ጃፓን 1.6 ሚሊዮን ሞደርና ክትባቶችን አገደች

ጃፓን 1.6 ሚሊዮን ሞደርና ክትባቶችን አገደች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጃፓን 1.6 ሚሊዮን ሞደርና ክትባቶች ተበክለው ሊሆን ይችላል ብላ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አገደች።

የጃፓን የጤና ሚንስትር እንዳለው፤ ቢያንስ 560,000 የሚደርሱ ብልቃጦች ውስጥ "ባዕድ ነገር ተገኝቷል።"

ጃፓን ውስጥ ክትባቶች የሚሸጠው እና የሚያከፋፍለው ታኬዳ ፋርማሱቲካል እንደገለጸው፤ ሞደርና ጥንቃቄ ለማድረግ ሲል ሦስት ዙር ክትባቶችን ለጊዜው አግዷል።

ስፔን የሚገኝ ክትባት ማምረቻ ውስጥ የተፈጠረ ችግር እንዳለ ቢገልጽም ዝርዝሩን አላብራራም።

ሞደርና እንዳለው እስካሁን ድረስ "አንዳችም የደኅንነት እና ውጤታማ ያለመሆን ችግር" አልገጠመውም።

ከጃፓኑ ክትባት አከፋፋይ ጋር በመሆን ጉዳዩን እንደሚመረምርም አክሏል።

የጃፓን ጤና ሚንስቴር "ባዕድ ነገሮች" ያለው ምን እንደሆነ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም ታኬዳ ፋርማሱቲካል ምርመራ ካደረገ በኋላ እንዳገኛቸው አስታውቋል።

የጃፓን ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ሰባት ክትባት ሰጪ ማዕከሎችም በ390 ብልቃቶች ላይ የክትባት መበከል እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

ክትባቶቹ ከመታገዳቸው በፊት የወሰዱ ሰዎች መረጃው እንዲደርሳቸው በሚልም የክትባቶቹ የመለያ ቁጥር ይፋ ተደርጓል።

የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ በመጣባት ጃፓን፤ በስምንት ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሏል።

ፋይዘር እና አስትራዜኒካ በአገሪቱ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተፈቅዷል። ለሞደርና ፍቃድ የተሰጠው ደግሞ ባለፈው ግንቦት ነው።

40 በመቶ ጃፓናውያን ሁለቱንም ክትባት ሙሉ በሙሉ ሲከተቡ፤ 50 በመቶው አንድ ክትባት ወስደዋል።