የታሊባን ከፍተኛ አመራሮች በስደት ከቆዩባት ኳታር ወደ አፍጋኒስታን መመለስ ጀመሩ

የታሊባን ፖለቲካ ኃላፊ ሙላህ ባራዳር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የታሊባን ፖለቲካ ኃላፊ ሙላህ ባራዳር

የታሊባን ቡድን ከፍተኛ አመራሮች በስደት ከቆዩባት ኳታር ወደ አፍጋኒስታን መመለስ ጀመሩ።

የታሊባን ፖለቲካ ኃላፊ ሙላህ ባራዳር ከሌሎች የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአፍጋኒስታኗ ካንዳራህ ግዛት ደርሰዋል።

ይህች ግዛት ታሊባን ከ20 ዓመታት በፊት በአሜሪካ መንግሥት ከስልጣን ከመወገዱ በፊት የቡድኑ ጠንካራ ይዞታ ነበረች።

ሙላህ ባራዳር ከታሊባን መስራቾች መካከል አንዱ ሲሆኑ በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው ግለሰብ ናቸው።

ሙላህ ባራዳር አፍጋኒስታን ሲደርሱ በርካታ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ በደስታ ተቀብሏቸዋል።

የፖለቲካ ኃላፊው መኪና ውስጥ ሆነው ከካንዳራ አየር ማረፊያ ሲወጡ በርካቶች ሰላምታ እና ድጋፍ ሲሰጧቸው የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወጥተዋል።

በርካታ የታሊባን አመራሮች መቀመጫቸውን ኳታር አድርገው ሰንብተዋል። አመራሮቹ በኳታር ዶሃ ተቀምጠው ነበር ከአሜሪካ ጋር የምዕራባውያኑ ጦር ከአፍጋኒስታን እንዲወጣ ሲደራደሩ የቆዩት።

የታሊባን ጋዜጣዊ መግለጫ

የታሊባን አመራሮች ወደ አፍጋኒስታን መመለስ ከጀመሩ በኋላ ታሊባን የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ ትናንት ሰጥቷል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢኑላህ ሙጃሂድ ቡድኑ መንግሥት ለመመስረት እየሰራ መሆኑን እና መንግሥት እንደተመሠረተ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ታሊባን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ "ሴቶች በማሕበረሰባችን ውስጥ ተሳትፎ ይኖራቸዋል"፤ "በሸሪዓ ሕግ መሠረት" እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል በማለት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢኑላህ ሙጃሂድ

ለምዕራባውያኑ አገራት በአስተርጓሚነት ሲሰሩ የነበሩ አፍጋናዊያን በታሊባን የበቀል እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ነበር። ይሁን እንጂ የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢኑላህ ሙጃሂድ ታሊባን "ማንም ሰው ላይ የበቀል እርምጃ አይወሰድም" ካሉ በኋላ ለአፍጋኒስታን መረጋጋት ሲባል "ታሊባን ለሁሉም ሰው ምህረት አድርጓል" ብለዋል በትናንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ።

መገናኛ ብዙሃንም በነጻነት እንዲሰሩ ታሊባን እንደሚፈቅድም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገራት ዜጎቻቸውን እና ሠራተኞቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ጥረት ማድረጋቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።

ዩኬ 2ሺህ የአፍጋን ዜጎችን ልትቀበል ነው

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በቀጣይ ዓመታት ከ20ሺህ በላይ አፍጋኒስታውያንን እንደሚቀበል አስታውቋል።

በመጀመሪያ ዓመት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስተርጓሚ ሆነው እና ሌሎች ስራዎችን ሲሰሩ የነበሩ 5ሺህ ሰዎችን ጨምሮ 10ሺህ ሰዎች ወደ ዩኬ ይዘዋወራሉ ተብሏል።

ሴቶች፣ ሕጻናት እና በተለያዩ ምክንያቶች በታሊባን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ሰዎች ይለያሉ ብሏል የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት።

አሜሪካ ከ1ሺህ ባላይ ዜጎችን ስለማስወጣቷ

አሜሪካ ትናንት ማክሰኞ ከ1ሺህ100 አሜሪካውያኖችን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷን የዋይት ሃውስ ኃላፊ ተናግረዋል።

ይህም እስካሁን ከአፍጋኒስታን የወጡ አሜሪካውያን አሃዝ ወደ 3200 ያደርሰዋል።

ከአሜሪካውያኑ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ 2ሺህ የአፍጋኒስታን ዜጎች ወደ አሜሪካ ተወስደዋል።

አሜሪካ በአውሮፕላን ጎማ ስር የሰው አካል መገኘቱን ማስታወቋ

አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ከተነሱ የጦር አውሮፕላኖቿ መካከል በአንደኛው ጎማ ስር የሰው አካል መገኘቱን ተከትሎ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብላለች።

ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ በርካቶች አፍጋኒስታንን ለቀው ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ትናንት እና ከትናንት በስቲያ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በመዲናዋ የሚገኘውን አየር ማረፊያ አጨናንቀው ታይተዋል።

በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቁ ምሥሎች ሰዎች አውሮፕላን ውስጥ ለመግባት ሲገፋፉ፣ እየተንቀሳቀሰ ካለ አውሮፕላን ሥር ሲሯሯጡ እና አውሮፕላን ላይ ሲንጠላጠሉ አሳይተዋል።

በዚህም ከ8 ያላነሱ የአፍጋን ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉ በስፋት ተዘግቧል። ከእነዚህም መካከል በአውሮፕላን ተገጭተው እንዲሁም አውሮፕላን ላይ ተንጠልጥለው አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ወድቀው ሕይወታቸው ያለፉ ስለመኖራቸው ተገልጿል።

የአሜሪካ አየር ኃይል ባወጣው መግለጫ ሲ-17 የጦር አውሮፕላኑ በካቡል አየር ማረፊያ የደህንነት ሁኔታው አስገቢ በሆነበት ወቅት በመቶዎች በሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ከተከበበ በኋላ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ለመነሳት መወሰናቸውን ገልጿል።

አውሮፕላኑ ኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ካምፕ እንዲያረፍ መደረጉን አስታውቋል።