የታንዛኒያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት የመጀመሪያዋን ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሾሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የታንዛኒያ የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ስቴርጎሜና ታክስ
ከወራት በፊት የታንዛኒያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ሥልጣን የመጡት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሳን የአገሪቱን የመጀመሪያ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር መሾማቸውን አስታወቁ።
የፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊን ድንገተኛ ሞት ተከትሎ የታንዛኒያን የመሪነት መንበር የያዙት ሳሚያ ሱሉሁ እንደ እርሳቸው ሁሉ የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትር ሞት ተከትሎ ነው አዲሷን ሚኒስትር የሾሙት።
አዲሷ የመከላከያ ሚኒስትር ስቴርጎሜና ታክስ በፕሬዝዳንቷ የተሾሙት ቀዳሚያቸው ኤሊያስ ክዋንዲክዋ ባለፈው ነሐሴ ወር ካረፉ በኋላ ነው።
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ለመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሹመት ከመስጠታቸው በተጨማሪ የሌሎች ሦስት የካቢኔ ሚኒስትሮችን ሹመት ያነሱ ሲሆን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሾመዋል።
በፕሬዝዳንቷ ከሥልጣናቸው የተነሱት የኮምዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ፋውስቲን ንዱጉሊሌ፣ ሌዮናርድ ቻሙሪሆ የትራንስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም ሜዳርድ ካሌማኒ የኢነርጂ ሚኒስትር ናቸወ።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንቷ ለአምስት ዓመታት ምክትላቸው ሆነው አብረዋቸው የሰሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ከሥልጣን አንስተዋቸው የነበሩትን ጃንዋሪ ማካምባን መልሰው ወደሥልጣን በማምጣት የአገሪቱ ኢነርጂ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸዋል።
ፕሬዝዳንቷ ዳኛ ኤሊዘር ፌሌሺን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አድርገው በመሾም አምባሳደር የተደረጉትን አዴላረደስ ኪላንጊን እንዲተኩ አድርገዋል።
የመጀመሪያዋ የታንዛኒያ ሴት ፕሬዝደንት የሆኑት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሳን ወደሥልጣን የመጡት ቀዳሚው ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ በልብ ችግር ምክንያት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ነው።
የአገሪቱ ስድስተኛ ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት ፕሬዝዳንት ሳሚያ 61 ዓመታቸው ሲሆን ለአምስት ዓመታት የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።