የሸሪዓ ሕግ ምንድን ነው? በሸሪዓስ ወንጀል የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?

ሸሪዓ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሸሪዓ ኢስላማዊ የፍትሕ ሥርዓት ነው። የሚቀዳውም ከቁርዓን ነው።

ቅዱስ ቁርዓን የኢስላም መንፈሳዊ መመሪያ ነው።

ሸሪዓ ከቅዱስ ቁርዓን የሚመዘዝ ይሁን እንጂ አተረጓጎሙ ላይ ግን ታላላቅ የኢስላም ሊቃውንት ይሳተፉበታል። ይህም 'ፈትዋ' ወይም ብያኔ ተብሎ ይጠራል።

በአንድ ጉዳይ ላይ 'ፈትዋ' ተሰጠ ሲባል በታላላቅ የሃይማኖቱ ሊቃውንት በጉዳዩ ፍሬ ነገር ላይ የአተረጓጎም ትርጓሜ ሰጡ እንደማለት ነው።

ሸሪዓ ጥሬ ትርጉሙ 'ንጹህ፣ በተቀደደለት ቦይ የሚፈስ ውሃ' እንደማለት ነው።

ይህም ሸሪዓ ለአንድ አማኝ 'ንጹሕና ቀጥተኛ የሕይወት መመሪያ' እንደማለት ነው ብለው ይተረጉሙታል።

ሸሪዓ ለሙስሊሞች የሕይወት መመሪያ ሕግጋትን የያዘ የሕግ ማዕቀፍ ነው ሲባል አማኞች ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ እንደ ሁኔታው ፖለቲካዊ ሕይወታቸውም በዚህ መንፈሳዊ ሕግ እንዲቃኝ ይሆናል ማለት ነው።

በሌላ አነጋገር ሁሉም ሙስሊሞች በሸሪዓ ሥርዓተ-ሕግ ጥላ ሥር እንዲኖሩ ይጠበቃል።

ጾም-ጸሎት ብቻም ሳይሆን ነዳያንን መመጽወት እና ሌሎች ማኅበራዊ መስተጋብሮቻቸው ሁሉ በዚሁ የመንፈሳዊ ፍትሕ ሥርዓት ሊቃኙ ይገባል።

ይህም ፈጣሪ (አላህ) የሰው ልጆች በምድር ላይ እስካሉ ድረስ እንዲከተሉት በቅዱስ ቁርዓን አማካኝነት የተሰጠ የሕይወት መመሪያ ገጸ በረከት እንደሆነ ተደርጎ በአማኞች ዘንድ ይወሰዳል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ሸሪዓ ሴትና ወንድ እንዴት መልበስ እንዳለባቸው በዝርዝር ይደነገጋል።

ለምሳሌ ሴትና ወንድ በሸሪዓ ሕግ እንዴት መልበስ እንዳለባቸው በዝርዝር ይደነገጋል።

ይሁንና አገራት አንድ የሸሪዓ ሕግን እየተከተሉም ቢሆን በአተረጓጎም ልዩነት ምክንያት መመሪያዎቻቸው ሊለያዩ ይችላሉ።

ሴቶች ሰውነትን የሚያጋልጡ ልብሶችን እንዳይለብሱ በሸሪዓ ይገደዳሉ። ሆኖም ይህ አገላለጽ ወጥ ትርጓሜ አለው ማለት አይደለም።

ይህን ተከትሎም የኒቃብ፣ የሒጃብ፣ የቡርቃ አለባበስ ልዩነቶች በተለያዩ ሸሪዓ ሕግን በሚከተሉ አገራትም የአተረጓጎም ልዩነቶች እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል።

ለምሳሌ በሸሪዓ ሕግ አልኮል መጠጦች ክልክል ናቸው።

መጠጦቹ ብቻም ሳይሆን አልኮል የሚሸጥባቸው ቦታዎች መገኘት፣ በአልኮል ፋብሪካዎች መሥራት፣ የአልኮል መጠጦችን ማከፋፈል፣ ማስተዋወቅ በማንኛውም የአልኮል ምርት ቅብብሎች የንግድ መስመር ተሳትፎ ማድረግ ሸሪዓ ክልክል ያደርጋል።

ይህ ጥቅል የሸሪዓ መመሪያ ነው።

ሆኖም አንድ ሙስሊም በሥራ አጋጣሚ ወይም በሌላ ሁኔታ አንድ ሰው አልኮል መሸጫ ቤት ወይም መቆመሪያ ቤት ውስጥ እንዲገኝ የሚያስገድደው ሁኔታ ቢፈጠር ምን ማድረግ እንዳለበት ለመጠየቅ ኢስላማዊ ሊቃውንትን ሊያማክር ይችላል።

ይህ ሁኔታ በሸሪዓ አተረጓጎም ዙርያ አገራት የተለያዩ እንዲሆኑ አንድ ምክንያት ሆኗል።

በሸሪዓ ውስጥ ወደ ኢስላማዊ ሊቃውንት ከሚያስኬዱ ጉዳዮች ሌሎቹ የቤተሰብ ሕግ፣ የፋይናንስ ሕግ እና ንግድ ሊሆኑ ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

በሸሪዓ ሕግ እንዲተገበሩ ከሚፈቀዱት ቅጦች መካከል ጥፋተኛውን በአደባባይ መግረፍ አንዱ ነው

በሸሪዓ ሕግ ከባድ የሚባሉት ቅጣቶች የትኞቹ ናቸው?

የሸሪዓ ሕግ ወንጀሎችን በጥቅሉ በሁለት ይከፍላቸዋል። ሐድና ታዚር ይባላሉ።

ሐድ ወንጀሎች ለትርጉም እምብዛምም ክፍት ያልሆኑ ደረቅ ወንጀሎች ሲሆኑ ታዚር የሚባሉት ደግሞ ቅጣቶቹ ጉዳዩን ለሚያዩት ዳኛ ሕሊና የሚተው ናቸው።

ለምሳሌ በሐድ ወንጀሎች ውስጥ የሚካተቱት ስርቆት፣ ዝሙት እና የሰው ነፍስ ማጥፋት ናቸው።

ስርቆት በሸሪዓ ሕግ ዝርዝር ሁኔታው ቢለያይም አጥፊውን ግራ ወይም ቀኝ እጅን በመቁረጥ ቅጣቱ ሊፈጸም ይችላል።

ዝሙት የፈጸመ ሰው ደግሞ ዝርዝር ሁኔታው ቢለያይም ከፍተኛው ቅጣት በድንጋይ ተወግሮ መገደል ነው።

አንዳንድ የኢስላማዊ ተቋማትና ጥናቶች ግን እነዚህ ከፍተኛ ቅጣቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ በርካታ ሂደቶች ያሉትና ጥፈቱ ከቅንጣት ጥርጣሬ ባለፈ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ መረጋገጥ ይኖርበታል ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የሰው ልጆችን በድንጋይ ወግሮ መግደልን በጽኑ ይነቅፋል።

ሸሪዓን የሚከተሉ አገራትም ቢሆኑ ይህን የሐድ ወንጀሎች ቅጣቶችን ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ ልዩነትን ያሳያሉ።

የሕዝብ ሐሳብ መመዘኛዎች የሚያሳዩትም ሙስሊሞች ሳይቀር በነዚህ ቅጣቶች ተፈጻሚነት ላይ በአመለካከት ልዩነት እንዳላቸው ነው።

በአውሮጳ ዕውቅ የኢስላም ጉዳዮች ተመራማሪ ጣሪቅ ረመዳን በነዚህ ከባድ ቅጣቶች ዙርያ የሙስሊሙ ዓለም ተፈጻሚ እንዳያደርጋቸው ጥሪ አቅርቧል።

እሱ እንደሚከራከረው ዝሙተኛውን በድንጋይ ወግሮ መግደልና ሌቦችን እጅ መቁረጥ አሁን ባለው ዓለም ባሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ መንፈሳዊ ነጥቦችን ብዙ ናቸው።

ሃይማኖት መቀየር ያስገድላል?

በሸሪዓ ከባባድ ወንጀሎች መካከል አንዱ ከኢስላም ሃይማኖት መውጣት (ኩፍር) ነው።

በሙስሊሙ ዓለም ይህ ጉዳይ እጅግ አከራካሪ ከሚባሉት የሸሪዓ ሕግጋት ይመደባል።

ይሁንና በርካታ የሚባሉ የኢስላም ሊቃውንት አንድ ሙስሊም ከሃይማኖቱ ካፈነገጠ በሞት መቀጣት እንዳለበት ያምናሉ።

ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ በተቃራኒው ይከራከራሉ።

እነዚህ ሊቃውንት የሚሉት ደግሞ ሃይማኖቱን የቀየረ አማኝ ቅጣቱን ማግኘት ካለበት ከፈጣሪ እንጂ ከምድራዊ ኃይል መሆን የለበትም።

ቁጥራቸው ብዙ አይሁን እንጂ ይህ የሞት ቅጣት ሃይማኖቱን በተወ ምዕመን ላይ ተፈጻሚ መሆን የለበትም የሚሉ ሊቃውን ሌላም የሚያነሱት ጠንካራ ነጥብ አላቸው።

እንደ ማስረጃ የቁርዓንን አንድ ቃል ይመዛሉ። እንዲህ ይላል፤ 'ሰዎችን በሚከተሉት ሃይማኖት ማስገደድ የለም' (ቀጥተኛ ያልሆነ ትርጉም)።

እንደ ማንኛውም የሕግ ማዕቀፍ ሁሉ የሸሪዓ ሕግም እጅግ ውስብስብ መልክ አለው።

ተፈጻሚነቱና አተረጓጎሙም በአመዛኙ በተርጓሚዎቹ የመንፈሳዊ ትምህርት ጥራትና ደረጃ የሚወሰን ነው።

ኢስላማዊ የሕግና ፍትሕ ሊቃውንት በየጊዜው መመሪያና ደንቦችን ያወጣሉ። ይህ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚሰጥ የመጨረሻ የሊቃውንት ትርጉም ውሳኔ 'ፈትዋ' በመባል ይታወቃል።

ሸሪዓ አምስት ዓይነት የሕግ ፍልስፍናዎች አሉት። በሱኒ ኢስላም ደግሞ አራት ዋና ዋና ትልልቅ አስተምህሮዎች ይገኛሉ።

እነዚህም ሐንባሊይ፣ መሊኪይ፣ ሻፊኢይ፣ እና ሐናፊይ ናቸው። በሺዓ ኢስላም አስተምህሮ ደግሞ ጃእፋሪይ የሚባል አለ።

እነዚህ መጠነ ሰፊ አምስት የሃይማኖቱ የሕግ ፍልስፍናዎች የቅዱስ ቁርዓንን ብሎም ከመጽሐፉ የሚመነጨውን የሸሪዓ ሕግን በመተንተን፣ በመተርጎም፣ እንዲሁም ተፈጻሚ በማድረግ ላይ ሰፊም ጠባብም የሆኑ ልዩነቶችን ያሳያሉ።

ለዚህም ነው ሁለት የሸሪዓ ሕግን ተግባራዊ ባደረጉ አገራት ለአንድ ወንጀል የተለያዩ ቅጣቶች ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉት።

ከሰሞኑ ካቡልን የተቆጣጠሩት የታሊባን ኃይሎች አፍጋኒሰታንን በሸሪዓ ሕግ እናስተዳድራታለን፣ ሴቶችም በሸሪዓ ሕግ መሠረት ይሰራሉ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው የሚለው ጥያቄ በዓለም ሚዲያዎች ጎልቶ የወጣውም ለዚሁ ነው።