አፍጋኒስታን፡ የማይታወቀው የታሊባን ቃል አቀባይ ፊት መታየቱ መነጋገሪያ ሆነ

ቃል አቀባዩ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ቃል አቀባዩ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ

ማክሰኞ ዕለት ታሊባኖች አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠሩ በኋላ የመጀመሪያውን መግለጫ ሲሰጡ ቃል አቀባዩ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ አብዛኛውን ንግግር አድርጓል።

በታሪካዊው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ከጋዜጠኞች ብዙ ጥያቄዎችም ቀርበዋል። በእነዚህ ወቅት ሙጃሂድ "በእስልምና ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ" የሴቶች መብት ይከበራል ብሏል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን ለሚመለከቱት አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ሌላው ትልቅ ጉዳይ የነበረው የቃል አቀባዩን ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ማየታቸው ነው።

ቃል አቀባዩ ለዓመታት በድብቅ ሲሠራ ቆይቷል። መልዕክቱን የሚያስተላልፈው በስልክ ብቻ ነበር።

የቢቢሲዋ ዬልዳ ሃኪም ከአሥር ዓመት በላይ ያነጋገረችውን ሰው ፊት በማየቷ 'በጣም ደንግጣ' ነበር።

ቃል አቀባዩ ለሌላ ጋዜጠኛ "ማንኛውንም የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶችን አንፈልግም" ሲል እርቅ እንደሚፈልጉ ገልጿል።

ሃኪም ግን ይህ ከእርሱ ትቀበለው ከነበረው አንዳንድ መልዕክቶች በጣም የራቀ ነው ትላለች።

"ከእነዚህ መልዕክቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ጠንካራ እስላማዊ ጽሑፎች ናቸው። አንዳንዶቻችሁ 'ይህ ሰው ለአሜሪካውያን ደም አፍሳሽ ነው። በአፍጋኒስታን መንግሥት ውስጥ ላለ ለማንም ሰውም ደም አፍሳሽ ነው። ዛሬ ደግሞ የበቀል እርምጃ አይኖርም ይላል" ብላለች።

ሃኪም "ለዓመታት ደም አፋሳሽ መግለጫዎች ሲልክ ቆይቶ አሁን በድንገት ሰላም ወዳድ ሊሆን ነው? ይህን ማስታረቅ ከባድ ነው" ስትል አክላለች።

ቃል አቀባዩ ሙጃሂድ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በታሊባን ታጣቂዎች የተገደለው የአፍጋኒስታን የሚዲያ እና የመረጃ ማዕከል ዳይሬክተር ዳዋ ካን ሜናፓል መቀመጫ በሆነው ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር።

በወቅቱ ሙጃሂድ ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን ሜናፓል "በልዩ ጥቃት ተገድሏል" ብለዋል።

ሙጃሂድን በማየታቸው ብዙ ጋዜጠኞች በትዊተር ላይ ሃሳባቸው አስፍረዋል።

ለዓመታት ፊት አልባው ቃል አቀባይ ከአንድ ሰው በላይ ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም ነበር።

የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ዋና ዘጋቢ ሊሴ ዱሴት እነዚህ ውይይቶች ከማኅበራዊ ድር አምባዎች በፊት ጋዜጠኞች በመደበኛ ስልክ ሲደውሉለት የነበሩ ናቸው ብላለች።

አንዳንዶች ማክሰኞ ዕለት ከካሜራዎቹ ፊት የተቀመጠውና ለዓመታት ጥያቄዎችን ሲመልስ የነበረው ሰው በጣም ወጣት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

"ለዓመታት የተፈበረከ ስም እንደሆነ እና በየተራ የሚሠሩ "ዛቢሁላህ" የሚባሉ ሰዎች እንዳሉ ግምቶች አሉ። አሁን ሁላችንም ይህን ዘቢሁላህ ሙጃሂድ እንደሆነ እየተቀበልን ነው። ምናልባት እሱ ላይሆን ይችላል?" ብላለች ዱሴት።

ሃኪም በበኩሏ ሁሉንም ምስጢር ማድረግ የታሊባን የጨዋታ አካል ነው ትላለች።

"ታሊባኖች እንደዚህ ናቸው። የተደራጁ እና ርዕዮተ-ዓለም ያላቸው ናቸው። በአጋጣሚ ምንም አይደረግም። በአንድ ሰው ላይ ምስጢር ለመፍጠር በድንገት ታየ። ስክሪፕቱን ከዚህ በተሻለ መጻፍ አይቻልም" ትላለች።

ሙጃሂድ አንድ ሰው ሆነ አልሆነ ማክሰኞ ዕለት የተሰላ ንግግር ለማድረግ በመሞከሩ ቃላቶቹ እንዳስፈራት ሃኪም ተናገራለች።

"ማስጠንቀቂያው በእውነቱ የሸሪአ ሕግ ነበር። ይህ ቀዝቀዛ ውሃ አከርካሪዬን ወደ ታች እንዲወርድ አደረገ። እነሱ አሁንም ምን እንደሚመስል አላስቀመጡም"

"ይህ የታሊባኖች ባህሪ ነው። አታላዮች ናቸው፣ ማራኪ ናቸው፣ ትክክለኛውን ቋንቋ እንዴት እንደሚጠቀሙ ቢያውቁም ለማመን ወይም ላለማመን በጭራሽ እርግጠኛ መሆን አይቻልም" ትላለች።

"ብዙ ምስጢር አለ ... ግን እነማን እንደሆኑ በእርግጠኝነት እናውቃለን?"