በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ስለደረሰው ፍንዳታ እስካሁን የሚታወቁ ነገሮች

በፍንዳታዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር አሁንም ድረስ እየጨመረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በፍንዳታዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር አሁንም ድረስ እየጨመረ ነው።

ሁለት ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ አቅም ያላቸው የቦምብ ፍንዳታዎች በካቡል የሚገኘውን የሀሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ክፍል እንዳልነበር ያደረጉት ሲሆን፤ በርካታ ንጹሀን ዜጎች ደግሞ አሁንም ከታሊባን አስተዳደር ለማምለጥ በረራዎችን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

በፍንዳታው ቢያንስ 90 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ ተጨማሪ 150 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ካቡል ውስጥ የሚገኙ አንድ ከፍተኛ የጤና ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፔንታጎን በበኩሉ ከሟቾች መካከል 13 አሜሪካውያን እንደሚገኙበት ገልጿል።

በርካታ የምዕራቡ ዓለም አገራት ዜጎቻቸው ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዳይሄዱ ካስጠነቀቁ ከሰዓታት በኋላ ነው ፍንዳታዎቹ የተከተሰቱት። በወቅቱም በአፍጋኒስታን የአይሲስ ክንፍ የሆነው አይኤስ-ኬ የተባለው ቡድን ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል ተገልጾ ነበር።

ስለ ፍንዳታው እስካሁን የምናውቀው

ፍንዳታዎቹ ከአየር ማረፊያው ውጪ ነው የተከሰቱት።

የመጀመሪያው ፍንዳታ ከአውሮፕላን ማረፊያው አጥር አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ባሮን ሆቴል አቅራቢያ ሲሆን በወቅቱም ሆቴሉ ውስጥ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚጓዙ አፍጋኒስታናውያንን ጉዳይ የሚከታተሉ ኃላፊዎች ነበሩ።

ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የተኩስ እሩምታ ተሰምቷል። በመቀጠል በአየር ማረፊያው ዋና ከሚባሉት በሮች መካከል አንዱ በሆነው አቤይ በር በኩል ሌላ ፍንዳታ ተሰምቷል።

አንዳንድ በአካባቢው የነበሩ ሰዎችን ጠቅሰው በሚወጡ መረጃዎች መሠረት ሁለተኛው ፍንዳታ የተከሰተው በርካታ አፍጋኒስታናውያን ተራቸውን ሲጠብቁበት በነበረው ትልቅ የፍሳሽ ማስወገጃ ጉድጓድ አካባቢ ነው። ፍንዳታው ሲከሰትም በአካባቢው የነበሩ ሰዎችን ወደ ጉደድጓዱ ጭምር እንደከተታቸው ተገልጿል።

አንድ የአሜሪካ ኃላፊ እንደገለጹት ቢያንስ አንደኛው ጥቃት ፈጻሚ ተቀጣጣይ ፈንጂ በሰውነቱ ላይ አስሮ ነበር።

በአሁኑ ሰአት የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ወታደሮች ጥቃቱ የደረሰበትን አካባቢ በንቃት እየጠበቁ ይገኛሉ።

ጥቃቱ ወደደረሰበት የአውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ የሚሄዱ የአሜሪካ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉና በፍጥነት አካባቢውን ለቅቀው እንዲሄዱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር ተብሏል።

የጉዳቱ መጠን

በፍንዳታዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር አሁንም ድረስ እየጨመረ ነው።

እስካሁንም ድረስ በአሜሪካ እና አፍጋኒስታን በኩል የመጨረሻ ቁጥር ያልተለጸ ሲሆን በታሊባን በኩልም ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ ይገመታል።

ነገር ግን የአሜሪካው ፔንታጎን 13 የአሜሪካ ወታደራዊ ሠራተኞች በፍንዳታዎቹ መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ተጨማሪ 15 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

አንድ የካቡል ከፍተኛ የጤና ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ እስካሁን ቢያንስ 90 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአጠቃላይ ደግሞ እስከ 150 የሚደርሱ ሰዎች ተጎድተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጩ በሚገኙ ምስሎች በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሰዎች ተሸክመዋቸው ሲሮጡ ታይቷል። በርካቶች ደግሞ ከአፍጋኒስታን የመውጣት እድል ካገኘን በሚል አሁንም ፍንዳታው በደረሰበት አካባቢ ተሰባስበው ይገኛሉ።

አንዳንድ አገራት ሰዎችን የማስወጣት ሥራቸውን አቁመዋል። ይህ ጥቃት ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ እንደሚያወሳስበው ይገመታል።

ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት እንደ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ካናዳ ያሉ ጥቂት የማይባሉ አገራት ከዚህ በኋላ ከአፍጋኒስታን በረራዎችን እንደማያደርጉ አስታውቀው ነበር።

ቱርክ በበኩሏ ላለፉት ስድስት ዓመታት በአውሮፕላን ማረፊያው ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ ገልጻለች።