የወባ በሽታን 70 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል አንድ ጥናት አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአንድ ጥናት መሰረት አዲስ አይነት የመከላከል መንገዶችን በመጠቀም አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት በወባ በሽታ የመያዝና የመሞት ዕድላቸውን በ70 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል ተጠቆመ።
የወባ በሽታ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸው ወራት ከመድረሳቸው በፊት ክትባቱን እንዲወስዱ ማድረግና በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች መከላከያ መድኃኒቶችን እንዲጨምሩበት በማድረግ ሙከራው ከፍተኛ የሆነ ውጤት ማስገኘቱን በለንደን የሚገኙ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።
የዚህ የወባ በሽታን የመከላከል ሙከራው የተደረገው ከቡርኪናፋሶ እና ከማሊ የተወጣጡ ከ17 ወራት በታች የሆኑ 6 ሺህ ህጻናት ላይ ነው ተብሏል።
አፍሪካ በየዓመቱ በወባ በሽታ ምክንያት እስከ 400 ሺህ ሞቶችን የምታስመዘግብ ሲሆን አብዛኞቹ ደግሞ እድሜያቸው ከአምስት ወራት በታች ነው።
ይህ ጥናት 'በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜድሲን' የህክምና መጽሔት ላይ የታተመ ሲሆን በሙከራው ላይ ለህጻናቱ አሁን ላይ የሚገኙ የወባ ክትባቶችን ቀድሞ መስጠትና የወባ በሽታ በብዛት በሚከሰትባቸው ወራት ደግሞ (አብዛኛውን ጊዜ የዝናብ ወራት ናቸው) ሌሎች የወባ መከላከያ መድኃኒቶችን በመስጠት ነው ከፍተኛ ውጤት የተገኘው።
"እኛ እናገኘዋለን ብለን ካሰብነው ውጤት በጣም የተሻለ ነገር ነው ያገኘነው" ብለዋል የምርምር ቡድኑ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ብራያን ግሪንዉድ።
"በሁለቱም አገራት ሙከራውን ከጀመርን በኋላ በወባ በሽታ ምክንያት ሆስፒታል የሚገቡና ህይወታቸው የሚያልፍ ህጻናት ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።"
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሰራው ሙከራ የዝናብ ወራት ከመድረሳቸው በፊት ሦስት የወባ ክትባቶች ለህጻናቱ የተሰጣቸው ሲሆን የዝናብ ወቅት ሲገባ ደግሞ የተለያዩ አይነት የወባ መከላከያ መድኃኒቶችን እንዲወስዱ ተደርጓል። በዚህም የወባ በሽታ ስርጭትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ታይቶበታል።
የዚህ ሙከራ ውጤትም ከየትኛውም አይነት ክትባትና መድኃኒት በተሻለ መልኩ ውጤት ያስገኘ ሲሆን በአፍሪካ በወባ በሽታ የሚጠቁ ህጻናትን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ይህም ሚሊየኖችን ህይወት እንደሚታደግ ከወዲሁ ተገምቷል።
በሙከራው ላይ ክትባቱን ቀደም ብለው ከወሰዱትና በዝናብ ወቅት ደግሞ ሌሎች መከላከያዎችን ከወሰዱት ህጻናት መካከል 624ቱ በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆን 11 ህጻናት ደግሞ ሆስፒታል ገብተው ህክምና ወስደዋል። በተጨማሪም የሟቾች ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ 3 ብቻ ነበር።
በዚህ ሙከራ እንዳይካተቱ ከተደረጉት ተመሳሳይ ቁጥር ካላቸው ህጻናት መካከል ደግሞ 1661 ህጻናት በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆን 37 ህጻናት ደግሞ ሆስፒታል ገብተዋል። የሟቾች ቁጥር ደግሞ 11 ነበር።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ይህ አዲስ ሙከራ በጣም ውጤታማ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። ከዚህ በፊት በሚደረጉ ሙከራዎች ጉንፋንን ቀድሞ ለመከላከል መሰል ጥረቶች ቢደረጉም በወባ በሽታ ላይ ሲሞከር ግን ይህ የመጀመሪያው ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት የወባ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ፔድሮ አሎንሶ ደግሞ "ይህን አዲስ አይነት የወባ በሽታ ክትባትና መከላከል ሥራ በመልካም ጎኑ ነው የምንመለከተው። አፍሪካ ውስጥ በርካታ ሞትን ማስቀረት እንደሚያስችል እንገምታለን" ብለዋል።
የወባ በሽታ ክትባቱ እስካሁን 740 ሺህ ለሚሆኑ ጋና፣ ኬንያ እና ማላዊ ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት የተሰራጨ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ይሁንታውን እስኪሰጥ እየተጠበቀ ነው።
በዚህ ሙከራ ላይ የትኛውም ህጻን ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላስተናገደ ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት ህጻናት ክትባቱን እና መከላከያ መድኃኒቶቹን እስከ 5 ዓመታቸው ድረስ እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን በዚያውም ሌሎች የተሻሉ አማራጮች ከመጡ አብረው እንደሚካተቱ ተገልጿል።