትዊተር ገጹ።

በተመሳሳይ ቀን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰላም ሚኒስትሯን ሙፈሪያት ካሚል ጠቅሶ እንደዘገበው መንግሥት ለትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንዳለው ዘግቧል። የሰላም ሚኒስትሯ ይህን የገለጹት ለዩኤስኤይድ ኃላፊ ሰማንታ ፓወር ነው።

ሳማንታ የሰብዓዊ ድጋፍ በበቂ መድረስ አለመቻሉ እንዳሳሰባቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

በቀጣይ ምን ሊከሰት ይችላል?

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁሉን አቀፍ የተኩስ ስምምነት ጥሪ እያቀረበ ባለበት በአሁን ወቅት የትግራይ አማጺያን ግን አሁን ያገኗቸውን ድሎች አጠናክረው ለመቀጠል የሚታገሉ ይመስላል።

በሌላ አንጻር አሁን በፌዴራልና በክልሎች ያለው የሠራዊት እንቅስቃሴና ክተት ምናልባት ለለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት በር እንዳይከፍት ስጋት አለ።

በጦርነቱ የሙትና ቁስለኞች የጉዳት ምጣኔ በአያሌው ሊያሻቅብ እንደሚችልም ይገመታል። ይህም በፌዴራልና በክልሎች ለጦርነት ጥድፊያ ያለ በቂ ስልጠና በርካታ ዜጎችን ወደ ግንባር ለመላክ የሚደረገው ሁኔታ ሊፈጥረው የሚችለው አደጋ ሲታሰብ ነው።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁሉን አቀፍ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ግፊት እያደረገም ጦርነቱ ተፋፍሞ ሊቀጥል እንደሚችል ነው አሁን መሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች የሚጠቁሙት።

ኢትዮጵያ ሱዳን ላሸማግል ማለቷን ሳትቀበል መቅረቷ ተዘግቧል። ይህም ኢትዮጵያ በሱዳን ገለልተኝነት ላይ ያላት እምነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ተከትሎ ነው ተብሏል።

የኤርትራ ሠራዊት ህወሓት ለአሥመራ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ በኢትዮጵያ መሬት ላይ መቆየቱ የሚያጠረጠር ሆኗል።

ሁሉም ተዋጊ ኃይሎች በትግራይ በጦርነቱ ውስጥ ለሚፈጸሙ ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰቶች ተጠያቂዎች ሆነዋል። አሁን ደግሞ ይህ ጥሰት ወደ አማራ ክልልና አፋርም ተስፋፍቷል።

የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት አሁን ከትግራይም አልፎ ወደ ሌሎች ክልሎች እየገባ ይመስላል። ሚሊዮኖች ለከፋ ረሀብና ለችጋር የሚጋለጡበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል ተብሎም ተሰግቷል።