ኢትዮጵያ ስለምትካፈልበት የአፍሪካ ዋንጫ እነማን ምን አሉ?

የአፍሪካ ዋንጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካሜሮን በየምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ትላንት ይፋ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ የውድድሩ አስተናጋጅ ካሜሮን በምትገኝበት ምድብ 'ሀ' ውስጥ ከቡርኪናፋሶ እና ከኬፕ ኤርዲ ጋር ተደልድላለች።

የምድብ ድልድሉ ይፋ በተደረገበት ዝግጅት ላይ የተለያዩ አገራት ተወካዮች እና የቀድሞ ተጫዋቾች ተገኝተው ነበር።

ቢቢቢ ስለ ምድብ ድልድሉ እና ስለ ቅድመ ዝግጅቱ ከቀድሞ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞችን ጠይቋል።

ካሜሮን መገኘቱ እንዳስደሰተው የተናገረው አል ሃጂ ዲዩፍ "በዚህ ዝግጅት ላይ ስለጋበዙኝ ለካሜሮን ሕዝብ እና ለካፍ ምስጋናዬ ይድረስ" ብሏል።

ዝግጅቱ የተቃና ስለነበረም ካሜሮንን እንኳን ደስ አላችሁ ያለው ዲዩፍ ስለአገሩ ሴኔጋል ተጠይቆም "ምድቡን በቀዳሚነት ማጠናቀቅ አለብን። ይህን ለማደረግም የሚቻለንን እናደርጋለን። ጥሩ በመጫወት ውድድሩን ማድመቅ አለብን" ብሏል።

እስከ ውድድሩ ፍጻሜ ድረስ ጨዋታዎችን ማሸነፍ፣ ትኩረት ማድረግ እና ጥሩ መጫወት ያስፈልጋል ያለው ዲዩፍ "የዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከአፍሪካ ዋንጫው ውድድር በፊት መሆኑ ለውድድሩ ይበልጥ እንድንዘጋጅ ያደርገናል" ሲል ሃሳቡን አጠናቋል።

ዲዲየ ድሮግባ በበኩሉ "በዚህ ደረጃ ላይ ስትገኝ ሁሉም 24 አገራት ለማሸነፍ ነው የሚፈልጉት" ሲል ሃሳቡን ገልጿል።

ስለዚህ ውድድሩ "ለግብጽ ለካሜሮን እና ለሁሉም ቡድኖች ከባድ ነው። ቢሆንም ጥሩ እግር ኳስ እንደምንመለከት አስባለሁ" ብሏል።

የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኑት ጌርኖ ሮር ከባድ ምድብ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።

"ግብጽና ሱዳን አሁን ጥሩ እየሆኑ ነው፤ ጊኒ ቢሳዉ አለች። ስለዚህ እንደናይጄሪያ ላለ ቡድን አደገኛ ነው። ማንንም ማሳነስ አያስፈልግም ሁሉንም በደንብ ማየት አለብን" ብለዋል።

በማጣሪያው አለመሸነፋቸውን አንስተው በውድድሩም መሸነፍ አንፈልግም ሲሉ ገልጸዋል።

ለመዘጋጀት እና ተጋጣሚዎቻችንን ማጥናት አለብን ያሉት አሰልጣኙ ቀጣዩ ትኩረት ከላይቤሪያ ጋር ያለው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነው መሆኑን ጠቁመዋል።

"ከባድ ጨዋታ ነው። በቀጣይ ወደ ካፕ ቨርዴ እናቀናለን። ውድድሩ ጥር ላይ በመሆኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ለመዘጋጀት ጊዜ አለን።"

"የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለዝግጅት ይረዳናል በተለይም ጥሩ ውጤት ካስመዘገብን ለበራስ መተማመን ይረዳናል። በሦስት ወር ስድስት ጨዋታ አለን። ብዙዎቹ ተጫዋቾች ከእንግሊዝ ስለሚመጡ በመጨረሻ ሰዓት ነው የሚመጡት ቢሆንም ለግብጹ የመጀመሪያ ጨዋታ እንዘጋጃለን" ሲሉ ገልጸዋል።

የካሜሮን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቿ ጋይል ኤግናሙት ሁሉም ምድብ ጠንካራ መሆኑን ጠቁማለች።

ብዙ ጠንካራ ቡድኖች በውድድሩ መኖራቸውን ጠቁማ "ጠንካራ ቴክኒሻን አለን። ጥሩ ሥራ ይሰራል። ለፍጻሜው የማንደርስበት ምንም ነገር የለም" ብላለች።

ሕዝቡ የወንዶቹን ቡድን ለመደገፍ እና ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ እንደሚደግፉ ተስፋዋን ገልጻለች።

የሴቶቹ ቡድንም ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር እንደሚደርስ አስታውቃለች።

"ከመጫወት በፊት መደሰት ከባድ ቢሆንም የፈለኩት አይነት ምድብ ነው የደረሰን ያሉት" ጋምቢያው አሰልጣን ቶም ሴንትፌት ናቸው።

ቱኒዚያ ጥሩ ቡድን መሆኑን ጠቁመው "እንደ የቱኒዚያ ዓይነት ቡድን ይስማማናል" ሲሉ ገልጸዋል።

"ማሊ እና ሞሪታኒያ በምድቡ አሉ። በዚህ ደስተኛ ብሆንም ተጋጣሚዎቻችንን ዝቅ አድርገን አናይም። ቡድኖቹ ጥሩ ቢሆኑም ለእኛም ዕድሎች ናቸው" ብለዋል።

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ስለሌለባቸው የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ጠቁመው ለዓለም ዋንጫው ማጣሪያ የሚሰተፉ ቡድኖች በመኖራቸው ጥሩ ቡድን ላያገኙ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

የመጨረሻውን 23 ተጫዋቾች ለመምረጥ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ካሜሮን እግር ኳስ የሚወድ አገር ነው። ስታዲየሞቹም ጥሩ ይመስላሉ። ሌሎቹን መሠረተ ልማቶች አላውቅም። ግን የእግር ኳስ አገር ነው። እዚህ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።

ጋምቢያ በውድድሩ እስከምን ለመጓዝ እንደምትጫወት ተጠይቀው "ጋምቢያ ለልምድ ነው እዚህ ያለነው። የቻልነውን ያህል እንሄዳለን። የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫችን ነው። በዚህ ውድድር ሁሌም ለመሳተፍ ነው የምንፈልገው" ሲሉ ምላሽ ሰጥዋል።