ከአሸናፊነት የተሰረዘው ኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጭ እንዴት ያልተፈቀደ ጫማ አደረገ?

በተስፋ ጌታሁን (ሦስተኛ)፣ ሌዮናርድ ላንጋት (አንደኛ) እና ኤድዊን ኮስጌይ (ሦስተኛ)

የፎቶው ባለመብት, vienna-marathon.com

የምስሉ መግለጫ,

በተስፋ ጌታሁን (ሦስተኛ)፣ ሌዮናርድ ላንጋት (አንደኛ) እና ኤድዊን ኮስጌይ (ሦስተኛ)

እሁድ መስከረም 02/2014 ዓ.ም በአውሮፓዊቷ አገር ኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና በተደረገው የማራቶን ውድድር ላይ ተሳትፎ አንደኛ በመውጣት ያሸነፈው ኢትዮጵያዊው ደራራ ሁሪሳ ከታላቁ ድሉ ጋር መቆየት የቻለው ከ45 ደቂቃዎች ያልበለጠ ነበር።

የደራራ አሸናፊነት በውድድሩ ላይ ከተረጋገጠ በኋላ የሩጫው ሥነ ሥርዓት ተቆጣጣሪዎች ውጤቱን ሙሉ ለሙሉ ከማጽደቃቸው በፊት አትሌቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አግኝተው ምርመራ ካደረጉ በኋላ ውጤቱን ውድቅ ማደረጋቸው ተነገረ።

ለዚህም ምክንያቱ ደራራ ተጫምቶት የተወዳደረበት ጫማ መርገጫ (ሶል) ለውድድሩ ያልተፈቀደ ውፍረት አለው ነው የሚል ነበር።

አትሌት ደራራ ውድድሩን 2፡09፡22 በሆነ ሰዓት ቢያጠናቅቅም ማንም ባልጠበቀው ሰበብ ከእጁ የገባው ታላቅ ድልን ለመነጠቅ ተገዷል። ይህ ክስተት የአትሌቱን ልብ ብቻ የሰበረ አልነበረም የአሰልጣኙ ገመዶ ደደፎን ጭምር እንጂ።

ደራራ አዲስ አበባ ሳለ የሚሮጥበትን ትክክለኛውን ጫማ አዘጋጅቶ እንደነበር የሚናገሩት አሰልጣኙ ችግሩ የተከሰተው ኦስትሪያ ከሄደ በኋላ በተላከለት ሻንጣ ውስጥ በነበረው የልምምድ ጫማ ሰበብ ነው ነው።

"ከሩጫው ዕለት በፊት ማታ ላይ የሰጠነውን የውድድር ጫማ ትቶ ለልምምድ እንዲሆን የተላከውን ጫማ አደረገ" ይላሉ።

በ39ኛው የቪየና ማራቶን ላይ ተሳትፎ በማሸነፍ አምስተኛው ኢትዮጵያዊ ለመሆን ችሎ የነበረው የ23 ዓመቱ ወጣት አትሌት ደራራ ድሉ ከእጁ ወጥቶ የአንደኛ ደረጃ አሸናፊነቱ ሁለተኛ ለወጣው ኬንያዊ አትሌት ተሰጥቷል።

"ሰይጣን አትብላ ሲልህ እንደዚህ አይነት ነገር ይፈጠራል"

ይህ ክስተት አሰልጣኙን በእጅጉ አስቆጭቷል "እኛ ምንም እንኳን አጠገቡ ባንኖርም ለሩጫ በሚሆነው ጫማ ሩጥ ብለነዋል። ለሩጫው የሚያደርገውን የጫማ አይነትም ለውድድሩ አዘጋጆች አስመዝግበን ነበር። እንግዲህ ሰይጣን አትብላ ሲልህ አንዳንዴ እንደዚህ አይነት ነገር ይፈጠራል።" ይላሉ።

አሰልጣኙ ገመዶ እንደሚሉት ደራራ የማይፈቀደውን ጫማ ያደረገው ጠዋት ተነስቶ ለውድድሩ ሲዘጋጅ የሩጫ እና የልምምድ ጫማው ተመሳስሎበት የልምምዱን ጫማ አድርጎ ወጥቷል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንንም ክስተትና የተፈጠረውን ስህተት ለውድድሩ አዘጋጆች ለማስረዳት እንደተሞከረ የሚገልጹት አሰልጣኙ "ነገር ግን አንዴ የወጣ ሕግ አለ። አትሌቱ ሕጉን ማክበር አለበት። በሩጫ ውድድር የሚፈቀድ እና የማይፈቀድ ጫማ አለ" ስለዚህም የደራራን አሸናፊነት ከመነጠቅ ማዳን አልተቻለም።

በሩጫ ውድድሮች ወቅት አትሌቶች ሊጫሙ የሚገባቸው ጫማዎች ዝርዝር ያለ ሲሆን በዚህም መሠረት ለልምምድ፣ ለእርምጃ፣ ለትራክ፣ ለአስፋልት እና በጫካ ውስጥ ለሚደረግ ሩጫ የሚደረጉ ጫማዎች የተለያዩ ናቸው።

አትሌት ደራራ ለዚህ ውድድር ሲል ለረዥም ጊዜ ሲዘጋጅ ከመቆየቱ አንጻር የአሸናፊነቱ መነጠቅ የሚፈጥርበት ስሜት ቀላል አይሆንም። አሰልጣኙ እንደሚሉት ግን አሁን የተፈጠረውን ነገር ወደኋላ መመለስ ስለማይቻል ስለወደፊቱ ማሰብና መዘጋጀት ላይ ያተኩራል ብለዋል።

"አትሌቱ ገና ልጅ ነው። አሁኑ ስለተከሰተው ነገር ምንም ማድረግ ባይችልም ለወደፊት መዘጋጀት ነው የሚጠበቀው። ሌሎች አትሌቶችም እንዲህ አይነቱ ችግር እንዳይገጥማቸው መጠንቀቅ አለባቸው" ብለዋል።

አትሌት ደራራ ሁሪሳ የቪየናው ማራቶን ላይ ከመሳተፉ በፊት ሕንድ ውስጥ በተካሄደው ተመሳሳይ ውድድር ላይ በመሳተፍ ሁለተኛው የማራቶን ውድድሩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

አትሌት ደራራ ውድድሩን ካሸነፈ ከ45 ደቂቃዎች በኋላ የውድድር ደንብን በመጣሱ ውጤቱ እንደተሰረዘበት ተነግሮታል።

የውድድር ጫማ ልዩነት

የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች የበላይ አካል እንደሚለው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ የመጣው የመሮጫ ጫማዎች ምርት በውድድሮች ውጤት ላይ ተጽእኖ እንዳይኖረው ለማድረግ በተለያዩ የሩጫ ወድድሮች ላይ የሚደረጉ ጫማዎችን በተመለከተ መስፈርቶችን አስቀምጧል።

በዚህም ምክንያት ነው ደራራ ለልምምድ ሲጫማው የነበረውን ጫማ በውድድር ላይ አድርጎ በመገኘቱ በልፋት ያገኘውን የከባዱን ውድድር የአሸናፊነት ክብር እንዲያጣ ሆኗል።

በአህጉረ አውሮፓ በየዓመቱ ከሚካሄዱ ዋነኛ የማራቶን ውድድሮች መካከል የሚመደበው የቪየናው ማራቶን ላይ ለሚያሸንፉ አትሌቶች የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት ይበረከታል።

የደራራ የአንደኝነት ውጤት መሰረዝን ተከትሎ ሁለተኛ የሆነው ኬንያዊው አትሌት ሌዮናርድ ላንጋት አንደኛ፣ ኢትዮጵያዊው በተስፋ ጌታሁን ከሦስተኛ ወደ ሁለተኛ እንዲሁም አራተኛ ወጥቶ የነበረው ሌላኛው ኬንያዊ ኤድዊን ኮስጌይ ሦስተኛ ሆነው ተሸጋሽገዋል።

የጫማው መርገጫ ውፍረት

በውድድሩ ላይ አትሌቶች መጫማት ያለባቸው የውድድር ጫማዎች የሶል ውፍረት ከ40 ሚሊሜትር መብለጥ የለበትም። የውድድሩ አዘጋጆች ባደረጉት ማጣራት የደራራ ጫማ 50 ሚሊሜትር ውፍረት እንዳለው ካረጋገጡ በኋላ ውጤቱ እንዲሰረዝ አድርገዋል።

"ውሳኔው ግልጽ ነው፤ በጣም እናዝናለን። ደራራ ለልምምድ ብቻ በሚውለው ጫማ ነው የሮጠው። በቴክኒክ ስብሰባ ላይ ለሁሉም አትሌቶች አሳውቀን ነበር" በማለት ከውድድሩ ኃላፊዎች አንዱ ተናግረዋል።

"ደራራን ልደርስበት አልቻልኩም"

ደራራን ተከትሎ ሁለተኛ የወጣው የ25 ዓመቱ ኬንያዊ አትሌት ሊዮናርድ ላንጋት ከውሳኔው በኋላ የአንደኝነትን ቦታ እንዲይዝ ተደርጓል። "የደራራ ውጤት መሰረዙን አላወቅሁም ነበር። መጀመሪያ ላይ ለማመን ተቸግሬ ነበር" ብሏል የውጤቱን ለውጥ ባወቀ ጊዜ የተሰማውን ሲናገር።

"የመጨረሻው አሯሯጭ ከ32ኛው ኪሎሜትር በኋላ ሲወጣ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። ሁሉንም ነገር በመጨረሻው ኪሎሜትር ላይ ለመሞከር ወስኜ ነበር ግን ደራራን መከተል አልቻልኩም" በማለት ተስፋ ቆርጦ በቀጣይ አመት ለማሸነፍ እንደሚዘጋጅ ወስኖ ነበር።

ላንጋት በቪየናው ውድድር ላይ ለመሳተፍ የበረራ መዘግየትና በኳታሯ መዲና ዶሃ ውስጥ በሚገኝ አየር ማረፊያ ውስጥ አንድ ሌሊት ማደሩን በመግለጽ በከባድ ጫና ውስጥ ሆኖ በውድድሩ መሳተፉን ተናግሯል ሲል የውድድሩ አዘጋጅ ድረ ገጽ አመልክቷል።