ለህሙማን ሌላ ህመም የሆነባቸው የመንግሥት ጤና ተቋማት ዋጋ ጭማሪ

ታሞ የተኛ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, MARCO LONGARI

ሠላማዊት የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። እናቷ ባለባቸው ህመም ምክንያት በየጊዜው ሐኪም ቤት ይመላለሳሉ። ሁሌም እንደምታደርገው እናቷ ላለባቸው ቀጠሮ በቅርቧ ወደሚገኘው ጤና ጣቢያ ይዛቸው ታቀናለች።

ጤና ጣቢያውን ከቅርበቱም በላይ በዋጋውም ተመራጭ ነው። ስትደርስ የገጠማት ግን ከከዚህ በፊቱ የተለየ ነው።

ዋጋው አይቀመስም። ካላቸው አቅም አንጻር ያልጠበቁትም ነው። "5 ብር የነበረው የካርድ ዋጋ 50 ብር ደርሷል።"

"ካርድ ብቻም አይደለም። ሁሉም የአገልግሎቶች ዋጋ ጨምሯል" ትላለች ሠላማዊት። ህክምና ላይ ያለው ምርጫ ደግሞ አንድ ብቻ ነው፤ መታከም።

ሠላማዊትም ወደ ግል የጤና ተቋም እንዳትሄድ ዋጋው ከዚህም ይብሳል። "ያለኝ አማራጭ ስልክ ደውዬ ተጨማሪ ብር በብድር እንዲያመጡልኝ ማድረግ ነው" ትላለች።

ነጻ የነበሩ አገልግሎቶችም ዋጋ ተቆርጦላቸዋል። የመንግሥት የህክምና ተቋማት ዋጋ መናር አዲስ አበባ ላይ ብቻ አልታጠረም።

ዶክተር ሱራፌል አየለ ይባላሉ። የጎንደር ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ሐኪም ናቸው። በሆስፒታሉ የአገልግሎት እና የህክምና ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ይላሉ።

'ትዕዛዙ ከፌዴራል የመጣ ነው' ያሉት ጭማሪ 'አስገራሚ' መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል። "ካርድ ማውጫ 5 ብር ነበር፣ አሁን 60 ብር ነው። ተኝቶ ለመታከም የአልጋ ክፍያ በቀን ከ10 ብር ወደ 180 ብር አድጓል። የላብራቶሪ እና ሌሎች ወጪዎችም በተመሳሳይ ጨምሯል" ብለዋል።

እንደ ዶ/ር ሱራፌል ከሆነ ከዚህ ቀደም ነጻ የነበሩ አገልግሎቶችም ዋጋ ተቆርጦላቸዋል።

"በነጻ ተኝተው ይታከሙ የነበሩ የምግብ እጥረት ያለባቸው ታካሚዎች (SAM Patients) አሁን ከሌላው እኩል ለአልጋ 180 ብር እየከፈሉ ነው። ልጁ በድህነቱ ምክንያት ምግብ አጥቶ የቀጨጨበት ወላጅም በቀን 180 ብር እንዲከፍል ይደረጋል" ይላሉ።

ቢቢሲ ከተለያዩ ምንጮች ባደረገው ማጣራት በመንግሥት የህክምና ተቋማት የሚሰጡ ዋጋዎች ጭማሪ የተለያየ መሆኑን አረጋግጧል።

ትኩረቱን በህክምና ባለሙያዎች ላይ ባደረገው ሐኪም በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ሐሳባቸውን ያሰፈሩት የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ዮናስ ላቀው 'የአማኑኤል ሆስፒታል የዋጋ ጭማሪ' በሚል ርዕስ የሚከተለውን አስቀምጠዋል።

"በፊት የካርድ 5 ብር የነበረው 50 ብር ሆኗል። ለተኝቶ ህክምና ማስያዣ 400 ብር የነበረው 9,000 ብር ሆኗል። ለአልጋ በቀን 3 ብር የነበረው 118 ብር ሆኗል።" ከአዲስ አበባ የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ ደግሞ ወራቤ እናቅና።

ዶ/ር ፈድሉ ጀንፋ በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው። እርሳቸው በሚሠሩበት ሆስፒታሉም በተመሳሳይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ይገልጻሉ።

የዋጋ ጭማሪው በተለያዩ ደረጃ የሚገለጽ መሆኑን ጠቁመው ለምሳሌ "የአልትራሳውንድ ዋጋ ከ150 ብር ወደ 300 ብር ከፍ ብሏል። ተኝቶ ታካሚዎች በቀን ለአልጋ ይከፍሉት የነበረው 47 ብር አሁን ወደ 170 ብር ከፍ ብሏል" ይላሉ።

የዋጋ ጭማሪው ሁሉንም አይመለከትም

ይህንን የዋጋ ክለሳ ያደረገው ጤና ጥበቃ ሚንስትር መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ናቸው።

"ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ዋጋ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ እና ከቆይታ፣ ከዋጋና ከብር የመግዛት አቅም አንጻር መስተካከል እንደነበረበት ይጠበቃል" ብለዋል። በተጨማሪም [በመንግሥት የጤና ተቋማት ላይ] አገልግሎት ላይ የሚቀርብ ቅሬታ አለ።

"ቅሬታውን ለመፍታት ደግሞ ሃብት ያስፈልጋል" ይላሉ ወይዘሮ ፍሬይህይወት። "በነበረው አሠራር ለህክምናው ዘርፍ ከሚወጣው ወጪ 60 ወይንም 70 በመቶ የሚሆነው በመንግሥት ነበር የሚሸፈነው። ቀሪው ነው በኅብረተሰቡ" ብለዋል።

የዋጋ ጭማሪው በጤና መድኅን ስር የታቀፉትን አይመለከትም። ዶ/ር ዮናስ ላቀው "ይህ ለውጥ የጤና ሚኒስትር በደነገገው መመሪያ መሠረት ነው። የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ያላቸው ታካሚዎች አሁንም በነጻ አገልግሎት ያገኛሉ። የሌላቸው ግን አገልግሎት ለማግኘት ክፍያ መፈፀም ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ህክምና ማግኘት የሚገባቸው ሰዎች እያገኙ አይደለም። "የህሙማን ቁጥር መቀነስ እንዳለ ጠቅላላ ሐኪሞች (ጀነራል ፕራክቲሽነርስ) ይነግሩናል። ሆስፒታል ገብተው በመተኛት መታከም የሚገባቸው በገንዘቡ ምክንያት አልገቡም እንደሚባል ሰምቻለሁ" ያሉት ዶ/ር ፈድሉ ናቸው።

የታካሚዎች ቁጥር በመቀነሱ የሚስማሙት ዶ/ር ሱራፌል "[ዋጋውን ሲያውቁ] በር ላይ ደርሰው ይመለሳሉ። አሁን አብዛኛዎቹ ታካሚዎች በዋጋ ጭማሪው ምክንያት እየተቸገሩ፣ ህክምና አቋርጠው ለመውጣት እየተገደዱ፣ አስፈላጊ መድሃኒቶችን ለመግዛት እና ምርመራዎችን ለማድረግ እየተቸገሩ ሲሆን የጤና መድኅን ተጠቃሚ የሆኑ ታካሚዎች ግን ያለ ምንም ችግር እየታከሙ ይገኛል" ብለዋል።

በጤና መድኅን እጦት ምክንያት ወደ ህክምና ተቋማት የሚመጣ ሰው በመቅረቱ ወይም በክፍያው ምክንያት ተገቢውን ህክምና ባለማግኘቱ ህይወት ልናጣ እንችላለን ሲሉ ሃሳቡን የሚደግፉት ዶ/ር ፈድሉ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Somchai um-im

የጤና መድኅን ያላቸውም በፈለጉት ቦታ መታከም አልቻሉም

ሌላው በህክምና ባለሙያዎች የተነሳው አሠራሩ ሊተገበር ስለመሆኑ ቀደም ተብሎ ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ እና ዝግጅት እንዲኖር መደረግ ነበረበት የሚል ነው።

አሠራሩን ተግባራዊ ከማድረግ በፊት ኅብረተሰቡ እንዲያውቅ እና እንዲዘጋጅ የስድስት ወር ቅድመ ዝግጅ ቢደረግበት የተሻለ ይሆን ነበር ይላሉ ዶ/ር ፈድሉ።

ወ/ሮ ፍሬህይወት ግን ኅብረተሰቡን ዝግጁ የማድረግ ሥራ የእነርሱ መሥሪያ ቤት አለመሆኑን በመጥቀስ ይህ የሚመለከተው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላው የተነሳው ችግር የጤና መድኅን ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ በሁሉም የመንግሥት የጤና ተቋማት ላይ መጠቀም አለመቻላቸው ነው።

"ያለው ዞናዊ አሠራር ነው። [በኛ ዞን የወጣ የጤና መድኅን] የሚሠራው በእኛ ዞን ብቻ ነው። ከአጎራባች ዞን ለሚመጡት አገልግሎት አይሰጥም። ስለዚህ ለመክፈል ይገደዳሉ። በዞን ብቻ መሆን የለበትም በክልል ደረጃ ወይንም በአገር አቀፍ ደረጃ መሆን አለበት" ይላሉ ዶ/ር ፈድሉ።

ተመሳሳይ ችግር እንዳስተዋሉ ዶ/ር ሱራፌልም ለቢቢሲ ተናግረዋል። አንድ ታካሚ ጎንደር ላይ ማግኘት ያልቻለውን ህክምና ለማግኘት ወደ ባህርዳር ቢያቀና ባለው የጤና መድኅን የሚሸፈን ባለመሆኑ ለመክፈል ይገደዳል ብለዋል። ይህ ደግሞ የጤና መድኅኑም ቢሆን ለሁሉም ነጻ ህክምና አያስገኝም ማለት መሆኑን አስረድተዋል።

የጤና መድኅኑ በሁሉም የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደማያስገኝ የሚስማሙት ወ/ሮ ፍሬህይወት "አሁን ያለው አሠራር የሪፈራል ሰንሰለቱን ጠብቆ ነው የሚሄደው" ይላሉ።

ይህም ማለት አንድ ታካሚ የጤና መድኅኑን ካገኘበት አካባቢ ካለ የጤና ተቋም በመሄድ ህክምና ያገኛል። ህክምናው ነጻ ነው። ህክምናው ከዚያ ተቋም በላይ ከሆነ ሪፈር ተጽፎለት ወደሚቀጥለው የጤና ተቋም ሄዶ መታከም ይችላል። በዚህ መልኩ ሲኬድም ህክምናው ነጻ ነው። ስለዚህ የሪፈር ሰንሰለቱን ይዞ እንጂ በራሱ መንገድ ሁሉም ጋር በመሄድ ነጻ መታከም አይችልም ማለት ነው።

ይህን ለመፍታት የጤና ተቋማት ከብዙ የጤና ተቋማት ጋር ውል እንዲገቡ እና አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ወ/ሮ ፍሬህይወት ተናግረዋል።

የጤና መድኅኑ ምዝገባ በዲጂታላይዝ አለመሆኑንም በምክንያትነት አቅርበዋል።

ምዝገባው ዲጂታላይዝ አለመሆኑ ታካሚዎች በተለያዩ የጤና ተቋማት ሄደው ለመታከም ካርዱን ሲጠቀሙ ለማመሳከር እንቅፋት መሆኑ ነው የችግሩ መነሻ።

ለሁሉም ያልተዘጋጀ የጤና መድ

ሌላው ችግር ደግሞ የጤና መድኅኑ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ያማከለ መሆኑ ነው። የመንግሥት ሠራተኞች እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በጤና መድኅኑ የማይታቀፉ መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሱራፌል እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።

የጤና መድኅኑ መደበኛ ባልሆነ የሥራ ዘርፍ የተሠማሩ እና ወር ጠብቀው ቋሚ ደመወዝ የማያገኙ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። "አሁን ተግባራዊ የተደረገው የጤና መድኅን መደበኛ ባልሆነ ሥራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ እና ከ10 በታች በሚቀጥሩ የሥራ ዘርፎች እና ዝቅተኛ የኑሮ መጠን ላይ ያሉትን እንደሚያቅፍ" ወይዘሮ ፍሬህይወት አረጋግጠዋል።

በቅርቡ ደግሞ ሌሎችንም ለማካተት የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ ችግሩ እንደሚፈታ ተናግረዋል። የጠየቅናቸው የህክምና ባለሙያዎች በዋጋ ጭማሪው ላይ ብዙም ቅሬታ ያላቸው አይመስሉም።

የማይስማሙት በተጨመረው ዋጋ መጠን እና በተጨመረበት ጊዜ ላይ ነው። ካነሷቸው ችግሮች ጎን ለጎን "አጠቃላይ ሃሳቡ ኅብረተሰቡን ወደ ጤና መድኅን ለማስገባት ይመስላል። ምክንያቱም ከኪስ ተከፍሎ አይቻልም።

ሁሉም ሰው በከፈለው ገንዘብ ይታከማል። የሴክተሩ ገንዘብም ይሻሻላል። ዕቅዱ እንደ ምዕራባውያኑ እና አሜሪካ ለማድረግ ነው። በአጠቃላይ አሠራሩን እደግፈዋለሁ። ዕቅዱ የጤና ሴክተሩን ለማሳደግ ነው። የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግም ያለመ ነው" የሚሉት ዶ/ር ፈድሉ ናቸው።

"ለምን በዚህ መጠን ዋጋ እንደጨመረ ለማወቅ ባደረኩት ጥረት ሆስፒታሎች ከዚህ በፊት ከመጠን ባነሰ ዋጋ አገልግሎት ሲሰጡ ስለነበር ለከፍተኛ ኪሳራ እንደተዳረጉ እና አሁን የወጣው ዋጋ ግን ተገቢው ክፍያ እንደሆነ ነው። በተጨማሪም በገጠር የሚኖረው ማኅበረሰብ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማበረታታት ነው" ይላሉ ዶ/ር ሱራፌል።

"ሌላው ጥያቄ የሆነብኝ ነገር 'ሆስፒታሎች ይህን የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ የሚሰጠው አገልግሎት ጥራትና ፍጥነቱ ከድሮው በተለየ ይጨምራል ወይ?' የሚለው ነው። ይህን በሂደት የምናየው ይሆናል። የታካሚዎቻችን መቸገር እና መንገላታት ግን ለህክምናውም ለሃኪሙም ከባድ ራስ ምታት ነው። ተገቢው ትኩረት እና መፍትሄ ያስፈልገዋል" ብለዋል።

የሠላማዊት እናት ህክምናቸውን ተከታትለው አገግመዋል። እሷም በቀጣዩ ቀን ዓመታዊ ክፍያ ፈጽማ የጤና መድኅን አባል ሆነዋል። በየጊዜው በእናቷ ምክንያት ሐኪም ቤት የምትመላለሰው ሠላማዊት አሁን "እፎይ ብያለሁ" ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, arnitorfason

40 ሚሊዮን ሰዎች በጤና መድን ታቅፈዋል

የጤና መድህን ማለት አንድ ቤተሰብ በአመት የተወሰነ ብር በመክፈል የቤተሰቡ አባል ሲታመም በነጻ አገልግሎት የሚያገኝበት መንገድ ነው።የጤና መድኅን የተጀመረው ኅብረተሰቡ ባልተጠበቀ ወጪ ወዳልታሰበ ድህነት እንዳይገባ ለማድረግ ነው ይላሉ ፍሬህይወት።

መደበኛ ያልሆነ የሥራ ዘርፍ እና በወር ቋሚ ደመወዝ የማይከፈላቸው ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። አሠራሩ ተግባራዊ ከተደረገ 10 ዓመት ይሆነዋል።

40 ሚሊዮን ያህል አባላት እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል። ካሉት አባላቱ መካከል 24 በመቶ ከድህነት ወለል በታች በመሆናቸው (8 ሚሊዮን ያህሉ መሆኑ ነው) ወጪያቸውን የሚሸፈነው በመንግሥት ነው።

እንደ የአካባቢው በሚለያይ ክፍያ በዓመት አንድ ጊዜ በሚደረግ ክፍያ አባል መሆን ይቻላል። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ ላይ አንድ አባወራ በዓመት 350 ብር በመክፈል ይመዘገባል።

የጥቅም ማዕቀፉም የልብ እና የአዕምሮ ህክምናን ጨምሮ እስከ አዲስ አበባ ድረስ በመንግሥት የህክምና ተቋማት የሚሰጥ ይሆናል።

አሁን በጤና ጥበቃ በመንግሥት የጤና ተቋማት ላይ ተደረገውን ጭማሪን ተከትሎ የጤና መድኅኑ ዓመታዊ ክፍያ ላይ ክለሳ በማድረግ ጭማሪ ሊኖር አንደሚችልም ወ/ሮ ፍሬህይወት ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የጤና ጥበቃን ሃሳብ ለማካተት በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።