ታሊባን በካቡል ውስጥ የሴቶች ተቃውሞ ሰልፍን በተነ

ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የታሊባን ኃላፊዎች በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በአስርታት የሚቆጠሩ ሴቶች ስለመብታቸው ለመጠየቅ የወጡትን የተቃውሞ ሰልፍ መበተናቸው ተገልጿል።

ሰልኞቹ በአንድ ድልድይ በኩል አቋርጠው ወደ ፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግስት በመሄድ ላይ ሳሉ ታሊባን አስለቃሽ ጭስና አይን የሚያቃጥል ሌላ ፈሳሽ ጭምር በመጠቀም ሰልፉን ለመበተን ጥረት አድርጓል።

ነገር ግን አንዳንድ የአፍጋኒስታን መገናኛ ብዙሀን እንደሚሉት ታሊባን ተቃውሞውን ሙሉ በሙሉ መበተን አቅቶት እንደነበርና ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንደሆኑ ዘግበዋል።

ከዚህ በፊትም በተለያዩ አጋጣሚዎች የካቡል ሴቶች ተቃውሟቸውን አደባባይ ወጥተው ሲገልጹ ነበር።

ሰልፈኞቹ ሴቶች ስራ የመስራትና በመንግስት መዋቅር ውስጥ የመካተት መብታቸውን በመጠየቅ ነው የተቃወሙት።

ታሊባን ደግሞ አፍጋንን የሚያስተዳድር መንግስት በቅርብ ቀን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ምንም እንኳን ታሊባን ሴቶች በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንደሚካተቱ የገለጸ ቢሆንም በሚኒስትር ደረጃ ግን ማገልገል አይችሉም ብሏል።

ይህን ተከትሎም በርካታ ሴቶች ታሊባን በአውሮፓውያኑ ከ1996 እስከ 2001 ስልጣን ላይ በነበረበት ይከተለው የነበረውን ሴቶች ላይ ያለው አቋም መልሶ እንዳኣመጣ ስጋታቸው እየገለጹ ነው።

በነዚህ ዓመታት ሴቶች ፊታቸውን እንዲሸፍኑ ይገደዱ የነበረ ሲሆን ሕግ ጥሰዋል የተባሉ ሴቶች ደግሞ ከፍተኛ ቅጣት ይጣልባቸው ነበር።

''ከ25 ዓመታት በፊት ታሊባኖች ሲመጡ ወደ ትምህርት ቤት እንዳልሄድ ከልክለውኝ ነበር'' ትላለች ጋዜጠኛዋ አዚታ ናዚሚ።

''ታሊባን ወደስልጣን በመጣ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለ25 ዓመታት በርትቼ ስሰራና ስማር ነበር። ይህን የማደርገው ለአገራችን መጻኤ ተስፋ ነው። ከዚህ በኋላ ይህ ሁኔታ ተመልሶ እንዲመጣ መፍቀድ የለብንም'' ትላለች።

ሌላኛዋ የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ ሶራኣ ለሬውተርስ የዜና ወኪል ስትናገር '' በጥይት ካርታ ጭምር ሴቶችን ጭንቅላታቸው ላይ ይመቷቸው ነበር። ሴቶቹም ደማቸውን እያፈሰሱ ሲጮሁ ነበር'' ብላለች።

በሌላ በኩል መሰል ተቃውሞዎችና ግጭት በፓንጂሺር ቫሊ እንዲሁም የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ተዋጊዎች ሰሜናዊ ካቡልም ቀጥለዋል።

ነገር ግን ታሊባን ግዛቲቱን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ግስጋሴ ስኬታማ እንደሆነና እስካሁንም ተጨማሪ ሁለት አካባቢዎችን መቆጣጠሩን ገልጾ በቅርቡም የግዛቲቱን ማዕከል እንደሚቆጣጠር አስታውቋል።

በግዛቲቱ ከታሊባን ጋር እየተዋጋ የሚገኘው 'ኤንአርኤፍ' በአካባቢው ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነና በሺዎች የሚቆጠሩ የታሊባን ወታደሮች እጃቸውን መስጠታቸውን አስታውቋል።

በፓንጂሺር ቫሊ ከ150 ሺ እስከ 200 ሺ የሚጠጉ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ውስጥ አፍጋኒስታን በሩሲያ ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት የተቃውሞ ማዕከል ነበረች። ታሊባን ስልጣን ከያዘ በኋላም ቢሆን አካባቢው የተቃውሞ መነሻ ነበር።

የኤንአርኤፍ ቃል አቀባይ አህማድ ማሱድ ሄራት ውስጥ ሴቶች ያደረጉትን ተቃውሞ በማድነቅ በፓንጂሺር አሁንም ተቃውሞም ይቀጥላል ብለዋል።

በታሊባንም ሆነ በኤንአርኤፍ በኩል የሚባሉትን ነገሮች በገለልተኛ ወገን በኩል ማረጋገጥ አልተቻለም።