ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ የሠራዊት አባላት ላይ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ

የመከላከያ አርማ

የፎቶው ባለመብት, FDRE DEFENCE

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ቀዳማዊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ከህወሓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በተባሉና በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈዋል በተባሉ የሠራዊቱ አባላት ላይ አስከ 18 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ፈረደ።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በትግራይ ክልል በፌደራሉ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሠራዊቱ ውስጥ በመሆን የተለያዩ የወንጀል ተግባራት ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ነው የተፈረደባቸው።

በዚህም መሠረት ወታደራዊ ችሎቱ ሐሙስ ነሐሴ 20/2013 ዓ.ም የቀረቡለትን ስምንት የክስ መዝገቦች መርምሮ በተከሳሾቹ ላይ ከስምንት አስከ 18 ዓመት የሚደርስ ጽኑ አስራት መወሰኑ ተገልጿል።

ችሎቱ ከተመለከታቸው መዝገቦች መካከል በአንደኛው ላይ የተለያዩ ክሶች የቀረቡበት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ በግዳጅ ላይ እያለ "ትግርኛ ተናጋሪ የሠራዊቱን አባላት ብቻ ነጥሎ በመሰብሰብ ከተቋሙ የዕዝ ሰንሰለት ውጪ ለጥፋት ሥራ የሚውል አደረጃጀት ፈጥረዋል" የሚል ይገኝበታል።

በዚህ አደረጃጀት አማካይነት "በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን አይነት ጥቃት በሚመሯቸው የሠራዊት አባላት ላይ ለመድገም አቅደው ሲሰሩ መቆየታቸውን" የቀረበባቸው ክስ ያመለክታል።

በተጨማሪም ክስ የቀረበባቸው የሠራዊቱ አባላት "ከሌላ ብሔር የመጡና አብረዋቸው የሚሠሩ ከፍተኛ አመራሮችን በመግደል ሠራዊቱን ወደ ትግራይ ይዘው ለመግባት አቅደው ነበር" የሚልና ሌሎችም ክሶች ቀርበዋል።

በሌሎቹ ሰባት የክስ መዝገቦች ጉዳያቸው የታየው የሠራዊቱ አባላት ሠራዊቱን ለትግራይ ልዩ ኃይል በመመልመል፣ የሽብር ወሬዎችን በማሰራጨት እና መከላከያ ሠራዊቱን በሚያፈርሱ ተግባራት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ተከሰዋል።

እንዲሁም ተከሳሾቹ በሕጋዊ ፍቃድ ሽፋን የትግራይን ልዩ ኃይል የሚያሰለጥኑ አባላትን ወደ ቦታው በመላክ በሠራዊቱ ውስጥ አንድነት እንዳይኖር ስጋት በመፍጠር፣ በህቡዕ ተደራጅቶ ሠራዊቱን ለማፍረስ በመጣር እና ሠራዊቱ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ ተግባራትን ፈጽመዋል ተብሏል።

ቀደም ባለው ችሎት ተከሳሾቹ የቀረቡባቸውን ክሶች እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የተከራከሩ ቢሆንም የሰነድና የሰው ማስረጃዎች ለችሎቱ ቀርቦ ነበር።

ወታደራዊ ችሎቱም ተከሳሾቹ የቀረቡባቸውን ክሶች በበቂ ሁኔታ መከላከል እንዳልቻሉ በመግለጽ በቀረበባቸው ክስ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማሳለፍ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ ነበር።

በዚህም መሠረት ክሱን ሲመለከት የቆየው የሠራዊቱ የደቡብ ዕዝ ቀዳማዊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ እና የተከሳሽ ጠበቃ የቅጣት ማቅለያ ከሰማ በኋላ በተከሳሾች ላይ ከ8 ዓመት እስከ 18 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ወስኗል።