"ልጆች ይዘን ዋሻ ውስጥ እየኖርን ነው" በሑመራና አካባቢው ያሉ የትግራይ ተወላጆች

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ስር በሚገኙት በሑመራ፣ አደባይ፣ እድሪስ፣ ቃፍታ ሑመራ ወረዳና ደጓጉም ቀበሌ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጾታዊ ጥቃት፣ ጅምላ እስራትና የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመ ነው ሲሉ ተጎጂዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ይህ በሐምሌ ወር እንደ አዲስ የጀመረ ጥቃት እንደሆነ በመግለጽ ህይወታቸውን ለመታደግ ተደብቀው እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ "በተባሉት አካባቢዎች ችግር ደርሶብኛል ብሎ ወደ ቢሮዬ ሪፖርት ያደረገ አንድም ትግርኛ ተናጋሪ የለም። እኔ በማስተዳድረው አካባቢ የሚኖር ሰው ጥቃት ሳይደርስበት እንዲኖር ማድረግ ደግሞ የእኔ ሥራ ነው" በማለት የቀረቡትን ክሶች ውድቅ አድርገዋቸዋል።

ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩት የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ ፋኖና የኤርትራ ሠራዊት ምዕራብ ትግራይን መቆጣጠራቸው ይታወቃል።

በምዕራብ ትግራይ የሚገኘው የሑመራ አካባቢ ከሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ፣ የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም የኤርትራ ወታደሮች ቦታውን ተቆጣጥረውት ቆይተዋል።

በሰኔ ወር መጨረሻ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከትግራይ ሲያስወጣ፣ ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበረው የሑመራ ከተማ የሚገኝበት ምዕራብ ትግራይ ግን በእነዚህ ኃይሎች ስር ይገኛል።

የአማራ ክልል መንግሥትም "ቀደም ሲል በኃይል የተወሰደው መሬታችንን አሁን በኃይል አስመልሰናል" በማለት አካባቢውን እንደማይለቅ ሲገልጽ ቆይቷል።

ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን የተሰለፈው የኤርትራ ሠራዊትም ተመልሶ ወደ አካባቢው እየገባ እንደሆነ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በመግለጽ እንዲወጣ አሳስበዋል።

"ልጆቼን ይዤ ዋሻ ውስጥ እየኖርኩ ነው"

ላለፉት 18 ዓመታት በምዕራብ ትግራይ ዞን ደጓጉም ቀበሌ የኖሩት ወይዘሮ አብርኸት*ካለፈው ሐምሌ 16/2013 ዓ.ም ጀምሮ በቀበሌዋ ነዋሪ በሆኑ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ይላሉ።

ገንዘባቸውና ንብረታቸው በታጣቂዎች ስለተወሰደ ህይወታቸውን ለማትረፍ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውን ይዘው ዋሻ ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

"መቀነቴ ላይ ቋጥሬው የነበረውን ትንሽ ገንዘብ ሰጠኋቸው፤ ንብረቴንም ወረሱት። አሁን ሁለት ልጆቼና ሁለት የልጅ ልጆቼን ይዤ ዋሻ ውስጥ እየኖርኩ ነው" ይላሉ።

ወይዘሮ አብርኸት ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ የአካባቢው ሕዝብ ንብረቱና ከብቶቹ እንደተወሰዱና ዳግም ሐምሌ ወር ላይ አዲስ ጥቃትና ዝርፊያ እንዳጋጠመው ይናገራሉ።

የ58 ዓመት ጎልማሳ የሆኑት አቶ አብርሃ ነዋሪነታቸው አደባይ ከተማ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ነበር የሚሉት አቶ አብርሃ፣ ከሐምሌ 21 ጀምሮ ደግሞ ታጣቂዎች እናቶችን አፍነው ጠመንጃ ደቅነው ገንዘብና ወርቅ አምጡ እያሉ ያሰቃያሉ ብለዋል።

አቶ አብርሃ በአምስት ታጣቂዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው እና እንደተዘረፉ ለአካባቢው አስተዳደር ቢያሳውቁም መፍትሄ አለማግኘታቸው ገልጸዋል።

ቄስ ኃይላይ የተባሉ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ፣ ከብቶቻቸውና 50 ሺ ብር እንደተወሰደባቸው በመግለጽ፣ በሑመራ ከተማ ለአምስት ቀናት መታሰራቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪ ንብረቱ እየተሰረቀና እየተገደለ ነው ብለው የሚናገሩት ቄስ ኃይላይ ከአካባቢው መልቀቅ ፈልገው የአማራ ክልል ሚሊሻዎች እንደከለከሏቸው ገልጸዋል።

ወደ አስተዳደር ቢሮ ስሄድ "ስንፈልግህ የነበረው አንተን ነው ብለው ደበደቡኝ፤ በኪሴ የነበረውን 5500 ብር እና ስልክ በመውሰድ ካድሬ ስለሆንክ 'ገንዘብ አምጣ' ብሎ አንዱ በቢላ ሊያጠቃኝ ሲል ሌላኛው 'ተወው' ብሎ እጄን ወደ ኋላ አስረው ከሌሎች ዘጠኝ ሰዎች ጋር ከአደባይ ወደ ሑመራ ወሰዱን" ብለዋል።

የአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ግን "በአማራ ክልል መንግሥት የተያዘ ምዕራብ ትግራይ የሚባል ቦታ አላውቅም" በማለት አካባቢዎቹ ላይ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ስለደረሰ ጥቃት መረጃ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል።

"በማንነቴ ምክንያት ንብረቴ ተሰረቀ፣ ጥቃት ደረሰብኝ የሚል ሰው ካለ ወደ እኔ መጥቶ ማመልከት ይችላል። ሕግ በሚፈቅደው መሰረትም እርምጃ እንወስዳለን። እስከ አሁን ግን በዚህ ጉዳይ የቀረበልኝ መረጃ ወይ ክስ የለም" ብለዋል።

እስርና ዘረፋ

በሑመራ፣ እድሪስና አደባይ ከተሞች በጅምላ የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች እንዳሉ፣ ልጆቻችን እና ሚስቶቻችን ጾታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው ንብረታችን እየተዘረፈ ነው፣ እርዳታም እየደረሰን አይደለም የሚሉ የትግራይ ተወላጆች በርካታ ናቸው።

አቶ ሐጎስ የአደባይ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

"በከተማዋ ብዙ ሰው እየተሰቃየ ነው፤ ሃብታሞች ተገድለዋል። ለአንዳንዶቹም አስክሬን ወደ አለበት ቦታ በመውሰድ እስከ 300 ሺ ብር ካልከፈላችሁ እንደዚህ እንገድላችኋለን እያሉ ያስፈራሯቸዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ስለሚደርስባቸው ችግር የአካባቢው አስተዳደር ስለማይሰማን በሚል አካባቢው ላይ ለሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች መናገራቸውን አቶ ሐጎስ ይናገራሉ።

ችግሩን ለመፍታት ሲሞክሩ ግን የአማራ ክልል ታጣቂዎች "አይመለከታችሁም" ይሏቸዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ በተጠቀሱት አካባቢዎች እንደዚህ አይነት ግፍ ተፈጽሟል የሚባለው ሐሰት እንደሆነ እና ወደ ቢሮው ያመለከተ ሰው እንደሌለ ይገልጻሉ።

"የትግራይ ሕዝብ በወልቃይትና ሑመራ ብቻ አይደለም የሚኖረው፤ በአዲስ አበባ፣ በጎንደርና በባሕር ዳርም ይኖራል" ሲሉም ይሞግታሉ።

በሌላም በኩል የምዕራብ ትግራይ ነዋሪዎች ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።

የ14 ዓመት ታዳጊ የሆነችው ቤቴልሄም በሑመራ ከተማ ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም በሦስት ታጣቂዎች እንደተደፈረችና ከሁለት ቀን በኋላ ወላጆችዋ መንገድ ላይ ወድቃ እንዳገኟት ገልጻለች።

በጊዜው ህክምና አለማግኘቷንና አሁን መንቀሳቀስ እንደማትችል ትናገራለች።

አቶ በሪሁ አይኔ እያየ ታዳጊ ልጄ ተደፍራለች ይላሉ።

"ሐምሌ 19 ማታ አራት ሰዓት መጥተው መጀመሪያ ገንዘብ አምጡ ብለው ደበደቡን። ገንዘብ ስላልነበረን ሞባይልና ሌሎች ንብረቶች ወሰዱ። ከቤተሰቦቼ ጋር ቤት ውስጥ እያለሁም ሚስቴን አሰሯት። እኔ ከቤት አስውጡኝ፤ ከዚያ የ15 ዓመት ልጄን ደፈሩብኝ" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ ህይወታቸውን ለማዳን ሰባት የቤተሰብ አባላታቸውን ይዘው ተደብቀው እንዳሉ ገልጸዋል።

*ታሪኩ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል።