የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ተሾሙ

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው መሾማቸውን አስታወቁ።

ይህ ውሳኔ የአፍሪካ ሕብረት በሁሉም አገራት ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም የፖለቲካ ውይይትን ለማበረታታት ከሚያደርገው ጥረት አንደኛው አካል እንደሆነ ተገልጿል።

የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ተሰየሙት ኦባሳንጆ በቀጠናው የሚገኙ ዋነኛ ተዋናዮችና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር እንደሚሠሩ ተጠቁሟል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበሩ ሙሳ ፋኪ ማህማት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፤ የአፍሪካ ሕብረትን የጋራ ጥቅም ለማስከበር ይህንን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ኃላፊነት በመቀበላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ልምድ እና በአፍሪካ መርነት (ፓን አፍሪካኒዝም) ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጠናው ስላለው ሁኔታ ያላቸው ከፍተኛ እውቀት ደግሞ ወሳኝ ነው ተብሏል።

ይህን ተከትሎም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለከፍተኛ ተወካዩ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ሙሳ ፋኪ ማህማት ጠይቀዋል።

ከፍተኛ ተወካዩም በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ወደ አካባቢው እንደሚመጡ ይጠበቃል።

የልዩ መልዕክተኛው ቀዳሚ ሥራ ለወራት የዘለቀው በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።