ጦርነት ያፈናቀላቸው የሠሜን ወሎ እናቶችና ህጻናት ፈተና

ደሴ በሚገኝ አዲስ ፋና ትምህርት ቤት ውስጥ ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ ልጇን እያጠባች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ደሴ በሚገኝ አዲስ ፋና ትምህርት ቤት ውስጥ ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ ልጇን እያጠባች

በሠሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ ሠሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የተዛመተው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ አስገድዷቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች የቀሩ ነዋሪዎች ረሃብን ጨምሮ ለተለያዩ የጤናና የደኅንነት ችግሮች መጋለጣቸው እየተነገረ ነው። ነገር ግን በስፍራዎቹ የነበረው የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ አሁን ያለውን ሁኔታ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ተሰደው የሚገኙት ደቡብ ወሎ ውስጥ በደሴ ከተማና በአካባቢው ነው።

በአሁኑ ጊዜ በከተማው ውስጥ 14 የተፈናቃዮች የመጠለያ ካምፖችና ትምህርት ቤቶች እነዚህን የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች እያስተናገዱ ነው።

በካምፖቹ ውስጥ ከህጻን እስከ አዋቂ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም በርካታ ህጻንት፣ ወላድና ነፍሰጡር እናቶች ይገኛሉ።

የሠሜን ወሎ ዞን የጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት አያሌው ለቢቢሲ እንደተናገሩት በእነዚህ መጠለያዎች ውስጥ ባለፈው አንድ ወር ብቻ ቢያንስ 118 ሴቶች ወልደዋል።

ከሐራ ከተማ ተፈናቅላ በደሴ መጠለያ ውስጥ ከወለዱት 118 እናቶች መካከል ወ/ሮ አያል ሰማው አንዷ ነች። ወ/ሮ አያል ተወልዳ ባደገችበት ሐራ ከተማ ትዳር መስርታ ሦስት ልጆችን አፍርታለች።

በኑሮዋም እርሷ እንዳለችው መካከለኛ የሚባል ሕይወትን ስትመራ ቆይታለች። አራተኛ ልጇን በዚህ ክረምቱ ወቅት ለመቀበል እንደባህሉ ለመታረሻ የሚሆናትን ሁሉ ስታሰናዳ ቆይታለች።

ለመውለድ ሳምንታት ሲቀሯት ግን ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ። የትውልድ መንደሯ የጦር ቀጠና ሆነ። ሁለቱን ልጆቿን አስተዛዝላ፣ የሁለት ዓመት ልጇን ደግሞ ራሷ አዝላ ቤት ንብረቷን ጥላ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ስደት ጀመሩ።

የትራንስፖርት አገልግሎት ሲገኝ ለ15 እና 20 ኪሎ ሜትር መንገድ እስከ 1 ሺህ ብር እየከፈለች ቀሪውን ደግሞ በእግር እየተጓዙ ወ/ሮ አያልና ልጆቿ ደሴ ደርሰዋል።

ከሐራ እስከ ደሴ በነበረው ጉዞ በእጇ የነበረውን ገንዘቧን ስለጨረሰች አልጋ ይዞ ወይም ቤት ተከራይቶ ኑሮን መጀመር ለወ/ሮ አያልና ቤተሰቧ የሚታሰብ አልነበረም። በመሆኑም የመጠለያ ካምፕ ውስጥ መግባት ብቸኛው አማራጭ ነው።

እናም ነፍሰጡሯ ወ/ሮ አያል ሦስት ልጆቿን ይዛ ደሴ ቅዳሜ ገበያ ትምህርት ቤት ውስጥ ወደተዘጋጀው መጠለያ በማምራት አስቸጋሪውን ኑሮዋን ጀመረች።

ወ/ሮ አያል በዚህ መጠያ ካምፕ መኖር በጀመረች በስምንተኛው ቀን የማይቀረው ጉዳይ መጣ፤ ምጥ። በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ተወስዳ አራተኛ ልጇን በሰላም ተገላግላለች።

ነገር ግን አያል ከወለደች በኋላ ራሷን አግልላ የምትታረስበት መጠለያ ስለሌላት የነበራት አማራጭ ወደነበረችበት የመጠለያ ተመልሳ ያለዘመድ አዝማድ እና ያለጎረቤት የአራስነት ጊዜዋን ከነልጆቿ በችግር ውስጥ ሆና እያሳለፈች ነው።

አያል ጨቅላ ልጇን ይዛ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ30 ሰው ጋር መኖር ከጀመረች 15 ቀናት አልፈዋታል። አሁን ያለችበትን ሁኔታ "አላህ ይመስገን፣ የባሰ አያምጣ" የምትለው አያል፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የእርሷንና የቤተሰቧን ሕይወት መትረፍ እንደመልካም አጋጣሚ ብትቆጥረውም፣ አሁንም ግን ስጋት አላት።

"በቂ ምግብም ስለማላገኝና ከ30 ሰው ጋር እየተጋፋሁ ስለምኖር፣ የእኔም የልጆቼም ጤና አሳስቦኛል። የሚሰጡን ዕርዳታም በቂ አይደለም፣ እስከዛሬ ባለችን የተወሰነች ገንዘብ ባለቤቴ እየገዛ ሲያበላኝ ነበር፤ አሁን ግን የነበረን ገንዘብ በማለቁ ችግር ላይ እወድቃለሁ የሚል ስጋት አለኝ" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Dessie City Admin.

ዓለምፀሐይ መኮንንም ከሐብሩ ወረዳ ተፈናቅላ የመጀመሪያ ልጇን በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ተገላግላለች። በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መርሳ ካምፓስ ውስጥ ትሰራ የነበረችው ዓለምፀሐይ፣ ባለቤቷም የመንግሥት ተቀጣሪ በመሆኑ የተሻለ የሚባል ኑሮ ይኖሩ እንደነበር ትናገራለች።

ጦርነቱ አድማሱን አስፍቶ መርሳ ከተማ ጫፍ ላይ ሲደርስ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ለመውለድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ነበር የቀሯት።

ጦርነቱ ጊዜያዊና ወዲያው መፍትሄ የሚያገኝ ችግር መስሏት ስለነበር ለመታረሻ ካሰናዳቸው በርካታ ዝግጅት መካከል አንዱንም ሳትይዝ፤ ችግሩን ለማምለጥ ከባለቤቷና ከበሽተኛ እናቷ ጋር በመሆን ወደ ደሴ ከተማ አቀኑ።

ደሴ በደረሰች በሦስተኛው ቀን ምጧ መጥቶ ዓለምጸሐይ የመጀመሪያ ወንድ ልጇን ተገላገለች። "ይህንን ሳስብ እንባዬ ይመጣል፣ የመጀመሪያዬ በመሆኑ በጥሩ ሁኔታ ለመታረስ በእርግዝናዬ ወቅት ብዙ ነገር አዘጋጅቼ ግን አንዱንም ሳልጠቀመው ይሄው ከሰው እጅ ላይ ወደቅኩ" በማለት ያለችበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በቀበሌ ቤት ከሚኖር ቤተሰብ ጋር ተጠግታ ዘጠኝ ሰዎች ሆነው እየኖሩ እንደሆነ የምትናገረው ዓለምጸሐይ፣ "40 ኪሎ ገብስ፣ ማር እና ቅቤ የመሳሰሉትን በደካማ ጉልበቴና ያለአጋዥ አዘጋጅቼ ይረጋጋል በሚል ብወጣም ምንም ነገር ሳላወጣ እንደወጣሁ ቀረሁ" ብላለች።

አሁን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየኖረች መሆኗን የምትናገረው ዓለምፀሐይ "በቂ ምግብ ስለማላገኝ ጡቴ ወተት አያመነጭም። ልጄም በመራቡ እያለቀሰ እየተጎዳብኝ ነው። አሁን ከሰው ቤት በመሆኔ የተገኘውን ከመመገብ ውጪ ምንም አማራጭ የለንም፣ ያለን ተስፋ ወደቤታችን መመለስ ብቻ ነው" በማለት ያለችበትን ሁኔታ ገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, Dessie City Admin.

እየሩስ ታደሰ ደግሞ ከ8 ዓመት ልጇ ጋር ከወልዲያ ነው የተፈናቀለችው። የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር ስትሆን ለመውለድ ከአምስት ያልበለጠ ቀን ቀርቷታል።

ደሴ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ መጠለያዎች መካከል አንዱ በሆነው ዳውዶ ትምህርት ቤት ውስጥ የምትኖረው እየሩስ፣ የሚንከባከባትም ሆነ የሚያግዛት ማንም ሰው እንደሌላት ትናገራለች።

እየሩስ የመጀመሪያ ልጇን የወለደችው በቀዶ ሕክምና ነው። ደም ግፊት ስላለባት የአሁኑን ሁለተኛውን ልጇንም በምጥ መውለድ እንደማትችል ተነግሯታል።

አሁን በምትኖርበት መጠለያ ውስጥ በአንድ ክፍል ከ37 ሰዎች ጋር እየኖረች ነው። ከአምስት ቀን በኋላ በቀዶ ሕክምና ስትወልድም ሌላ የመታረሻ ስፍራ ስለሌላት ይህንኑ መጠለያ ብቸኛ አማራጭ አድርጋ አዲሱን ልጇን ይዛ ከሆስፒታል ለመመለስ ተስፋ አድርጋለች።

ስለምትታረስበት ሁኔታ እየሩስ ለቢቢሲ ስትናገር "ምንም የተዘጋጀ ነገር የለም፤ እንዲሁ በደመነፍስ ነው እየኖርን ያለነው። ተመሳሳይ ምግብ ነው የምንበላው፣ የምንኖረውም ከታመመው፣ ከሕጻኑ፣ ከአዛውንቱ ከሁሉም ጋር ነው። ይህ በራሱ አንድ ስጋት ነው" ትላለች።

እነዚህ እናቶች ጦርነቱ የመኖሪያ ቀያቸው ሳይደርስ ተፈናቅለው ደሴ መድረስ የቻሉ ናቸው። በሺዎች ሚቆጠሩ ሌሎች የሠሜን ወሎ ዞን እናቶች ደግሞ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አይታወቅም።

ስለጉዳዩ ቢቢሲ የጠየቃቸው የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት አያሌው "በአማካይ በወር ከ6 ሺህ በላይ እናቶች በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ጤና ተቋማት ይወልዱ ነበር፣ አሁን በመጠለያ ካምፕ ከወለዱት 118 እናቶች ውጪ ሌሎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አይታወቅም" ብለዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ስድስት ሆስፒታሎች፣ በርካታ የግል የጤና ተቋማት እና ጤና ጣቢያዎች ለእናቶች የወሊድ አገልግሎት እና ክትትል ይሰጡ ነበር።

ነገር ግን አመጺያኑ አካባቢዎቹን ከተቆጣጠሩ ወዲህ እነዚህ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በመውደማቸውና ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው እናቶች በዚህ ወቅት ምን እንደገጠማቸው አይታወቅም ብለዋል ኃላፊዋ።

ከወላድ እናቶች በተጨማሪ በዞኑ ውስጥ የተለያዩ መድኃኒቶችን ይወስዱ የነበሩ ሕሙማን ሕክምናቸው በመቋረጡ "አሁን በሕይወት ይኖራሉ ለማለት እንቸገራለን" ይላሉ ወ/ሮ ሰላማዊት።

በዞኑ ከ18 ሺ በላይ የስኳር ታካሚዎች፣ ከ20 ሺህ በላይ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች፣ 1145 የቲቢ ታካሚዎች እንደነበሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።