ምግብ የጫኑ 100 መኪናዎች መቀለ መግባታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ

በትግራይ ሰዎች በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የሚካፋፈል የእርዳ ምግብ ሲወስዱ

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY

የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ 100 የጭነት መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀለ መግባታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

3500 ቶን ይመዝናሉ የተባሉት የጭነት መኪናዎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሕይወት አድን ቁሶችን ጭነው ነው ወደ ክልሉ የገቡት።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከአጋሮቹ ጋር በመጣመር በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በተቻለው መጠን ለሟሟጋዝ እንደሚጥር አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል የነበረው እርዳታ አቅርቦት ከተጠናቀቀ ሁለት ሳምንት እንደሆነ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ግራንት ሌይቲ አስታውቀው ነበር።

አስተባባሪው ባወጡት መግለጫ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ማቅረብ አለመቻሉ፣ የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት መኖሩ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለው ነበር።

በትግራይ ክልል 90 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል፤ 400 ሺህ ያህሉ ደግሞ ረሃብ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ሲሉ አስተባባሪው መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

በአማራ እና አፋር ክልል ደግሞ 1.7 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ሊጋለጡ ከጫፍ ደርሰዋል ብለዋል የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪው።

የሰላም ሚኒስቴር በበኩሉ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ በሁለት ተከታታይ ቀናት 152 የጭነት መኪናዎች እህልና ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ትግራይ ክልል ገብተዋል ብሏል።

እስካሁን ድረስ 500 ገደማ የጭነት መኪናዎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ክልሉ ማቅናታቸውን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማሕበራዊ ድር አምባ ገፁ በለቀቀው መግለጫ ህወሓት በአማራና አፋር ክልል በኩል የእርዳታ መኪናዎች እንዳይጓጓዙ እንቅፋት ሆኗል ሲል ወቅሷል።

ቡድኑ በተደጋጋሚ በአፋርና አማራ ክልሎች በፈፀማቸው ጥቃቶች ምክንያት 4.5 ሚሊዮን ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፤ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ደግሞ ተፈናቅለዋል ይላል ሚኒስቴሩ።

ባለፈው ሳምንት መግለጫው ያወጡት የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ አስተባባሪው ሌይቲ በአፋር በኩል የሚያቀና አንድ መንገድ ብቻ መኖሩን አስታውሰው የሎጂስቲክስ እና ቢሮክራሲው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን ከባድ እንዳደረገው አመልክተው ነበር።

የሰላም ሚኒስቴር በፊት የነበሩት ሰባት የፍተሻ ጣቢያዎች ተቀንሰው ሁለት ሆነዋል ሲል የነበረው መጉላላት በከፊል መቀነሱን አስታውቋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተመጣጣኝ እርዳታ ለማቅብ በየቀኑ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ቁስ እና ነዳጅ የጫኑ 100 ተሸከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባት ቢኖርባቸውም፤ ከዚህ ውስጥ እስካሁን ወደ ክልሉ መግባት የቻለው ዘጠኝ በመቶ ብቻ የሚሆኑ ተሸርካሪዎች ናቸው ብሏል የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም።

የፌደራሉ መንግሥት ወደ ክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ እክል የሆኑት የህወሓት አማጺያን ናቸው ይላል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እርዳታ በተገቢው ሁኔታ እንዳይቀርብ "እንቅፋት እየፈጠረ ያለው ህወሓት በመሆኑ የተደራሽነት ችግር ጥያቄ መነሳት ያለበት ከዚሁ ቡድን አንጻር ነው" ብለው ነበር።

ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት ናቸው የተባሉ አሠራሮች እንዲስተካከሉ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዋናነት ከምግብና የሕክምና ቁሳቁሶች በተጨማሪ ነዳጅና የጥሬ ገንዘብ እጥረት በትግራይ ክልል ትልቅ እክል መሆኑ እየተዘገ ይገኛል።