በጊኒ ወታደሮች መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ሥልጣን መያዛቸውን ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Guinea TV
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጊኒ ውስጥ ወታደሮች መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ባለፈው ዓመት በምርጫ ያሸነፉትን ፕሬዝዳንት ከመንበራቸው ማስወገዳቸውን ገለጹ።
ወታደሮቹ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ሥልጣን መቆጣጠራቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ በቴሌቪዥን ከታየ በኋላ ፕሬዝዳንቱ አልፋ ኮንዴ የት እንዳሉ አልታወቀም።
ወታደሮቹ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የአገሪቱን መንግሥት መበተናቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው በወታደሮቹ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት በፕሬዝንዳንቱ ጠባቂዎች አማካይነት ከሽፏል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና የአፍሪካ ሕብረት መፈንቅ መንግሥቱን አጥብቀው ከተቹ በኋላ ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ በአስቸኳይ እንዲላቀቁ ጠይቀዋል።
እሁድ ጠዋት በዋና ከተማዋ ኮናክሪ ውስጥ በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ለሰዓታት የቆየ ከባድ የተኩስ ልውውጥ በኋላ መፈንቅለ መንግሥት መሞከሩ የታወቀው።
በቴሌቪዠን ላይ ቀርበው የመንግሥት ግልበጣ መካሄዱን ያስታወቁት ስማቸው ያልተገለጸና የአገሪቱን ሰንደቅ አላማ በለበሱ በርካታ ወታደሮች የታጀቡ ዘጠኝ ወታደሮች ናቸው።
ወታደሮቹ ለወሰዱት እርምጃ እንደምክንያት የጠቀሱት በአገሪቱ ተንሰራፍቷል ያሉት ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና ድህነት መሆኑን ገልጸዋል።
እራሳቸውን የእርቅና ልማት ብሔራዊ ኮሚቴ ብለው የጠሩት ወታደሮቹ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት መታገዱንና ሁሉን አቀፍ አዲስ ሕገመንግሥት ለማቀርቅ ምክክር እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል።
በርካታ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት የጊኒው መፈንቅለ መንግሥት የተመራው የቀድሞ የአገሪቱ ዋነኛ ወታደራዊ ኃይል መሪ በነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ ነው።
ቢቢሲ ስለትክክለኝነቱ ሊያረጋግጠው ባልቻለ አንድ ቪዲዮ ላይ ወታደሮቹ ፕሬዝዳንት ኮንዴ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው እንዲናገሩ ሲጠይቁና ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ታይተዋል።
በቪዲዮው ላይ ጂንስ ሱሪና ከነቴራ ለብሰው ሶፋ ላይ ተቀምጠው ባዶ እግራቸውን የሚታዩት ፕሬዝዳንቱ በአካላቸው ላይ የደረሰ ጉዳት አይታይም።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጀርባ ያሉት ወታደሮች እንዳሉት የአገሪቱ የአየርና የየብስ ድንበሮች በሙሉ ለአንድ ሳምንት ያህል መዘጋታቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን የጊኒ መከላከያ ሚኒስቴር መፈንቅለ መንግሥቱ በፕሬዝዳንቱ ታማኝ ኃይሎች "በቁጥጥር ስር መዋሉንና ጥቃት ፈጻሚዎቹ ተገፍተው ማፈግፈጋቸውን" አመልክቷል።
ምንጮች ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በርካታ የአገሪቱ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቶችና የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ወደሚገኝበት የከተማዋ ክፍል የሚያደርሰው ብቸኛው ድልድይ ተዘግቶ በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቁ ወታደሮች እየተጠበቀ ነው።
ያልተረጋተጡ ዘገባዎች እንደሚሉት ደግሞ በተኩስ ልውውጡ መካከል ሦስት ወታደሮች መገደላቸውን አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንት ኮንዴ ከባድ ተቃውሞ እየተካሄደ በነበረበት ባለፈው ዓመት በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ተመርጠዋል።
በተፈጥሮ ሀብቷ ባለፀጋ እንደሆነች የሚነገርላት የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ጊኒ ለዓመታት ባጋጠማት አለመረጋጋትና የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት በዓለም ላይ ካሉ ደሃ አገራት መካከል ትገኛለች።