ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ግብዣ ቱርክ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 12/2013 ለጉብኝት ቱርክ መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በቱርክ የሚኖራቸው ቆይታ ከፕሬዝደንት ኤርዶጋን ጋር ተገናኝተው በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ጉዳዮች እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ቱርክ የሚጓዙት በአገሪቱ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ግብዣ መሆኑን የቱርክ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬትን ጠቅሶ አናዱሉ የዜና ወኪል መዘገቡ ይታወሳል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ታደርጋለች በማለት ወዳጅነታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ፕሬዝደንቱ ይህን ማለታቸው የተሰማው ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት እንደነበር ተገልጾ ነበር።

ሁለቱ መሪዎች ሐምሌ 25/2013 ዓ.ም በስልክ በተወያዩበት ወቅት ቱርክ ለኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ ፕሬዝደንት ኤዶጋን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በቱርክ ለምን ያህል ቀናት እንደሚቆዩ የተባለ ነገር ባይኖርም፤ ጉብኝቱ የኢትዮጵያ እና የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ከተጀመረበት 125ኛ ዓመት ጋር መገናኘቱ ልዩ ያደርገዋል ሲል የቱርክ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በጉብኘቱ ወቅት ሁለቱ አገራት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይገመግማሉ እንዲሁም ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ይመክራሉ ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በድንበር ይገባኛል እና በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ የምትገኘው የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ከቀናት በፊት ወደ ቱርክ ተጉዘው ነበር።

ሱዳን ጄነራሉ ወደ ቱርክ የተጓዙት የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግነኙነት ለማጠናከር ነው ብላለች።

ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን በፕሬዝደንት ኤርዶጋን ግብዣ የሁለት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው ባለፈው ዓርብ ወደ ካርቱም ከመመለሳቸው በፊት በቱርክ እና በሱዳን መካከል በርካታ ስምምነቶች እና የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርመዋል።

የኃይል አቅርቦት፣ መከላከያ፣ ፋይናንስ እና መገናኛ ብዙኃን በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አናዱሉ ዘግቦ ነበር።

ቱርክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካደረጉ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን የጨርቃ ጨርቅ እና የኤሌክትሪክ ማስተላላፊያ ገመዶች ማምረቻዎችን ጨምሮ የቱርክ ኩባንያዎች 2.5 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ፈሰስ ማድረጋቸውን ከዚህ ቀደም የቱርኩ ዜና ወኪል አናዱሉ ዘግቧል።

ቱርክ በመካከለኛው ምሥራቅ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ነች።

በሌላ በኩል የአሜሪካ ፕሬዝደንት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በቀጠናው የሚያደርጉት ጉብኝት እንደቀጠለ ሲሆን በቅርቡ ኢትዮጵያ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ጄፈሪ ፌልትማን በፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጥያቄ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ግጭት በተመለከተ ለመነጋገር ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ሮይተርስ የዜና ወኪል ከቀናት በፊት ዘግቦ ነበር።

ፌልትማን ከነሐሴ 9 እስከ 18 ወደ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እንደሚጓዙ እና ከየአገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚገናኙ የአሜሪካ መንግሥት ከቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።