በእስራኤል ጭንቅላታቸው ተጣብቆ የተወለዱ መንትዮች በቀዶ ህክምና ተለያዩ

መንትዮቹ ከሕክምናቸው በኋላ

የፎቶው ባለመብት, SOROKA MEDICAL CENTRE VIA REUTERS

የምስሉ መግለጫ,

ከአንድ ዓመት በፊት የተወለዱት ልጆች ወደፊት ሙሉ በሙሉ መደበኛ ሕይወት ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጭንቅላታቸው ተጣብቆ የተወለዱ የአንድ ዓመት መንትዮች በእስራኤል ያልተለመደ በተባለለት ቀዶ ሕክምና ተለያይተው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመተያየት በቁ።

ባለፈው ሳምንት በቢርሼባ ከተማ በሶሮካ የሕክምና ማዕከል 12 ሰዓታት የፈጀውን ቀዶ ህክምና ለማከናወን የወራት ዝግጅት ተደርጓል።

በደርዘን የሚቆጠሩ የእስራኤል እና የሌሎች ሃገራት ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

በስም ያልተጠቀሱት መንትያ እህትማማቾች ከህክምናው በኋላ በጥሩ ሁኔታ እያገገሙ ነው ተብሏል።

"በራሳቸው እየተነፈሱ እና እየተመገቡ ነው" ሲሉ የሶሮካ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ኤልዳድ ሲልበርስተይን ለእሥራኤሉ ቻናል 12 ተናግረዋል።

በዓለም ላይ 20 ጊዜ ብቻ የተደረገው ይህ መሰል ቀዶ ህክምና በእስራኤል ሲደረግ የመጀመሪያው ነው።

ቀዶ ህክምናው ከመደረጉ ከወራት በፊት የሲሊኮን ከረጢቶች ወደ ጭንቅላታቸው ገብተው በጊዜ ሂደት ቆዳቸው እንዲለጠጥ ተደርጓል። የራስ ቅሎቹ እንደገና ከተሠሩ በኋላ ተጨማሪ ቆዳቸው የራስ ቅላቸውን እንዲሸፍን ጥቅም ላይ ውሏል።

የመንትዮቹ የ 3ዲ ምናባዊ እውነታን የሚያሳይ ዝግጅት መደረጉንም የሶሮካ ዋና የነርቭ ቀዶ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ሚኪ ጊዶን ተናግረዋል ። አክለውም "ደስተኛ ያደረገን ሁሉም ነገር እንዳሰብነው መሆኑ ነው" ብለዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የተወለዱት ልጆች ወደፊት ሙሉ በሙሉ መደበኛ ሕይወት ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።