የአእምሮ ጤና፡ 'ማንኛውም ሰው የአእምሮ ጤና መታወክ ሊገጥመው ይችላል'

ዶ/ር ዮናስ ላቀው

የፎቶው ባለመብት, Dr. Yonas

በኢትዮጵያ ብቸኛ በሆነው የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሰሩት ዶ/ር ዮናስ ላቀው ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ በርካታ አሉታዊ አመለካከቶች እዚህም እዚያም ሲነገሩ አስተውለዋል።

አሉታዊ አመለካከቶቹ ሆስፒታሉ መጥተው ሕክምና በሚያገኙ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ታክመው ከሄዱ በኋላም የሚቀጥሉ በመሆናቸው ግለሰቦቹን ለማግለልና ለመድልዎ ማጋለጡን የታካሚዎቻቸውን ታሪክ በመጥቀስ ያስረዳሉ።

በሆስፒታሉ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ላይም የሚነገሩ እና እነርሱንም የአእምሮ ሕሙም አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያም አስተውለዋል።

ይህንን እና ሌሎች ምልከታዎቻቸውን በ171 የመጽሐፍ ገጾች ውስጥ አሰናድተው ለአንባቢ አብቅተዋል።

በአማኑኤል ሆስፒታል ከሦስት ዓመት በላይ እየሰሩ የሚገኙት ዶ/ር ዮናስ ላቀው "የአማኑኤል ሆስፒታል ታሪኮች" ይሰኛል መጽሐፋቸው።

ዶ/ር ዮናስ መጽሐፍ ለማሳተም አዲስ አይደሉም። ከዚህ ቀደም ሁለት የትርጉም ሥራዎችን ማሳተማቸውን ከቢቢሲጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ያሳተሟቸው መጻህፍት 'ቀላሉን ነገር አታካብድ' እና 'አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች' ይሰኛሉ።

'በአማኑኤል ሆስፒታል ብዙ የሚገመቱ እና ብዙ ደግሞ ማይገመቱ ነገሮች ይከሰታሉ'

ዶ/ር ዮናስ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ አማኑኤል ሆስፒታል በተደጋጋሚ ሲነገሩ ያደመጧቸው ነገሮች ተመሳሳይ እና በተለይ ደግሞ "በአእምሮ ሕሙማን ላይ ማግለልና መድልዎ የሚያደርሱ ናቸው" ሲሉ ትዝብታቸውን ይናገራሉ።

'የአማኑኤል መድኃኒት ያጀዝባል፣ አማኑኤል ሆስፒታል የሚሰሩ ሐኪሞቹ ራሳቸው ያማቸዋል' ከሚሉት ጀምሮ በሕሙማኑ ዙሪያ ፈገግታን ለማጫር ተብለው የሚነገሩ በርካታ ቀልዶችን ያስታውሳሉ።

እነዚህ እውነታውን አያሳዩም የሚሉት ዶ/ር ዮናስ "በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ በየዕለቱ በሥራችን የሚገጥመን የሰዎች ወድቆ መነሳት፣ የሰዎች ቤተሰባዊ ፍቅር፣ እናቶች ለልጃቸው የሚከፍሉትን ዋጋ፣ ጽናት፣ ተስፋ የመሳሰሉ ነገሮች ናቸው።"

የአእምሮ ሕመም ሲባል ልብስን አወላልቆ፣ መንገድ ላይ መሮጥ የሚመስለው በርካታ ሰው መኖሩን ዶ/ር ዮናስ ያስረዳሉ።

"ለአንዳንድ ሰው እንዲያውም ይህም በቂ አይደለም፤ ልብሱን አውልቆ እየሮጠ መኪና ሲመጣ ከሸሸ የእውነት አሞት ቢሆን አይሸሽም ነበር፤ . . . አልታመመም አውቆ ነው" የሚሉ ሰዎች መኖራቸውንም ታዝበዋል።

"እንዲህ ዓይነት የአእምሮ ሕመም ያላቸው ሰዎች ከመቶ ሁለት በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው" የሚሉት ዶ/ር ዮናስ ቀሪው በአግባቡ ለብሶ፣ በሥራ ገበታው ላይ የሚገኝ፣ ተከራይቶ የሚኖር፣ የተለያየ ማኅበራዊ ግዴታውን ያለማስተጓጎል በአግባቡ የሚወጣ ነገር ግን በተለያየ የአእምሮ ሕመም የሚቸገር መሆኑን ያብራራሉ።

የአእምሮ ሕመም ሲባል በፍጥነት ወደ አእምሮ የሚመጣው "ጨርቅ ጥሎ ጎዳና መውጣት" የሚለው አስተሳሰብ ስለሚመጣ ማንም ሰው በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም አይመጣም ሲሉ ሰርጾ የኖረው የተሳሳተ አመለካከት የፈጠረውን ክፍተት ያስረዳሉ።

"99 በመቶ ጨርቁን ያልጣለ አእምሮ ሕመምተኛ ይበዛል።"

አእምሮ መታመም ራስን ከመሳት ጋር እንደማይገናኝ በመግለጽም፣ ይህ ሰዎች እንዳይታከሙ አንደኛው ተግዳሮት መሆኑን በመግለጽ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Dr. Yonas

የትኛውም ሰው የአእምሮ ጤና መታወክ ይገጥመዋል

"አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ ሊታመም ይችላል" የሚሉት ዶ/ር ዮናስ የአእምሮ ሕመም የተለያዩ መልኮችን በመጽሐፉ ውስጥ ለማሳየት ታሪኮችን ማቅረባቸውን ይናገራሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ጥናት ከአራት ሰው አንዱ በአእምሮ ሕመም ጤናው ይታወካል የሚሉት ዶ/ር ዮናስ ይህ በኢትዮጵያም ውስጥ ተመሳሳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በአማኑኤል ሆስፒታል ከ200 በላይ አልጋዎች መኖራቸውን እንዲሁም የተለያዩ አእምሮን ማከም የሚያስችሉ የተደራጁ ክፍሎች እንዳሉ ገልፀዋል።

አማኑኤል ሆስፒታል፣ የሁሉም የእምነት ተከታዮች፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ድረስ መጥተው የሚታከሙበት ተቋም መሆኑን ዶ/ር ዮናስ ይናገራሉ።

የህክምና ባለሙያዎች ሆነው የአእምሮ ጤና ችግር የሚገጥማቸው መኖራቸውንም ዶ/ር ዮናስ ያነሳሉ።

ሰዎች አእምሮ ውስጥ 'ጨርቁን የጣለ' የሚለው አመለካከት በመኖሩ እንጂ ከ300 በላይ የአእምሮ ሕመም ዓይነቶች መኖራቸውን ዶ/ር ዮናስ ያብራራሉ።

አንዳንዶቹን የአእምሮ ሕመም መሆናቸውን ብዙ ሰው እንደማያውቃቸው በመግለጽ "መኮላተፍ፣ መንተባተብ፣ ሂሳብ ትምህርቶችን ለመቀበል መቸገር፣ አልጋ ላይ መሽናት፣ የተለያዩ ዓይነት የሰብዕና ችግሮች፣ ሱስ፣ ጭንቀት፣ የመርሳት ችግር፣ ጭንቀት፣ ስንፈተ ወሲብ ወዘተ" አእምሮ ጤና ችግሮች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ዝርዝሩ እየረዘመ ሲሄድ ከምናቃቸው ሰዎች መካከል ምን ያህሉ ሰው በዚህ ሕመም ይቸገራል ብሎ ማስላት ጉዳዩ ወደ ቤተሰባችን፣ ባልደረቦቻችን እና ጓደኞቻችን የቀረበ መሆኑን እንገነዘባለን። በዚህም በርካታ ሰዎች በተለያየ የአእምሮ ጤና መታወክ እንደሚቸገሩ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ይላሉ።

ሱስ እና የአእምሮ ሕመም

ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ከሚመጡ ሰዎች መካከል በርካታ ሰዎች ከሕመማቸው በተጓዳኝ የአልኮል፣ የጫት፣ የሲጋራ፣ የካናቢስ ሱስ እንዳለባቸው ዶ/ር ዮናስ ይናገራሉ።

"ሱስ ለብቻው የአእምሮ ህመም ነው" የሚሉት ዶ/ር ዮናስ፣ በርካታ ሱስ አምጪ ነገሮች መኖራቸው ከግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበት ያነሳሉ።

ሱስ በራሱ የአእምሮ ሕመም ከመሆኑ ባሻገር ሌሎች የአእምሮ ህመሞችን የመቀስቀስ፣ የማባባስ ጉልበትም አለው።

"ከቡና ሱስ ጀምሮ ጠንከር ወዳሉ ሱስ አስያዥ ነገሮች ሲኬድም እንደ አልኮል፣ ሲጋራ፣ ጫት፣ በመርፌ የሚወሰዱ አደንዛዥ ዕጾች ሄሮይን፣ ኮኬይን የመሳሰሉት ወደ ሕክምና ሲመጣ ደግሞ ለሕመም ማስታገሻ ተብለው የሚሰጡ መድኃኒቶች፣ ለእንቅልፍ የሚሰጡ መድኃኒቶች ሱስ ሆነው በየቀኑ እርሱን ሳይወስዱ መንቀሳቀስ አለመቻል" በራሱ የአእምሮ ሕመም መሆኑን ይናገራሉ።

ሱስ አብዛኛውን ጊዜ የሚጀመረው በአቻ ግፊት፣ ሱስ አስያዝ ነገሮች በአካባቢ በቀላሉ ሲገኙ፣ መሆኑን የሚያስረዱት ዶ/ር ዮናስ ". . .ከቁጥጥራቸው ውጪ ሲወጣ እና ማኅበራዊ ግንኙነትን፣ የሥራን፣ የቤተሰብ ኃላፊነትን እየሸፈነ ሲመጣ ወደ ሱስነት አድጓል እንላለን።"

ወደ አማኑኤል ሆስፒታል መጥተው ሕክምና ያገኙ እና ጤናቸው የተመለሰ ሰዎች በድጋሚ ሱስ ውስጥ ገብተው ሕመማቸው ሲያገረሽ መመልከታቸውንም ዶ/ር ዮናስ ያስታውሳሉ።

ከዚህ በፊት ወደ አማኑኤል የሚመጡ ታካሚዎችን በመርፌ የሚወሰዱ አደንዛዥ ዕጾችን እንደሚጠቀሙ እንደማይጠየቅ የሚናገሩት ዶ/ር ዩናስ አሁን ግን መጠየቅ መጀመሩን ይገልጻሉ።

ለዚህም ምክንያታቸውን በአስረጅ ሲያስደግፉ፣ "በቅርቡ የጥቁር አንበሳ ኢፒዲሞሎጂስቶች በሰሩት ጥናት በአዲስ አበባ ብቻ 4000 ሰዎች በመርፌ የሚወሰዱ አደንዛዥ ዕጾች ይጠቀማሉ" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Dr. Yonas

የአእምሮ ሕመም መገለል እና መድል

የአእምሮ ሕመም ገጥሟቸው ታክመው የዳኑ ሰዎች ሕክምና ማስረጃቸውን ለሚሰሩበት ተቋም ሲያስገቡ ከዚያ በኋላ አስተያየት ሲሰጡ፣ አማራጭ ሃሳብ፣ የሚሰማቸውን ቅሬታ ሲያቀርቡ በተደጋጋሚ ለመገለልና መድልዎ ይጋለጣሉ።

ምንም የማይናገሩ ከሆነ ግን አንዳች ችግር ሳይገጥማቸው ህይወታቸውን እንደሚቀጥሉ ዶ/ር ዮናስ ያነሳሉ።

በአእምሮ ሕሙማን ላይ በሚደርስ መገለል እና መድልዎ የተነሳ ሕሙማኑ ወደ ሕክምና ተቋም እንዳይመጡ እንደሚያደርግ ዶ/ር ዩናስ ይናገራሉ።

ለዚህም ማሳያነት የታካሚያቸውን ታሪክ የሚጠቅሱት ዶ/ር ዮናስ፣ በሆስፒታሉ ታክሞ ከጨረሰ በኋላ የሕክምና ማስረጃ በማጻፍ ለመሥሪያ ቤቱ ማስገባቱን ይናገራሉ።

ከዚህ በኋላ በስብሰባዎች ላይ አስተያየት ሲሰጥ፣ የማይስማማበትን ሲያስረዳ፣ በስብሰባዎች ላይ ሲናገር ከአለቃው ጋር መስማማት አለመቻሉን እንዳጫወታቸው ያስታውሳሉ።

በአለቃው ከአማኑኤል የተሰጠውን የህክምና ማስረጃውን በመጥቀስ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለበት በመግለጽ ለማሸማቀቅ እና ለማግለል መጋለጡን ይናገራሉ።

በአንድ ወቅት የአእምሮ ሕመም ስለነበረባቸው ብቻ የሥራ እድገት የታለፋቸው፣ በዚህ ምክንያት ከሥራ የተባረሩ ሰዎች መኖራቸውንም አክለው ገልፀዋል።

የአእምሮ ሕመም ታክሞ እንደሚድን አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ የአእምሮ ሕመምን ከመንፈስ ጋር ማገናኘት፣ የሚጋባ ነው ብሎ ማሰብ ለማግለልና መድልዎ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ባለሙያው አመልክተዋል።

ሌላው የአእምሮ ሕሙማን ኃይለኛ እና ሰው ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ናቸው ብለው የሚያስቡ ሰዎች እንደሚሸሿቸው እና እንደሚርቋቸው ይገልጻሉ።

እውነታው ግን ይላሉ ዶ/ር ዩናስ የአእምሮ ሕሙማን "ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ስድስት እጥፍ ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑ ነው" በማለት ጥቃቶቹ አካላዊ፣ ጾታዊ እንዲሁም ሥነልቦናዊ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ቤተሰቦችም ቢሆኑ የአእምሮ ሕመም ያለበትን ሰው ከተለያዩ ነገሮች አግልለው ሲያኖሩ ማየታቸውን ያስረዳሉ።

የቤተሰብ መርዶ ሳይነገራቸው የሚቀሩ፣ ከየትኛውም ሥራ ታቅበው ቴሌቪዥን ሲመለከቱ እንዲውሉ የሚደረጉ፣ በተቃራኒው ደግሞ አላስፈላጊ ንግግሮችን የሚናገሯቸው መኖራቸውንም ታዝበዋል።