አሜሪካ ዕቀባ የጣለችባቸው የኤርትራ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊልጶስ ወልደዮሐንስ ማን ናቸው?

ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/TESFANEWS

የምስሉ መግለጫ,

ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት ውስጥ ተፈጽመዋል ከተባሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ በኤርትራ ጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ላይ ዕቀባ መጣሏን ከቀናት በፊት አስታውቃለች።

በዚህ የአሜሪካ ጠቅላይ ግምጃ ቤት እገዳ ምክንያት ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ በአሜሪካ ውስጥ ባላቸው ንብረትና ገንዘብ ላይ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ዕቀባ የተጣለ ሲሆን ለሚመለከተው የአገሪቱ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣንም ስለግለሰቡ ሪፖርት እንደሚደረግ አመልክቷል።

ስለእኚህ ከፍተኛ የኤርትራ ጦር ሠራዊት ባለሥልጣን ምን ይታወቃል?

ከአሥመራ ከተማ ትንሽ ኪሎ ሜትር ራቅ ብላ በምትገኝ ቁሸት በተባለች መንደር የተወለዱ የኤርትራ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ1972 ነበር ለኤርትራ ነጻነት ይካሄድ ወደነበረው የትጥቅ ትግል የገቡት።

ወደ በረሃ ወጥተው ለጥቂት ወራት ወታደራዊ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ከኤርትራ ደጋማ ክፍል ወደ ቆላማው የሳህል በረሃ አዲስ ምልምሎችን በሚያመላልሰው ቡድን እንዲሁም የተዋጊው ቡድን በጦር መሳሪያ ማከማቻ ዘርፍ ውስጥ ተመድበው ሠርተዋል።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ በዘጠነኛ ሻለቃ የቡድን ኮሚሽነር በመሆን እግረኛ ተዋጊ የነበሩ ሲሆን ከዚያም የሻምበል አዛዥ ለመሆን ችለዋል።

በ1977 አጋማሽ በ23ኛ ብርጌድ የሻለቃ አዛዥ ሆነው የተሾሙት ፊሊጶስ፤ በዚያው ወቅት በተካሄዱ በርካታ ከባድ ጦርነቶች ውስጥ አዛዥም ተዋጊም ሆነው ተሳትፈዋል።

በ1978 ደግሞ የደርግ መንግሥት ባካሄዳቸው ከባድ ወታደራዊ ዘመቻዎች የኤርትራ ነጻ አውጪ ሠራዊት ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ ከተሞችና ምሽጎች እንዲለቁ ስላደረጋቸው ወደ ተራራማው የሳህል በረሃ አፈገፈጉ።

እዚያም ፊሊጶስ የ44ኛ ብርጌድ አዛዥ በመሆን ከደጋው ክፍል እስከ ሳህል ከመቶ ኪሎ ሜትሮች በላይ ርቀት ባለው ክልል ውስጥ በተደረጉ ትላልቅና ተከታታይ ውጊያዎች ላይ ተሳትፈዋል።

ጄነራል ፊሊጶስ ኤርትራን ነጻ ለማውጣት በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ከባድና ወሳኝ ውጊያዎች ውስጥ ሠራዊት በመምራት የተሳተፉና በበርካታዎቹም ስኬታማ የጦር መሪ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ኤርትራ ነፃ ከወጣች በኋላ የሜጀር ጄነራልነት ማዕረግ ተሰጥቶቷቸው የኮር አዛዥ ሆኑ።

ከ20 ዓመት በፊት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተካሄደው የድንበር ጦርነት ወቅት ደግሞ የመረብ ግንባር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።

ጄነራሉ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት በአምስት ወታደራዊ ዞኖች ተከፋፍሎ በተደራጀበት ወቅት ደግሞ የዞን ሁለት አዛዥ ሆነው ነበር።

ከስድስት ዓመት በፊት የቀድሞው የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄነራል አንደማርያም ገብረእግዚአሔር ሲያርፉ፤ ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ባለአራት ኮከብ የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ አግኝተው ኃላፊነቱን በመረከብ እስከ አሁን ድረስ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች የበላይ ሆነው እየሰሩ ነው።

ጄኔራል ፊልጶስ በወታደራዊ ጉዞቸው፣ ሠራዊታቸውን በጥብቅ ቁጥጥር የሚከታተሉ ወታደራዊ ዕቅዶችንና ተፈጻሚነታቸውን በቅርብ የሚከታተሉ የተዋጣላቸው ወታደር እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ባህሪያቸውን በተመለከተም ጄኔራሉ ብዙ የማይናገሩ፣ ኮስታራ፣ በጣም ጠንቃቃ፣ ምንም ነገር ችላ የማይሉ ቆፍጣና ወታደር እንደሆኑ አብረዋቸው የሰሩ ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።

የኤርትራ ገዢ ፓርቲ በሆነው በሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ ስር ባለው "ሕድሪ ኣሳታሚ" የተሰኘው ድርጅት ባሳተመው "መፈጸምታ" በተሰኘው መጽሐፍ "ጦርነት ከሳይንስ ይልቅ ጥበብ ነው" በሚል ርዕስ ጄነራሉ በተለያዩ ጦርነቶች ወቅት ያጋጠማቸውን ፈተና እንዴት በጥበብ እንዳለፉ አስፍረዋል።

በነጻነት ታጋይነት በረሃ ለዓመታት የቆዩት ከነጻነት በኋላ ደግሞ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ የአመራርነት ቦታ ላይ ለ30 ዓመታት የቆዩት ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ የአሜሪካ መንግሥት ዕቀባ ኢላማ ሆነዋል።

ይህ ዕቀባ በንብረትና በገንዘብ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን ጄነራሉ በአሜሪካም ሆነ ከኤርትራ ውጪ ስላላቸው ሀብት የሚታወቅ ነገር የለም።

ዕቀባውን የጣለው የአሜሪካ መንግሥት ግምጃ ቤትም እገዳው በየትኞቹ የጄነራሉ ንብረቶችና ጥቅሞች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆኑ በግልጽ አላመለከተም።

በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ እንደነበረ የሚነገረው የኤርትራ ሠራዊት የተለያዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን በተመለከተ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርት አድርገዋል።

የአሜሪካ መንግሥትም በጦሩ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ላይ ዕቀባው የተጣለው በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

ይሁን እንጂ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሠራዊቱና በመሪው ላይ የቀረበውን ክስና የተጣለውን የዕቀባ እርምጃ "ኢ-ሕጋዊና ተቀባይነት የሌለው" ነው ሲል እንደማይቀበለው አስታውቋል።