መሬት መንቀጥቀጥ፡ በሄይቲ የሟቾች ቁጥር ወደ 2 ሺህ ተጠጋ

የነፍስ አድን ሠራተኞች በሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ

በሰሜን አሜሪካዊቷ አገር ሄይቲ ቅዳሜ ዕለት ባጋጠመ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 1ሺህ 941 ሰዎች መሞታቸው መረጋገጡን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

የሟቾቹ ቁጥር ቀድሞ ከተገለጸው ከ500 በላይ ጨምሯል።

በ7.2 ማግኒትዩድ በተለካው በዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ጉዳት ያጋጠማቸው ሲሆን በርካቶችም የደረሱበት አልታወቀም።

በካረቢያኗ አገር ሄይቲ በዚህ ሳምንት የጣለው ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ለነፍስ አድን ሥራውም እንቅፋት ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው 500 ሺህ የሚሆኑ ሕጻናት መጠለያ፣ ንጹህ ውሃ እና ምግብ የማግኘት እድል የላቸውም አሊያም ደግሞ ውስን ነው።

በአገሪቷ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት -ዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ብሩኖ ሜስ " በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ ሁሉንም ነገራቸውን ያጡ በርካታ የሄይቲ ቤተሰቦች አሁን እየኖሩ ያሉት ጎርፍ ላይ ነው" ብለዋል።

በአደጋው ቤት አልባ የሆኑ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም የሚወርድባቸው ዶፍ መቋቋም ወይም ደግሞ በአደጋው ወደ ፈራረሰው አሊያም ለመፍረስ ቋፍ ላይ ወዳለ ሕንጻ መመለስ ይኖርባቸዋል።

ደቡብ ምዕራብ ሄይቲ በተለይ በሌስ ካይስ ከተማ በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል።

የከተማዋ ነዋሪ ማጋሌ ሳዴት "ማክሰኞ ምሽት በቤተክርስቲያን መጠለያ አግኝቼ ነበር፤ ነገር ግን መሬቱ እንደገና ሲንቀጠቀጥ በሰማሁ ጊዜ በሩጫ ወጥቻለሁ" ስትል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግራለች።

እርሷ እንዳለችው ሰዎች ራሳቸውን ጎዳና ላይ ከመውደቅ እፎይታ ሊያገኙ የሚችሉበት መዋቅሮችም ጥቂት ናቸው።

አንዳንድ ሆስፒታሎች በመጨናነቃቸውና የጤና ቁሳቁስ አቅርቦት ባለመኖሩ ሐኪሞች የተጎዱትን ለማከም ፈተና ሆኖባቸዋል።

ባለፈው ወር የፕሬዚደንቱን ግድያ ተከትሎ ከፖለቲካ ቀውስ ያልወጣችው ሄይቲ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል።

ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አሬል ሄንሪ ለአንድ ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ ያወጁ ሲሆን ሕዝቡም እንዲተባበር አሳስበዋል።

ሄይቲ ባለፉት ዓመታት እአአ በ2016 ያጋጠማትን 'ሃሪኬን ማቴው'ን ጨምሮ በተከታታይ በተፈጥሮ አደጋዎች ተመትታለች።

እአአ በ2010 ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ ግን በርካታ ሰዎች የሞቱበት አደጋ ነው። በአደጋው ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ በአገሪቷ መሠረተ ልማት እና ምጣኔ ሐብት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት አስከትሏል።