በቤንሻንጉል ጉሙዝ ከሕግ ውጪ የታሰሩ 19 ሴቶች ከነልጆቻቸው እንዲፈቱ ተጠየቀ

የኢሰመኮ አርማ

የፎቶው ባለመብት, EHRC

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከሕግ አግባብ ውጪ 19 ሴቶች ከህፃናት ልጆቻቸው ጭምር መታሰር አሳሳቢ እንደሆነና በአስቸኳይ እንዲፈቱም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ጠየቀ።

ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ እነዚህ ለእስር የተዳረጉት ሴቶች በክልሉ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ባለቤቶች መባሉንም አስፍሯል።

ተጠርጣሪዎቹም የአካባቢውን ጸጥታ ለመመለስ በመተከል ዞን በተቋቋመው ኮማንድ ፖስትና በሚመለከታቸው የዞኑ ባለስልጣናት በመወሰድ ካሉ እርምጃዎች ጋር ተያይዞ የሚፈለጉ እንደሆነም ተገልጿል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በእስር ላይ ለነበሩ ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት ሰጥተዋል ወይም በዋስትና ለቀዋል የተባሉ ሰባት ሰዎች መታሰራቸውን በተመለከተ ግለሰቦቹ የታሰሩት የዋስትና ደንቡን በመጣስ ተጠርጣሪዎቹ መጥፋታቸውን ተከትሎ መሆኑን ከአካባቢው ባለስልጣናት መረዳቱን ኮሚሽኑ አሳውቋል።

በርካታ ጥቃቶች በሚፈጸሙበት በዚህ ክልል የአካበቢውን ጸጥታ ለማረጋገጥ በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ተብሏል።

በተለይም በቅርቡ ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም በዶቢ፣ ቡለን ወረዳ 5 የሚሊሻ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ እርምጃዎቹ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥለዋል ብሏል።

"ነገር ግን በተጠርጣሪዎቹ ፈንታ የተጠርጣሪዎቹን ባለቤቶች ማሰር በሕግ የተከለከለ ነው" መሆኑንም ኢሰመኮ በመግለጫው አስፍሯል።

ኢሰመኮ ጉዳዩን የሚከታተልና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ጋር ውይይቱን እንደሚቀጥል አስታውቆ የታሰሩት ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል።