በቤንሻንል ጉሙዝ ወደ 540 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች እንዳሉ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ካርታ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ወደ 540 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ሲኖሩ በደቡብ ክልል ደግሞ ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አስታውቋል።

ኦቻ በሳምንታዊው ሪፖርቱ እንዳሰፈረው በክልሉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት ተፈናቃዮች ወስጥ 384 ሺህ 490 (71 በመቶ) የሚሆኑት 270,684 በመተከል ፣ 95,989 በካማሺ፣ 17,817በአሶሳ ዞኖች ውስጥ እንደሚገኙ አስፍሯል።

ቀሪዎቹ 148,000 ስደተኞች ደግሞ 77,543ዎቹ በአዊ እና 69,469ዎቺ በወለጋ ዞኖች ተፈናቅለዋል እንደሚኖሩ ተመልክቷል።

በክልሉ ውስጥ በሚገኘው ታጣቂና በክልሉ መንግሥት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በአማራ ክለል አዊ ዞን የነበሩ 50 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮችንም ወደ መተከል ዞን ማስፈር እንደታቸለም ተገልጿል።

በተለይም በክልሉ መተከል ዞን በታጣቂዎች የሚደርሰው ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ወደ ካማሺና አሶሳም ተዛምቶ በርካቶችን ወደ አጎራባች ክልሎች እንዲፈናቀሉ አስገድዷል ብሏል።

እነዚህ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የበርካቶችን ህይወት ከመቅጠፍ በተጨማሪ ቤቶችና የንብረት ውድመቶችን አስከትሏል።

ከኦቻ በተገኘው መረጃ መሰረት በመተከል ዞን አምስት ግጭት በተከሰተባቸው ወረዳዎች ቢያንስ 12,000 ቤቶች ወድመዋል ፣ 90 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በከፊል ተጎድተዋል እንዲሁም 41 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተጎድተዋል።

በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች እና በጉሙዝ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አልፎ አልፎ ውጊያው እንዳለ በሚነገርባት ካማሺ ዞን ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሁንም ውጥረት ውስጥ እንደሆነም ድርጅቱ አስታውቋል።

በካማሺ ዞን ታጣቂዎች በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የገጠር ቀበሌዎችን በቁጥጥር ስር እያዋሉ ሲሆን ፣ በቅርቡም ሚዚጋ (ሶጋ) ከተማን መቆጣጠራቸውን መግለጫው አመልክቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለው አለመረጋጋት የሰብዓዊ ተደራሽነቱን በእጅጉ ገድቦታል ብሏል።

በክልሉ ወስጥ በካማሺ፣ መተከል እንዲሁም በአሶሳ ዞን በምትገኘው ኦዳቢልዲጊሉ ወረዳ የእንቅስቃሴ ገደብ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑንም አሳስቧል።

በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰዎች ከሞትና ለመፈናቀል ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከእነዚህም መካከል ለረጅም ጊዜ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት የቆየው የመተከል ዞን በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ ይህንንም ለመቆጣጠር በሚል የክልሉና የፌደራል መንግሥት የጸጥታ አካላት በጥምረት የሚመሩት የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) በዞኑ ውስጥ ከተቋቋመ ወራት ተቆጥረዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በክልሉ የተለያዩ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ሲሆን ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለማምጣትም እየተሞከረ ነው።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥትና ታጣቂው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ከወራት በፊት የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙ ሲሆን በክልሉ በተደጋጋሚ በንፁሃን ላይ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ለመቀነስ ያለመና የሚከሰተውንም የፀጥታ ችግር በዘላቂነት መፍትሔ ለማምጣት መሆኑንም የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊን አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር ለቢቢሲ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ በተጨማሪ ድርጅቱ በደቡብ ክልል ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ሁኔታ ገምግሞ በክልሉ ወደ 1.4 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጿል።

በክልሉ በተደጋጋሚ በተከሰተው ግጭት፣ ድርቅ፣ እሳት፣ ጎርፍ፣ ወረርሽኝ እና የሰብል ተባዮች ምክንያት በቅርብ አመታት ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ቁጥር ከፍ አድርጎታል ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ መንግሥት፣ የአገር ውስጥና አለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እየተሞከረ እንደሆነም ሪፖርቱ አመላክቷል።

በተለይም በኮንሶ ዞን እና በአካካቢው በሚገኙ ልዩ ወረዳዎች በጥቅምት ወር ላይ በተነሳው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች የትኩረት ማእከል ሆነዋል ተብሏል።

ከነዚህ አካባቢዎች በተጨማሪ ኦቻ በዚሁ ሪፖርቱ በምዕራብና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች እንዲሁ 51 ሺህ ተፈናቃዮች እንዳሉ ተመድ ያመላከተ ሲሆን አዳዲስ መናቀሎችም እየተመዘገቡ ነው ተብሏል።

በወለጋ ዞኖች ውስጥ በቀጠለው የታጣቂዎችና የፀጥታ ኃይሎች ግጭት ያለው የፀጥታ ሁኔታ ያልተረጋጋ እና አካባቢዎቹንም ለእርዳታ ተደራሽ እንዳይሆኑ አድርጎታል ብሏል።