ጁቬንቱሶች ፍላጎታቸው ከተሟላ ሮናልዶን መልቀቅ እንደሚችሉ አሳወቁ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጁቬንቱሶች ፍላጎታቸው ከተሟላ ክርስቲያኖ ሮናልዶን በዚህ ክረምት ለመሸጥ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታወቁ።

የ36 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ ኮንትራቱ ሊጠናቀቀ አንድ ዓመት ይቀረዋል።

የሮናልዶ የወደፊት ዕጣ ፈንታ መነጋገሪያ ሲሆን ክለቡ ከዩዲኒዜ ጋር ባደረገው የሴሪ አ መክፈቻ ጨዋታ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አልተካተተም።

ወኪሉ ዮርጌ ሜንዴዝ ማንቸስተር ሲቲ እና ፓሪስ ሴንት ዠርሜንን ጨምሮ እሱን ሊያስፈርሙ ከሚችሉ በርካታ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ጋር ተነጋግሯል።

ሲቲ ስምምነት ለመፈጸም እያሰበ ሲሆን ከቋጫ ላይ ግን አልደረሰም።

ሜንዴዝ ሐሙስ ከክለቡ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ወደ ጁቬንቱስ ተጠርቶ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል።

ከምክትል ፕሬዝዳንቱ ፓቬል ኔድቬድ፣ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ማውሪዚዮ አሪቫቤኔን እና የስፖርት ዳይሬክተሩን ፌዴሪኮ ቼሩቢኒን ጨምሮ ከሌሎችም ጋር ለመነጋገር ነው ወደ ቱሪን ያቀናው።

በሮናልዶ ዙሪያ ሁሉም አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለሜንዴዝ ተነግሮታል። ነገር ግን ጁቬንቱስ ከሦስት ዓመት በፊት በ99.2 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈረሙትን ተጫዋች በነጻ መልቀቁን እንደማይቀበል ተነግሯል።

ሮናልዶ ከሪያል ማድሪድ ወደ ጁቬንቱስ መሄዱ እንዳላስደሰተው ይታወቃል።

ለሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከመወዳደር ይልቅ የጣሊያኑ ቡድን ሮናልዶ ከመጣ ጀምሮ ሩብ ፍጻሜውን ሳያሳልፍ ቀርቷል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ተሸንፏል።

ቡድኑ ባለፈው የውድድር ዘመን የሴሪ አ ዋንጫውን ከተከታታይ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ በኢንተር ሚላን ተነጥቋል። የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነትን ያረጋገጡት በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነው።