የሕዳሴ ግድብ ዘንድሮ በሱዳን የጎርፍ መጠን ላይ ተጽዕኖ አላሳደረም ተባለ

ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Water, Irrigation and Energy/FB

የምስሉ መግለጫ,

ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በዚህ ዓመት በሱዳን የተከሰተው የጎርፍ መጠን ላይ ምንም ተጽዕኖ አላሳደረም ተባለ።

የሱዳን የመስኖ ሚንስትር ያሲር አባስን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ በዚህ ዓመት በሱዳን በተከሰተው የጎርፍ መጠን ላይ የሕዳሴ ግድቡ ምንም ለውጥ አላስከተለም።

ሱዳን በግድቡ ምክንያት የጎርፍ መጠን ለውጥ ያመጣል በሚል ስጋት ከፍተኛ ወጪ አውጥታ ቅድመ ጥንቃቄ ስታደርግ እንደነበርም ተዘግቧል።

የሱዳን የመስኖ ሚንስትር ያሲር አባስ በትዊተር ገጻቸው "ግድቡ ውሃ ቢሞላም የግድቡ ግንባታ በዚህ ዓመት የጎርፍ መጠን ላይ ተጽዕኖ አላሳደረም። ነገር ግን ከውሃ ሙሌቱ በፊት የመረጃ ልውውጥ ስላልነበረ ሱዳን ጎርፍ በምጣኔ ሀብቷ እና በማኅበራዊ ሕይወት የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ለመቅረፍ ስትል ለቅድመ ጥንቃቄ ከፍተኛ ወጪ አውጥታለች" ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ለዓመታት ሲወዛገቡ ነበር። በቅርቡ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት ስታከናውን ግብፅ እና ሱዳን መቃወማቸው አይዘነጋም።

ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ የሚተበቀው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሲተናቀቅ ከአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ይሆናል።

ግንባተው ከሰማኒያ በመቶ በላይ የተጠናቀቀው ግድብ በቅርቡ የሙከራ ኃይል ማመንጨት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለአካባቢው አገራት ከማቅረቡ በተጨማሪ፤ በየዓመቱ በጎርፍ የምትጠቃውን የሱዳንን ጫና ይቀንሰዋል ተብሏል።

ግብፅ እና ሱዳን ለተቃውሟቸው እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ሦስቱ አገራት ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት ጀምራለች የሚለውን ነው።

ኢትዮጵያ ግን አንዳችም መርህ እንዳልጣሰችና የተፋሰሱን አገራት አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ የግድቡን ውሃ ሙሌት እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

ሱዳን በዝናባማ ወቅት በአገሯ የሚከሰተውን ጎርፍ ለመቀነስ የሕዳሴ ግድቡ እንደሚረዳት ተናግራለች። የሕዳሴ ግድቡ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ስለምትሆንም ግንባታውን ትደግፋለች።

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ስለ ግድቡ ውሃ ሙሌትና አሠራር ግልጽ መረጃ እየሰጠች አይደለም ስተል ሱዳን ትተቻለች። እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሱዳን አቋም ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብፅ የቀረበ ሆኗል።

ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ዙርያ ሦስቱ አገራት ስምምነት ሳይፈርሙ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ መጠየቃቸው ይታወሳል። ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ወስደውትም ነበር።

የጸጥታው ምክር ቤት ሦስቱ አገራት በዋነኛነት በአፍሪካ ሕብረት የበላይ አሸማጋይነት ለጉዳዩ እልባት እንዲሰጡ ምክረ ሐሳብ መስጠቱም ይታወሳል።

የሱዳን የመስኖ ሚንስትር እንዳሉት ግድቡ ከሐምሌ 20 በኋላ የተሞላውን ውሃ ያህል ወደ ውጪ አፍስሷል።

ሱዳን ለመጀመሪያ ጊዜ ግድቦቿን ተጠቅማ በየዓመቱ የሚያስቸግራትን የጎርፍ መጠን ዘንድሮ መቆጣጠር መቻሏን ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ጎርፍ እየተከሰተ በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ዜጎችን ይፈትን ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት በዓመቱ መባቻ ላይ እንዳለው፤ በመላው ሱዳን በክረምት ወቅት ወደ 70,000 የሚጠጉ ሰዎች ችግር ላይ ይወድቃሉ።

ከእነዚህ አብዛኞቹ የሚኖሩት በዓባይ ወንዝ መፍሰሻ አቅራቢያ ነው። ነጭ ዓባይ እና ጥቁር ዓባይ ወደ ግብፅ የሚፈሱት በሱዳን መዲና ካርቱም ከተገናኙ በኋላ ነው።

ዘንድሮ ግን ሱዳን ውስጥ በጎርፍ ምክንያት ችግር የገጠማቸው ሰዎች 380,000 እንደሆኑ የተመድ መረጃ ይጠቁማል።