የታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠር ለአፍሪካ 'ጂሃዲስቶች' አንድምታው ምንድን ነው?

የታሊባን ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

አፍጋኒስታን በታሊባን ቁጥጥር ስር መውደቋን ተከትሎ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ደስታቸውን እየገለፁ ነው።

ከሶማሊያ አልሸባብ ጋር የተገናኘ አንድ የመገናኛ ብዙኃን "ፈጣሪ ታላቅ ነው" በማለት ጽፏል።

የአልቃይዳ ተባባሪ የሆነው ጀመዓቱ ኑስራት አል-ኢስላም ወል ሙስሊሚን (ጄኤንኤም) መሪ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን መልዕክቱን ታሊባንን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ከጠፋበት ብቅ ብሏል።

የጂኤንኤም መሪ ኢያድ አግ ጋሊ "እኛ እያሸነፍን ነው" ያለውም አፍጋኒስታን ውስጥ የውጭ አገራት ለቀው መውጣታቸውና ፈረንሣይ በምዕራብ አፍሪካ ሳህል ቀጠና ውስጥ ያለውን ወታደራዊ ኃይሏን ለመቀነስ ያደረገችውን ውሳኔን በማነጻጸር ነው።

ይህንን በአፍጋኒስታን የተከሰተውን ሁኔታ እያነጻጸሩ ያሉትም የአፍሪካ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ብቻ አይደሉም።

ከአፍሪካ ቀንዷ አገር ሶማሊያ እስከ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ ያሉ ጋዜጦች ታሊባንን በተመለከተ በርካታ ጽሁፎችን አትመዋል። ዜጎችም ስጋታቸውን በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እያጋሩ ነው።

ታሊባን የአፍጋኒስታንን መቆጣጠር ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር በሚያደርጉት ውጊያ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ኃይሎች ለሚተመማኑ የአፍሪካ መንግሥታት ከፍተኛ የማንቂያ ደወል ነው።

በሶማሊያ የመጨረሻዋ ሰዓት እየተቃረበች ይመስላል

በአፍጋኒስታን ውስጥ ያለውን ጠንካራ ንጽጽር በመመልከት በሶማሊያ ውስጥም ከፍተኛ ስጋት አለ።

በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ አጋማሽ የአልቃይዳ ተባባሪው የአልሸባብ ቡድን አመፅ ከመጀመሩ በፊት ሶማሊያ በመንግሥት መፈራረስ እና ለአስርት ዓመታት በቆየ የእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ ነበር።

በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የሚደገፈው መንግሥት የአገሪቱን አብዛኛውን ክፍል እንደገና ለመቆጣጠር ሲታገል የቆየ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስልጣን ስር በሚንቀሳቀሱ የአፍሪካ ሕብረት ወታደሮች ላይም ጥገኛ ነው።

የፎቶው ባለመብት, SOMALI ARMY / HANDOUT

የምስሉ መግለጫ,

የሶማሊያ ጦር

ዋነኛው ግብ የነበረውም ታጣቂዎችን በማስወገድ የማዕከላዊውን መንግሥት ተቋማት ለመገንባት ጊዜ መስጠት ነው።

ነገር ግን እንደ አፍጋኒስታን ሁሉ በሶማሊያም ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቷል የሚል ክስ ቀርቧል።

በዚህ ዓመት በዋና ከተማዋ ምርጫው ዘግይቷል በሚል የፀጥታ ኃይሎች እርስ በእርስ ሲጋጩም ታይቷል።

እነዚህ ጉዳዮች በሶማሊያ የመንግሥት ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ጥርጣሬን አስከትለዋል።

በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ የፖለቲካ አማካሪ የሆኑት ኢልሃም ጋሳር ዓለም አቀፍ አጋሮች አልሸባብን በማጥፋት ላይ እንጂ ጠንካራ የሶማሊያ መንግሥት በመገንባት ላይ አላተኮሩም ይላሉ።

"ትኩረቱ መካከለኛውን የሶማሌያውያን ኑሮ የተሻለ ለማድረግ እና ዘላቂነት ያለው ሥርዓትን ለመፍጠር በጭራሽ አልነበረም" በማለትም ያስረዳሉ።

የሶማሊያ መንግሥት በዚህ ዓመት መጨረሻ በፀጥታ ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም እንዲሆን ቢታሰብም፤ ነገር ግን በሠራዊቱ አቅም ላይ በተነሱ ጥያቄዎች ምክንያት ይህ የሚሆን አይመስልም።

የሶማሊያ የደኅንነት ተቋም ሂራአል ኢንስቲትዩት ኃላፊ የሆኑት ሳሚራ ጋይድ "የሶማሊያ ኃይሎች ከአፍጋኒስታን በባሰ ሁኔታ ታጣቂዎችን ለመመከት ዝግጁ አይደሉም" ብለዋል።

"የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይሎች ካገኙት ድጋፍ 0.005 በመቶ ያህሉን እንኳን አላገኙም" ይላሉ።

አክለውም "ለሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችን መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ተጨባጭ ድጋፍ አናሳ ነው። ሶማሊያ አሁንም በመሣሪያ ማዕቀብ ውስጥ ናት፣ ስለዚህ አፍጋኒስታን የነበራትን ዓይነት የጦር መሣሪያ መግዛት አልቻልንም" በማለትም ያስረዳሉ።

ነገር ግን በሶማሊያ አሁን ባለው ሁኔታ የውጭ ዕርዳታ እንዴት እና መቼ ነው የሚቆመው ወደሚለው ትኩረት ተሸጋግሯል።

የአውሮፓ ሕብረት ቀድሞውኑ የገንዘብ ድጋፉን የቀነሰ ሲሆን መንግሥስት ራሱን ለመቻል በሚደረገው ዝግጅት በቂ ጊዜ ያለው አይመስልም።

በማሊ የነገሰው ፍርሃት

ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ ከአፍሪካ ታላላቅ አገራት አንዷ የሆነችው ማሊ በሰሜናዊ እና በማዕከላዊ ግዛቶቿ ከተለያዩ የጂሃዲስት ቡድኖች ጋር ስትፋለም ቆይታለች።

ታጣቂዎቹ የተለያዩ ግዛቶችን እንዳይቆጣጠሩም ማሊ በፈረንሳይ እና በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መታገዝ ነበረባት።

ነገር ግን የቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ማሊን ማገዝ በማሊያውያን እንዲሁም በፈረንሳያውያን ዘንድ ድጋፍ አላገኘም።

በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር ፈረንሳይ የወታደሮቿን ቁጥር እንደምትቀንስ አስታውቃለች። በዚህም መሰረት በሚቀጥለው ዓመት ከ2 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ ብቻ ይሆናል ብላለች።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በደንብ ያልሠለጠኑ እና በቂ መሣሪያ የሌላቸው የማሊ ወታደሮች እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን ሊቋቋሙት አይችሉም የሚል ስጋት አለ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የማሊ ህፃናት

"ሁኔታው እንደ አፍጋኒስታን ተመሳሳይ ሊሆን ስለሚችል በርካታ ሰዎች ይሰጋሉ" በማለት የማሊው 'ሌ ፓይስ' ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ቡራኢማ ጉንዶ ይናገራል።

"የውጭ አገራት ወታደሮች በማሊ መቆየት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ነገ ከሄዱ ሁኔታው የበለጠ አደገኛ ይሆናል" በማለትም ያክላል።

በማሊ ውስጥ እንደ ሌሎች ህትመቶች ሁሉ 'ሌ ፓይስ' የአገሪቱ መሪዎች የጦር ኃይሏን ለማጠናከር የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የፖለቲካ መፍትዎች

ልክ እንደ አፍጋኒስታን በአፍሪካ ውስጥ የእስልምና እንቅስቃሴ ደካማ የመንግሥት ተቋማትን፣ እንደ ትምህርት እና የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶች አለመኖር እንዲሁም ከድህነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ መስፋፋት ችሏል።

እነዚህ ምክንያቶች በሞዛምቢክ ካቦ ዴልጋዶ ግዛት ውስጥ ታጣቂዎች እንዲመሰረቱ እና በምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ተዋጊዎችን ለመመልመል እና የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት እንደ መንገድ ይጠቀሙባቸው ነበር።

በአንዳንድ አጋጣሚዎች ታጣቂዎች ለማኅበረሰባቸው የተሻሉ አገልግሎቶች እና ፍትሕ ለመስጠት ጣልቃ ይገባሉ፤ ይህም ሁኔታ የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

አክራሪነትን ለማጥፋት ወታደራዊ እርምጃዎች አዋጭ እንዳልሆኑና ከታጣቂዎች ጋር የሚደረግ ድርድርን ጨምሮ የፖለቲካ መፍትሔዎችን የማምጣቱ ነገር በበርካቶች ዘንድ ገዥ ሃሳብ ነው።

ነገር ግን የደኅንነት ዘርፍ ባለሙያው ፉላን ናስሩላህ በምዕራብ አፍሪካ ካሉ እስላማዊ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ማዕከላዊ መንግሥትን ቢቆጣጠር በጣም አስደንጋጭ እንደሚሆን ይናገራሉ።

"አፍጋኒስታን ውስጥ በተከሰተው ሁኔታ መነጽር አፍሪካን ወይም ሌላ ማንኛውንም የጂሃዳዊ እስላማዊ ቡድን መታየት የለባቸውም። ሁኔታዎቹ በጥቂቱ ከመመሳሰል በስተቀር በጣም የተለያዩ ናቸው" ይላሉ።

"በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱት ቡድኖች እንደ ታሊባን የተቀናጀ ኃይል አይደሉም። እነሱ የተለያዩ ሚሊሻዎች ቅልቅልና ግቦቻቸው ሁልጊዜም ባይሆን አንዳንድ ጊዜ የሚጣጣሙ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስናየው ደግሞ በአይኤስ እና በአልቃይዳ መካከል ባለው ፉክክር ተባባሪዎቻቸው እርስ በእርስ ሲጣሉ ታይተዋል" በማለት ያስረዳሉ።

የምዕራብ አፍሪካ እስላማዊ ቡድኖች "መንግሥት ደካማ በሆነበት ስፍራዎች አሉ፣ ግን እነሱም ቢሆኑ ከደካማ መንግሥት የበለጠ ደካማ ናቸው" ሲሉ ናስሩላህ ይናገራሉ።

መወሰድ ያለባቸው ትምህርቶች

በአፍጋኒስታን የተከሰተው ሁኔታ በአፍሪካ ፖሊሲ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ለማወቅ ጊዜው ገና ነው።

ነገር ግን በአገራቱ ላሉ የውጭ ኃይሎች የተሻለ መውጫ ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይቱ ተጀምሯል።

የዓለም አቀፉ የቀውስ ቡድን አካል የሆነው 'ኮምፎርት ኢሮ' "ከአፍጋኒስታን አፋጣኝ ትምህርቶች" ሊወሰዱ ይገባል ይላል።

ባለሙያዋም ቢሆኑ "በሙስና የተዘፈቁና በውጭ ኃይሎች ድጋፍ ጥገኛች የሆኑ መንግሥታት በአገር ውስጥ ትንሽ ወይም ምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌላቸው መንግሥታት ዓለም አቀፍ ድጋፍ በሚቀንስበት ጊዜ የተጀመረውን ሥራ ማስቀጠል የማይችሉ ሰው ሰራሽ ግዛቶች ናቸው" ይላሉ።

አፍጋኒስታንን ለመሸሽ በሚሞክሩ ሰዎች አስደንጋጭ ትዕይንት ውስጥ "እንደ ሶማሊያ ባሉ አገራት ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳይፈጠር በዓለም አቀፍ አጋሮች በኩል ሌላ እሳቤ ይፈጠራል" ብለው ያምናሉ።

የውጭ ኃይሎች ከሶማሊያ መውጣት የበለጠ እንደሚዘገይ እና የመጨረሻ አወጣጣቸውም የታሰበ እንደሚሆን ይናገራሉ።