በአፍጋኒስታን ጉዳይ ኮንግረስ ፊት የቀረቡት አንቶኒ ብሊንከን ምን አሉ?

አንቶኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ትላንት በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርበው መንግስታቸው ከአፍጋኒስታን የወጣበትን መንገድ በአግባቡ የተፈጸመ ነው ሲሉ ተከላከሉ።

ብሊንከን በተለይም ወደ ኋላ የቀሩ አሜሪካዊያን እና ከአሜሪካዊያን ጋር ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች ጉዳይን አስመልክቶ በርካታ ወቀሳዎች የደረሰባቸው ሲሆን የሪፐብሊካኑ ፓርቲ ወኪሎች ሂደቱ ታሊባን በአሳፋሪ መንገድ እንዲያሸንፍ የፈቀደ ነበር ሲሉ ተችተዋል።

ዴሞክራቶች በበኩላቸው በዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት የተፈረመውን የአሜሪካ እና የታሊባን ስምምነት ላይ ያተኮሩ ትችቶችን አሰምተዋል።

ብሊንከን በበኩላቸው ሂደቱ ቢዘገይ ኖሮ የሚመጣ ለውጥ እንደልነበረ በመግለጽ የመንግስታቸውን ውሳኔ ተከላክለዋል።

አሜሪካ ለ20 ዓመታት በአፍጋኒስታን በነበራት ቆይታ ከ6 ሺህ በላይ አሜሪካውያን እና 100 ሺህ የአፍጋኒስታን ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ጦርነቱም ከሁለት ትሪሊዮን ዶላር በላይ የወጣበት ነበር።

ዴሞክራቶች ብሎም የባይደን አስተዳደር አባላት በአገር ውስጥ ብሎም ከውጪ አገራት እየተሰነዘሩ ያሉ ትችቶችን ወደ ጎን በማለት ትኩረቱን ከመጨረሻው ቀናት ለመቀየር ሲሞክሩ ታይተዋል።

ይልቁንም ትልቁ ኪሳራ በአሜሪካ ታሪክ ረጅሙ በተባለለት ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ስህተቶች አማካኝነት የተከሰተ ነው ብለዋል።

በዚሁ የኮንግረስ ጉባኤ ላይ ሪፐብሊካኖች በካቡል ውስጥ «የተተዉ» የአሜሪካ ተባባሪ አፍጋኖች ዕጣ ፈንታ፣ የሽብር ሥጋት እና የሰብአዊ መብት ስጋቶች መጨመርን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በማንሳት ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተጋጭተዋል።

ብሊንከን በመክፈቻ ንግግራቸው ለ 20 አመታት የቀረቡ የትጥቅ ብሎም የስልጠና ድጋፎች ውጤት ካላመጡ በተጨማሪ አምስት ወይም 10 ዓመታት የሚመጣ ለውጥ አይኖርም ብለዋል።

እንዲሁም አንድም የአሜሪካ ወታደራዊ ወይም የስለላ ተቋማት አፍጋኒስታን በዚህ ፍጥነት ትወድቃለች ብለው እንዳልተነበዩ ተናግረዋል።

ብሊንከን እስካሁን ድረስ ከአፍጋኒስታን ያልወጡ አሜሪካዊያን ቁጥርን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ 100 የአሜሪካ ዜጎች ለመውጣት ጥያቄ እንዳቀረቡ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥም ለ 60 ዎቹ «መቀመጫዎችን» በማመቻቸት እንዲወጡ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም 30ዎቹ ብቻ ለመውጣት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ከአሜሪካ ጋር ሲሰሩ የነበሩ እና አሁንም በካቡል የሚገኙ አፍጋኖችን በተመለከተ ግን በቁጥር የተደገፈ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ሌላው ብሊንከን የቀረበላቸው አንኳር ጥያቄ አሜሪካ ታሊባንን እንደ ሕጋዊ መንግስት ትቀበለዋለች ወይ የሚለው ነው።

«የትኛውንም አይነት ቅቡልነት ወይም ድጋፍ የሚፈልጉ ከሆነ እንደልብ የመጓዝ መብትን ከማክበር ይጀምራል። ታሊባን በዚህ ሰአት አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ ይገኛል፤ ይህ እውነታው ነው» ሲሉ ለኮንግረሱ ተናግረዋል።

አክለውም «አገሪቱ በአለም አቀፍ ዕርዳታ ላይ በመመስረቷ ምክንያት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በታሊባን ላይ <ጉልህ መደራደሪያ (Leverage)> አለው ሲሉም ተደምጠዋል።

ታሊባን አሸባሪ ቡድኖችን በአፍጋኒስታን እንዳይቋቋሙ ቁርጠኛ መሆኑን መግለጹን ተናግረው «ይህ ማለት ግን በታሊባን እንተማመናለን ማለት አይደለም። ስጋቶችን ንቁ ሆነን መከታተላችንን እንቀጥላል» ሲሉ ለኮንግረሱ ተናግረዋል።