የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊቲስ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ
የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊቲስ በኢትዮጵያ በቅርቡ በነበራቸው ጉብኝት የትግራይ አማጺያን ወታደራዊ አዛዦች ጋር አልተገናኘሁም አሉ።
ማርቲን ግሪፊቲስ ይህን ያሉት ጄኔቭ ከሚገኘው የድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በቅርቡ ስላደረጉት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ዘርዘር ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።
ሹመቱን በቅርብ ያገኙት ማርቲን በመጀመሪያ የሥራ ጉዟቸው መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ማድረጋቸው ይታወሳል።
አስተባባሪው ወደ ኢትዮጵያ በፍጥነት መሄዴ በጣም አስፈላጊ ነበር ብለዋል ለጋዜጠኞች።
ለስድስት ቀናት በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረጉት ኃላፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አግኝተው ማነጋገራቸውን ተናግረዋል።
"ከትግራይ ክልል ስለመለስ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ማግኘቴ በጣም አስፈላጊ ነበር። ምክንያቱም ሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተ በጋራ መሥራት እንደምንችል ማውራት ስላለብን። እርዳታና ከለላ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች እንዴት መድረስ እንደሚቻል ካገኘኋቸው ሰዎች ጋር ገንቢ የሆነ ንግግር አድርጊያለሁ" ብለዋል አስተባባሪው።
በተባበሩት መንግሥታት አውሮፕላን ወደ ትግራይ ክልል የተጓዙት የእርዳታ ማስተባበር ኃላፊው ከተፈናቀሉ ሰዎች፣ ከሴቶች ከአስተማሪዎች እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።
አልፎም ከጥቅም ውጪ የሆኑና የተዘረፉ መሠረተ ልማቶችን መመልከታቸውን ለጋዜጠኞች አሳውቀዋል።
"የእርዳታ ሥራው በቀን 100 የጭነት መኪናዎችን ይጠይቃል። ነገር ግን እኔ እዚያ በነበርኩበት ወቅት 178 መኪኖች ብቻ አፋር ላይ ቆመው ነበር። በኋላ ላይ ወደ መቀለ መጓዛቸውን ሰምተናል። አሁን 40 መኪኖች ለመግባት እየተጠባበቁ እንደሆነ ሰምቻለሁ። የእኛ ዓላማ በቀን 100 መኪኖች ነው" ብለዋል።
ኃላፊው በትግራይ በነበራቸው ቆይታ "ከክልሉ አስተዳዳሪዎች ጋር" መነጋገራቸውንና ዘንድሮ የታረሰው መሬት ቢበዛ ከወትሮው ግማሽ በላይ እንደማይሆን መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ማርቲን ግሪፊትስ አክለው የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት የቁሳቁስ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
"የተዘረፉና የወደሙ የጤና ተቋማትን አይተናል። የጤና ባለሙያዎች አሉ ግን ደመወዝ የሚከፍላቸው የለም። የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ ተቋማቱ ቢያንስ መሠረታዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ለማድረግ እየሠሩ ነው። በሦስት ሳምንታት ውስጥ በትግራይ ክልል ያሉ ሕፃናትን የኩፍኝ በሽታ ክትባት መስጠት እንጀምራለን። እነዚህ ቁሳቁሶች መድረስ አለባቸው" ብለዋል።
ኃላፊው ከትግራይ ሲመለሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሰላም ሚኒስትሯ ጋር ገንቢ ውይይት እንዳደረጉ ጠቅሰዋል።
ነገር ግን የሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶችና ሰዎች በሕዝቡ ዘንድና በማኅበራዊ ሚድያ እየተወቀሱ ነው ይላሉ ኃላፊው።
ማርቲን ግሪፊትስ ይህ መቆም አለበት ይላሉ። በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት የዩኤስአይድ ኃላፊም ተመሳሳይ ሐሳብ ማንሳታቸውን ያወሳሉ ኃላፊው።
"ያገኘኋቸው ሚኒስትሮች ይህ እንደማይቀጥል ቃል ገብተውልኛል። እኔ አንዳንድ ሰዎች አሉ የምትሉ ከሆነና ማስረጃ ካላችሁ ንገሩን። እኛ እንመረምራለን፤ ብያቸዋለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
አስተባባሪው ሁለት ወይም ሦስት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መታገዳቸውን መስማታቸውን ጠቅሰው ነገር ግን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየመከሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኃላፊው በግጭቱ ምክንያት 100 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከአማራ ክልል መፈናቀላቸውን ተናግረው፤ ከአማራ ክልልና ከሶማሌ ክልል ፕሬዝደንቶች ጋር በእርዳታ አቅርቦት ዙሪያ መምከራቸውን አውስተዋል።
ማርቲን ግጭቱ መቆም አለበት፤ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ተኩስ ማቆም በጣም አስፈላጊ ነው ይላሉ። አክለው የፌደራሉን መንግሥት የተኩስ አቁም አዋጅ በመልካም እንደሚያዩት ነገር ግን በዚህ ላይ ተመርኩዞ ብዙ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኃላፊው ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ በአፋር ክልል የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ ተሸካርካሪዎች በቀላሉ መተላለፍ ያልቻሉት በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህንን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብረው እየሠሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ከትግራይ አማፂያን ጋር ተገናኝተው እንደሆነ እና አማፂያኑ ጥቃት የማቆም ሐሳብ አላቸው ወይ ተብለው የተጠየቁት ማርቲን ግሪፊትስ፤ "እኛ ከትግራይ ወታደራዊ አዛዦችና ፖለቲካዊ መሪዎች ጋር ግንኙነት የለንም። እንደምታውቁም እኛ የእርዳታ ሥራ አቅራቢዎች ነን። ስለዚህ ከወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ ሆስፒታል ከሚያስተዳድሩ ጋር ብቻ ነው ግንኙነታችን። እኛ ሁለቱን አካላት ማወያየት ሥራችን አይደለም" ሲሉ ምላሸ ሰጥተዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናጥል ተኩስ አቁም አድርገዋል። ይህን የምጠራጠርበት ምክንያት የለኝም። ወደ አፋርና አማራ ክልሎች እያቀኑ ያሉት የትግራይ ኃይሎች ሊረዱት የሚገባው ነገር እኛ በቀን 100 መኪኖች ያለ ተኩስ አቁምም ቢሆን ማስገባት ነው ዓላማችን። ነገር ግን ጦርነት ቢቆም ለትግራይ ሕዝብ መልካም ነበር። እኔ የእርዳታ አስተባባሪ እንጂ አደራዳሪ አይደለሁም ስለዚህ እጄን ወደዚያ ባልሰድ ይሻላል።"
ኃላፊው ከዚህ በኋላስ የትግራይ ኃይሎችን የማግኘት ሐሳብ አለዎት ወይ ተብለው ተጠይቀው ይህ የእሳቸው መሥሪያ ቤት ሥራ እንዳልሆነ ነገር ግን ጦርነቱ መቆም እንዳለበት እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
"የትግራይ ሕዝብ ደኅንነትና ብልጽግናን ማስጠበቅ ከፈልግክ ትክክለኛው መንገድ ግጭቱን ማቆም ነው። የተናጠል ተኩስ አቁም መልካም ነገር ቢሆንም ሊስፋፋ ይገባል።"
ኃላፊው በቅርቡ ባደረጉት ጉብኝታቸው በአብዛኛው ትግራይ ክልል ምንም ዓይነት ግጭት እንደሌለ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።