ደቡብ ኦሞ፡ ስለ ሙርሲዎች ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ የሰነደው ጥናት

ሙርሲዎች

የፎቶው ባለመብት, Hailemeskel Simache

ፍሬው ግርማ (ዶ/ር) የሥነ ልሳን ምሁር ናቸው። በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች አስተምረዋል።

አሁን ደግሞ ጂንካ ዩኒቨርስቲ የሙሉ ጊዜ ተመራማሪ ናቸው። የዶክተሬት ዲግሪያቸውን በአውስትራሊያ ጄምስ ኩክ ዩኒቨርስቲ ሰርተዋል።

ሙርሲዎች ግን ሲጠሯቸው ራሳቸው ባወጡላቸው ስም ኦሊ ቻጊ በማለት ነው።

ፍሬው ግርማ ዶ/ር ጥናታቸውን ለመስራት ከሙርሲዎች ጋር ሲኖሩ ቤተሰብ ማፍራታቸውን እና ስሙም ከዚያ በኋላ እንደወጣላቸው ይናገራሉ።

ለሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጄምስ ኩክ ዩኒቨርስቲ በሚማሩበት ወቅት በብራዚል አማዞን አካባቢ በሚኖሩ ሕዝቦች ላይ ጥናታቸውን እንዲሰሩ ሃሳብ ቀርቦላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

በመቀጠልም በፓፓዋ ኒው ጊኒ በሚገኙ ሕዝቦች ቋንቋ ላይ ጥናታቸውን እንዲሰሩ ተጠይቀው ነበር።

በፓፓዋ ኒው ጊኒ ከ850 በላይ ቋንቋዎች እንደሚነገርባት የሚገልጹት ፍሬው (ዶ/ር)፣ በዚያ በሚገኝ እና አነስተኛ ቁጥር ተናጋሪ ያላቸው እንዲሁም ሊጠፉ የተቃረቡ ቋንቋዎች እና ባህሎች ላይ እንዲሰሩ ቢጠየቁም አልተቀበሉትም።

ከዚያ ይልቅ ግን በደቡበን ክልል ውስጥ በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ ሕዝቦች ላይ ትኩረታቸውን ማድረጋቸውን እና ወደ ሙርሲዎች ዘንድ ማምራታቸውን ይናገራሉ።

የሙርሲ ቋንቋ ሰዋሰው

በቅርቡ በሙርሲዎች ቋንቋ ላይ ያተኮረ 'የሙርሲ ቋንቋ ሰዋሰው' የተሰኘ መጽሐፍ ለገበያ በቅቷል።

መጽሐፉ የሙርሲ ቋንቋ ሰዋስው 'A Grammar of Mursi' የተሰኘ ሲሆን በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና መምህር በሆኑት ፍሬው ግርማ (ዶ/ር) የተፃፈ ነው።

ወደ ሰባት መቶ የሚጠጋ ገጽ ያለው የመጽሐፉ ዝግጅት አምስት ዓመታት እንደወሰደባቸው በመግለጽ አራቱን ዓመታት ለዶክተሬት ዲግሪያቸው ማሟያ፣ አንዱን ዓመት ደግሞ ወደ መጽሐፍ ለመቀየር መጠቀማቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የመጽሐፉ የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ ሙርሲዎች ታሪክ፣ አኗኗር፣ ባህላዊ አስተዳደር እና ፍልስፍና የሚገልጽ ሲሆን ቀሪዎቹ ምዕራፎች በሙርሲዎች ቋንቋ ሰዋስው ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ፍሬው ግርማ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

"ይህ መጽሐፍ ለሙርሲ ሕዝብ ታሪኩ ብቻ ሳይሆን ቅርሱ ነው" የሚሉት ፍሬው ግርማ (ዶ/ር)፣ መጽሐፉ የሙርሲዎችን ሥርዓተ ጽህፈት ለመቅረፅ፣ መደበኛ ትምህርት በሙርሲዎች ለማስጀመር፣ የቋንቋውን መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት ያገለግላል ሲሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አብራርተዋል።

በተለይም ለትምህርት ባለሙያዎች፣ ለታሪክ ፀሐፊዎች፣ ለጎብኚዎች፣ ለተማሪዎች በማጠቀሻነት እንደሚያገለግልም ገልፀዋል።

እንዲህ ዓይነት የተደራጁ ጥናቶች በአግባቡ ተሰንደው ለመላው ዓለም እንዲደርሱ ማስቻል አነስተኛ ተናጋሪ ባላቸው ቋንቋዎች በራሱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ምሁሩ ጨምረው ያብራራሉ።

ፀሐፊው ከመጽሐፋቸው ሦስቱን ቅጂ ለጂንካ ዩኒቨርሲቲ እና አንድ ደግሞ ለደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል ማበርከታቸውንም ገልፀውልናል።

በእንግሊዝኛ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ፤ ብሪል የተባለ የኔዘርላንድስ አሳታሚ ድርጅት በ139 ዶላር በአውሮፓ ለገበያ አቅርቦታል።

አሳታሚው በማኅበራዊ ሳይንስ፣ በሥነ ልሳን፣ በሕግ፣ በሥነ ሰብ እንዲሁም በሥነ ሕይወት መስኮች የሚሰሩ ጥናቶችን ሲያሳትም ከ300 ዓመታት በላይ ልምድ ማካበቱን አክለው ተናግረዋል።

ፍሬው (ዶ/ር) በጥናታቸው ዙሪያ ከ10 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በአውስትራሊያ እና ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ማቅረባቸውን በዘርፉ አሉ የተባሉ ምሁራንም ጥናታቸውን መገምገማቸውን ያስረዳሉ።

ፍሬው (ዶ/ር) አክለውም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙ ቋንቋዎች መካከል በኤርቦሬ ቋንቋ እና ባህል ላይ ያተኮረ ሌላ ሥራ ለማቅረብ ከጂንካ ዩኒቨርስቲ ጋር እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Firew Girma

'የሙርሲ ቋንቋ በዓለም ላይ እጅግ ጥቂት ቋንቋዎች ብቻ ያላቸውን ባህርያት ይዟል'

ደቡብ ኦሞ በብዝሃ ባህልነት እና ቋንቋዎች ስብጥር የሚታወቅ መሆኑን የሚናገሩት ፍሬው ግርማ (ዶ/ር)፣ ከቋንቋ ቤተሰቦች ረገድም ሦስቱ በዚሁ ዞን እንደሚነገሩ ገልፀዋል።

በደቡብ ኦሞ አካባቢ ብቻ ኩሽ፣ ናይሎ ሳህራዊ፣ ኦሞቲክ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደቡ ቋንቋዎች ይነገራሉ።

የፍሬው ግርማ (ዶ/ር) ጥናት ትኩረት የሆነው ሙርሲ ቋንቋ ደግሞ ከናይሎ ሳህራዊ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ነው።

"ከሥነ ልሳን አንጻር ከታየ ስብጥሩ እጅጉን ይገርማል" ይላሉ ፍሬው ግርማ (ዶ/ር)። የሙርሲ ቋንቋ በዓለም ላይ እጅግ ጥቂት ቋንቋዎች ብቻ ያላቸውን ባህርያትን ይዟል ሲሉም ያክላሉ።

እንዲሁም "ሙርሲ ቋንቋ ለየት የሚያደርገው እጅግ ውስብስብ የድምጽ እና የድምጸት ሥርዓት አለው" ሲሉ ይናገራሉ። በተጨማሪም ውስብስብ የሆነ የቃላት አረባብ፣ አገነባብ፣ አመሰራረት እንዳለው ያብራራሉ።

ፍሬው ግርማ (ዶ/ር) የደቡብ ኦሞ ዞን 16 ብሔረሰቦች የሚገኙበት እና የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በአንድ ውስን ስፍራ በስብጥር የሚኖሩበት መሆኑን በመጥቀስ በዚህ የተነሳ በዓለምም ሆነ በአፍሪካ ልዩ ያደርገዋል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Hailemeskel Simache

የሙርሲ ቋንቋን የፊደል ገበታ ማጠናከር

በሙርሲ፣ በማኪ መንደር ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ የሚያስተምር አንድ ትምህርት ቤት ብቻ መኖሩን ፍሬው ግርማ (ዶ/ር) በጥናታቸው ላይ ጠቅሰዋል።

በዚህ ትምህርት ቤት የሙርሲ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶችን ይማራሉ።

እኤአ እስከ 1989 ድረስ የሙርሲ ቋንቋ ወደ ጽሑፍ ቋንቋነት አልተሸጋገረም ነበር።

በ1989 የኤስ አይ ኤም ሚሲዮናውያን የአማርኛ የፊደል ገበታን በመጠቀም ቋንቋው የራሱ የጽህፈት ሥርዓት እንዲኖረው አደረጉ።

ይህንን ተከትሎም እኤአ በ2005 በላቲን ቋንቋ ፊደል ገበታ ያዘጋጁ ምሁራን መኖራቸውን የፍሬው ግርማ (ዶ/ር) ጥናት ያሳያል።

ፍሬው ግርማ (ዶ/ር) በእርግጥ ተማሪዎች አሁን ይህንን የፊደል ገበታ እየጻፉበት ቢሆንም መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ይጠቁማሉ።

ያሉትን የቋንቋውን ድምጾች በሳይንሳዊ መልኩ እንዲወክሉ ተደርጎ መቅረፍ እንደሚቻልም ያሰምሩበታል። ይህ ግን "ፖለቲካዊ ውሳኔ" እንደሚጠይቅ ሳይገልጹ አላለፉም።

የፎቶው ባለመብት, Gianni GIANSANTI

የምስሉ መግለጫ,

ሙርሲዎች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ አርብቶ አደር ናቸው።

ትንሽ ስለ ሙርሲዎች

ሙርሲዎች በቁጥር ብዙ አይደሉም። የኢትዮጵያ ስታትስቲክ ባለስልጣን መረጃ 7 ሺህ 500 መሆናቸውን ሲገልጽ፣ ዶ/ር ፍሬው ደግሞ 10 ሺህ ገደማ ናቸው ብለው ይገምታሉ።

መኖሪያቸው ደቡብ ኦሞ ነው። ከቦዲዎች፣ ኛንጋቶም፣ አሪ፣ ሀመር፣ ዲሜ እና ባጫ ጋር ይጎራበታሉ።

የኦሞ እና ማጎ ወንዞች በዙሪያቸው ሲፈሱ፣ በእነዚሁ ወንዞች የተሰየሙት ብሔራዊ ፓርኮችም ከብበዋቸዋል።

የኑሯቸው መሰረት አርብቶ አደርነት ነው።

አብዛኛው ከተሜ ሙርሲዎች የሚያውቃቸው ከንፈር ተልትሎ በማስጌጥ ልማዳቸው እንዲሁም በዶንጋ ግጥሚያቸው ነው።

ሴቶቻቸው ከንፈር እና ጆሮ ተልትሎ ሸክላ በማስገባት የማጌጥ ምርጫን የመፈፀም ወይንም ያለመፈፀም ፈቃድ አላቸው። እምቢኝ፤ አልፈልግም ካለች የሚያስገድዳት አካል አይኖርም።

ሙርሲዎች ሲንቀሳቀሱ ከእጃቸው 'ዶንጋ' አይጠፋም፤ ወደ አማርኛ ስንመልሰው በትር እንደ ማለት ነው።

ወደ ባህላዊ ልማዱ ስንወስደው ደግሞ በወጣት ወንዶች መካከል፣ በዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ ግጥሚያ ነው።

በእርግጥ ብዙ አልተነገረለትም እንጂ የሙርሲ ልጃገረዶች ጥንካሬያቸውን የሚፈትሹበት የግጥሚያ ልማድም አለ-'ኡላ' ይሰኛል።

ወንዶቹ ለዚሁ ግጥሚያ ተብሎ በተዘጋጀ በትር ሲፋለሙ፣ ሴቶቹ ደግሞ በእጅ አንባራቸው በመጋጠም የጥንካሬያቸውን መጠን ይፈታተሻሉ።

የሙርሲዎች ማህበራዊ ሕይወት መልክ

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከ1896 ጀምሮ ከአውሮፓ ተነስተው የመጡ ጂኦግራፈሮች፣ አንትሮፖሎጂስቶች እና አሳሾች፣ የኦሞን ወንዝን ተከትለው እስከ ቱርካና እና ሶማሊያ ድረስ አሰሳ ማድረጋቸውን ዶ/ር ፍሬው ያነሳሉ።

እነዚህ አሳሾች ሙርሲዎችን እግረ መንገዳቸውን እያዩ የተለያዩ ማስታወሻዎችን ትተው አልፈዋል።

በእነዚህ ሰነዶች መሰረት ሙርሲዎች ከማጂ አካባቢ መምጣታቸውን ሰፍሯል።

ሙርሲዎች አሁን ወዳሉበት አካባቢ እንዴት መጥተው እንደ ሰፈሩ የሚናገሩት አፈ ታሪክ፣ ከመጽሐፍ ቅዱሱ የሙሴ ታሪክ ጋር ይመሳሰላል።

የፎቶው ባለመብት, Firew Girma (PHD)

ሙሴ ቀይ ባሕርን ከፍሎ እስራኤላውያንን እንዳሻገረው፣ እነርሱም 'ካዉሎ ኾሮ' ሲሉ የሚጠሩት ጀግናቸው የኦሞን ወንዝ እንዲያቋርጡ እንደረዳቸው ይናገራሉ።

ሙሴ ቀይ ባህርን በትር ጥሎ ከፈለ፣ ካውሎ ኾሮም ልክ እንዲሁ የኦሞን ወንዝ በመክፈል ሙርሲዎችን አሻገረ።

የዛሬዎቹ ሙርሲዎች አሁን የሚገኙበት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት፣ ሦስት ትልልቅ ፍልሰቶችን ማካሄዳቸውን ምሁሩ ያስረዳሉ።

በታሪካቸው ሰነድ መሰረት የመጀመሪያውን ፍልሰት ያካሄዱት በ19ኛው ክፍለ ዘመን መካከለኛ ላይ ነው።

መነሻቸውም ከሱዳን ጋር ከሚዋሰነው የኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ አካባቢ መሆኑ ይነገራል።

ሁለተኛው ፍልሰት እኤአ በ1920ዎቹ፣ ሦስተኛው ደግሞ በ1970ዎቹ ውስጥ ያካሄዱት ነው።

ሙርሲዎች አራት ተጠሪዎች ወይንም ባላባቶች አሏቸው።

እነዚህ ባላባቶች፣ ሙርሲዎች በዋናነት በሚገኙበት ከተማ፣ ማኪ፣ ጥንት ሙርሲዎች ኦሞን እንደተሻገሩ የሰፈሩበት ስፍራ፣ ዶንጎሶ፤ ሞይዞ እና ቦንጎዞ ላይ መቀመጫቸውን አድርገዋል።

በአራቱም ስፍራዎች ባላባቶች ቢኖሩም ዋናው ባላባት ግን የሚኖሩት ማኪ ላይ ነው።

እነዚህ ከተለያየ ጎሳ የተውታጡት ባላባቶቹ የተለያየ የሥራ ድርሻ አላቸው።

ሕልም የሚፈታ፣ ባህላዊ ሥርዓት የሚያዘጋጅ፣ የሚመርቅ፣ ዝናብ ሲጠፋ እንዲሁም የሙርሲ ሕዝብ እና እንስሳት በተለያዩ በሽታዎች እንዳይጠቁ የሚለማመኑ ብሎም የሚባርኩ ናቸው።

በእያንዳንዱ ሙርሲ ሕይወት ውስጥ እጅግ ጠቃሚ የሆነው ክፍል ጋብቻ ነው።

ይህ ግን ሊሳካ የሚችለው ለምትታጨው ልጃገረድ ቤተሰብ፣ 37 ከብቶችን በስጦታ መስጠት ሲቻል ብቻ መሆኑን ፍሬው (ዶ/ር) ይናገራሉ።