ሁለቱንም እጆቹን ያጣው ቻይናዊ አራት የፓራ ኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያዎችን ሰበሰበ

ዤንግ ታዎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይናዊው የፓራ ዋናተኛው ዤንግ ታኦ በቶኪዮ ፓራ ኦሎምፒክ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማሸነፉና ክብረ ወሰኖችን መስበሩ በርካቶችን እያስገረመ ይገኛል።

ዤንግ አካል ጉዳተኛ ሲሆን ሁለቱንም እጀቹን አጥቷል።

''ልጄ ተመልከቺ፤ ምንም እንኳን እጆች ባይኖሩኝም በጣም ፈጣን ዋናተኛ ነኝ'' ብሏል ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ ለሴት ልጁ በላከው የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት።

ዤንግ ገና ታዳጊ ሳለ ነበር በኤሌክትሪክ ሾክ ምክንያት ሁለቱንም እጆቹን ያጣው። በቶኪዮ ፓራ ኦሎምፒክ ድሞ በነጻ ቀዘፋ፣ ባክስትሮክ እንዲሁም በተርፍላይ ዘርፎች የበላይነትን መውሰድ ችሏል።

ሁሉም ድሎቹ ደግሞ በዓለም እና በፓራ ኦሎምፒክ ክብረ ወሰን ሆነው ተመዝግበዋል።

ረቡዕ ዕለት በ50 ሜትር ነጻ ቀዘፋ በማሸነፍ የውድድሩን ክብረ ወሰን በእጁ ማስገባት የቻለ ሲሆን ያሸነፈውም የወርቅ ሜዳሊያ ለአገሩ ቻይና በፓራ ኦሎምፒክ ያገኘችው 500ኛ የወርቅ ሜዳሊያ ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህም በርካታ ቻይናውያን በማህበራዊ ሚዲያዎች በኩል ለዤንግ ያላቸውን ክብርና ፍቅር ሲገልጹለት ነበር።

ቻይና የመጀመሪያውን የፓራ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊኦኣ ማግኘት የቻለችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1984 ላይ ኒው ዮርክ ውስጥ በተካሄደው ውድድር ነበር።

ዤንግ ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃል '' ይህ ውድድር የቶኪዮ የመጨረሻዬ ስለሆነ ያለኝን አቅም ሁሉ ሰብስቤ እንዲሁም ያለምንም ቁጭት ነው የተፎካከርኩት። እንደሚመስለኝ በህይወቴ ምርጡ ውድድር ነበር'' ብሏል።

ሰኞ ዕለት ደግሞ ዤንግ በ50 ሜትር የጀርባ ቀዘፋ የፍጻሜ ውድድርን በ31.42 ሰከንዶች በሆነ ሰአት በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችሏል።

ድሉን ተከትሎም ዤንግ ለሁለት ዓመት ሴት ልጁ ባስተላለፈው ስሜታዊ የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት ተከትሎ በርካቶች ማበረታቻና አድናቆታቸውን እያጎረፉለት ይገኛሉ።

ዤንግ ውድድሩን ለመጀመርና በኃይል ለመወርወር ከገንዳው ፊትለፊት ከሚገኝ ብረት ጋት የተያያዘ ፎጣ በጥርሱ በመያዝ የተጠቀመ ሲሆን በርካታ የምህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም ድፍረቱን እና ጥንካሬውን እየገለጹ አድናቆታቸውን አጉርፈውለታል።

አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ዤንግ ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት በየቀኑ የ10 ኪሎሜትር ዋና ያደርግ ነበር።

ገና የ13 ዓመት ታዳጊ ሳለ ወደ ውሃ ዋና ስፖርት የገባው ዤንግ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የጀመረው ደግሞ ከስድስት በኋላ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራ ኦሎምፒክ የተሳተፈው ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2012 በተካሄደው የለንደን ኦሎምፒክ ሲሆን እስካሁን ድረስ ደግሞ 9 ሜዳሊያዎችን ሰብስቧል።