ከወራት በፊት በታጣቂዎች ታፍነው የነበሩ ናይጄሪያዊያን ሕፃናት ተለቀቁ

ትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የናይጄሪያ ታጣቂዎች ባለፈው ግንቦት ከአንድ የእስልምና ትምህርት ቤት አፍነው የወሰዷቸውን በርካታ ሕፃናት መልቀቃቸውን የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ተናገሩ።

ናጀር ግዛት ውስጥ ከሚገኘው የተጊና ትምርህርት ቤት ነበር 136 የሚደርሱ ሕፃናት ነበሩ በታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት።

የትምህርት ቤቱ ሰዎች 15 ሕፃናት ከታፈኑበት ማምለጥ ሲችሉ ስድስት ሕፃናት ደግሞ በቁጥጥር ሥር ሳሉ ሞተዋል ብለዋል።

ናይጄሪያ ውስጥ በርካታ ሕፃናትን አፍኖ ወስዶ ማስለቀቂያ መጠየቅ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ እየተለመደ መጥቷል።

የትምህርት ቤቱ ኃላፊ አቡባካር አልሃሳን ምን ያክል ሕፃናት እንደተለቀቁ በግልፅ ባይናገሩም "አሁን በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ያለ ሕፃን የለም" ብለዋል።

ኃላፊው ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል እንደተናገሩት ሕፃናቱ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እየመጡ ነው።

ሕፃናቱ እንዴት ከታጣቂዎቹ እገታ ነጻ ሊወጡ እንደቻለ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ፋቲ አብዱላሂ የ18 ዓመት ሴት ልጇና የ15 ዓመት ወንድ ልጇ በታጣቂዎቹ ተወስደውባት ነበር። አሁን ግን ተለቀዋል ብላለች።

"ልናያቸው በጣም ጓጉተናል" ስትልም ተናግራለች።

ባለፈው ግንቦት መገባደጃ ላይ ነበር ታጣቂዎች በሞተር ብስክሌት እየከነፉ መጥተው በትምህርት ቤቱ ላይ ተኩስ የከፈቱት።

በወቅቱ ታጣቂዎቹ በከፈቱት የተኩስ እሩምታ ምክንያት አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ መጎዳቱ ይታወሳል።

ሰዎች እሩምታውን ሽሽት እግሬ አውጪኝ ሲሉ ታጣቂዎቹ ወደ መማሪያ ክፍሎች በማቅናት ሕፃናቱን በቁጥጥር ሥር አውለዋቸዋል።

ሐምሌ ላይ ታጣቂዎቹ ሕፃናቱ እንዲለቀቁ ካሳ ለመክፈል የመጣን አንድ ግለሰብም አፍነው ነበር።

የሕፃናቱ ቤተሰቦችና የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ያላቸውን ሀብትና ጥሪት ሸጠው ሕፃናቱ እንዲለቀቁ ገንዘብ ቢልኩም አፋኞቹ አይበቃም ብለው ነበር።

ካለፈው ታኅሣሥ ጀምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች ናይጄሪያ ውስጥ ከሚገኙ ትምህት ቤቶች ታፍነው ተወስደዋል።

ባለሥልጣናት ይህንን እየተስፋፋ ያለ ወንጀል ማስቆም አለመቻላቸው ለወቀሳ ዳርጓቸዋል።