"ህወሓት በደቡብ ጎንደር ሆስፒታሎችን ሳይቀር ዘርፏል" የዞኑ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, AMHARA COMMUNICATION
ዘረፋና ውድመት ከተፈፈመባቸው ተቋማት አንዱ
በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የነበረው የህወሓት ኃይል መጠነ ሰፊ ዘረፋ፣ የመሠረተ ልማት ውድመትና ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ።
ቢቢሲ ያናገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዳሉት አካባቢዎቹን ለመቆጠጠር በተደረገ ውጊያና ከዚያ በኋላ በነበሩ ጊዜያት በህወሓት ኃይሎች ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ የሆኑት አቶ ይርጋ ሲሳይ ቅጣው ለቢቢሲ እንደተናገሩት አማጺያኑ ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን በመግባት በተለይ ጋይንት፣ ንፋስ መውጫ፣ ጎብጎብ ሳሊህ፣ እንዲሁም ጉና በጌምድር እንዲሁም በከፊል የፋርጣን አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ነበር ብለዋል።
በዚህ ወቅትም በአካባቢዎቹ የሚገኙ ሆስፒታሎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋም፣ የመብራት ሰብ ስቴሽን፣ ባንኮችና ሌሎችም ሕዝባዊ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም የግል ንብረቶች ሳይቀሩ መዘረፋቸውን ሚናገሩት አቶ ይርጋ ሌሎች ንብረቶች ደግሞ መልሰው ጥቅም ላይ እንዳውሉ ሆነው ወድመዋል ብለዋል።
የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት የንፋስ መውጫ ነዋሪ አቶ አልማው ጥጋቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለሦስትና ለአራት ቀናት አጎራባች በሆነው ደብረዘቢጥ በሚባለው ስፍራ ጦርነት እንደነበርና የከባድ መሳሪያ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አማጺያኑ "ወደ ከተማችን ከገቡ በኋላ በአካባቢው የሕዝብ መገልገያ የሆኑት እንደ ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶችና ባንኮችን የመሳሰሉ ተቋማትን ዘርፈዋል። ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑም አድርገዋል" ይላሉ።
ከባድ ውድመትና ዘረፋ ደርሶበታል የተባለው በንፋስ መውጫ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊታውራሪ ገብርዬ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለምነው ስዩም ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ባንኩ በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ዘረፋና የንብረት ውድመት ደርሶበታል።
አማጺያኑ ወደ ዞኑ በገቡበት ወቅት ነዋሪዎች በግልም ሆነ በቡድን ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ ከሠራዊቱ ውጪ ከነዋሪው አስካሁን በደረሳቸው መረጃ ቢያንስ 21 ሰዎች መሞታቸውን የሚገልጹት አቶ ይርጋ ቁጥሩ ከዚህ በላይም ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
ሌላኛው የነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪ ያሬድ አለነ በበኩሉ ከተማዋ በህወሓት ኃይሎች ስትያዝ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ፤ ጥቃቱን በመፍራት ወደ ሌሎች ቦታዎች የሸሹ ነዋሪዎች ስላሉ ሁሉም ሲመለስ የሞቱት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር እንደሚለይ ገልጿል።
"ንፋስ መውጫ ከተማ እንዳልነበረች ሆናለች" የሚለው ያሬድ ባንኮችና በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የሕዝብ ተቋማት እንዲሁም የግል ንብረቶች ስለተዘረፉና እንዲወድሙ ስለተደረገ በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ከእንቀስቃሴ ውጪ ሆና ቀዝቅዛለች ብሏል።
የዞኑ ዋና ከተማ ከሆነችው ከደብረ ታቦር በተጨማሪ በንፋስ መውጫ ላይ የህወሓት ኃይሎች በተኮሱት ከባድ መሳሪያ የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን አቶ ይርጋ ተናግረዋል።
የነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪው አቶ አልማው በበኩላቸው አማጺያኑ ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ "እኔ የማውቃቸውና በዚሁ ቀበሌ የሚኖሩና በስም የማውቃቸው ጭምር ከሃያ በላይ ሰዎች ተገድለዋል" ሲሉ ተናግረው፤ ተገደሉ ካሏቸው ሰዎች መካከል የሚያወቋቸውን ሰዎች ስም ዘርዝረዋል።
በአካባቢዎቹ በሰውና በንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር "በርካታ የቤት እንስሳት በጠላት ተመተዋል። የአርሶ አደሩ ንብረት የሆኑ ብዙ ከብቶች፣ ፈረሶች፣ በጎች የጠፉበት ሁኔታ ነው ያለው" ያሉት ደግሞ አቶ ይርጋ ናቸው።
የፎቶው ባለመብት, AMHARA COMMUNICATION
የብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ኃላፊ በአካባቢው ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር ሲያስረዱ ከሆስፒታል በተጨማሪ ወደ ሰባት የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል እንዲሁም ውድመት ተፈጽሞባቸዋል ብለዋል።
"በተግባር አይተን እንዳረጋገጥነው በሮች ተሰብረዋል፣ የተለያዩ የሆስፒታል መገልገያዎች፣ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ተዘርፈዋል። በነገራችን ላይ ቁሳቁሶቹን አውጥተው ተቋሙን እንኳን ቢተው ጥሩ ነው። ተቋሞቹም እንዲፈርሱ ነው ያደረጉት" ሲሉ የደረሰውን ጉዳት ዘርዝረዋል።
በተጨማሪም በከተማው የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ያመለከቱት አቶ ይርጋ፤ ባንኩን ከአማጺያኑ ለመከላከል ጥረት ያደረጉ የጥበቃ አባላት መገደላቸውንና ባንኩ ከባድ ጉዳት ደርሶበት መዘረፉን ተናግረዋል።
በአካባቢው ባሉ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትና በግል ንበረቶች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የሚናገሩት አቶ ይርጋ ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር ለማወቅ ኮሚቴ አዋቅረው እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የንፋስ መውጫ ነዋሪ የሆኑት አቶ አልማው ጥጋቡ በከተማዋ ላይ የደረሰው ውድመት የከተማዋን ገጽታ እንደቀየረው በመግለጽ "ንፋስ መውጫን ከጦርነቱ በፊት የሚያውቃት ሰው አሁን ሲመለስ ከተማዋ እሷ መሆኗን ይጠራጠራል። የሚያውቋት ከተማ መሆኗን በድፍረት መናገር አይቻልም" ብለዋል።
በህወሓት ኃይሎች ዘረፋና ውድመት ተፈጸመባቸው የተባሉት በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኙት አካባቢዎች በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር ለስምንት እና ለዘጠኝ ቀናት መቆየታቸውንና ይህ ሁሉ ጉዳት የደረሰው በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደሆነ አቶ ይርጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አካባቢዎቹ ካለፈው ሰኞ ነሐሴ 17/2013 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራሉ ሠራዊትና በክልሉ ልዩ ኃይል አማካይነት ከህወሓት ኃይሎች ነጻ እንደሆኑ የአካባቢው የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ የሆኑት አቶ ይርጋ ሲሳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዘጠኝ ወራት በፊት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ለወራት በዘለቀው ጦርነት ባለፈው ሰኔ ወር የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስጣቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የተኩስ አቁም ለማድረግ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች እስኪሟሉ ድረስ ውጊያ እንደሚቀጥሉ ያስታወቁት የህወሓት ኃይሎች ጦርነቱን ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አማራና አፋር ክልል አስፋፍተውት ቆይተዋል።
በዚህም አማጺያኑ ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ጥቃት ከፍተው አንዳንድ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ችለዋል። በተስፋፋው ጦርነት ሳቢያም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ አጎራባቾቹ ሁለቱ ክልሎች አሳውቀዋል።
የፌደራል መንግሥቱና የክልል ኃይሎች አማጺያኑን ከያዟቸው ስፍራዎች ለማስለቀቅ የተጠናከረ ዘመቻ እያካሄዱ መሆናቸውንና ነጻ የወጡ ቦታዎች እንዳሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ።
ይህንንም ተከትሎ ከህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ነጻ እንደሆኑ ከተነገረላቸው አካባቢዎች መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች በሕዝብ መገልገያዎችና በግል ንብረት ላይ በአማጺያኑ ዘረፋና ውድመት መፈጸሙ በስፋት እየተነገረ ነው።
በአገሪቱ ምክር ቤት ከወራት በፊት በሽብርተኛ ቡድንነት የተፈረጀው ህወሓት ኃይሎቹ ፈጽመውታል ስለተባሉት ዘረፋና ውድመት እስካሁን ያለው ነገር የለም።