አፍጋኒስታን ቀውስ፡ ታሊባን ጠንካራ ተቃዋሚዎች ባሉበት አካባቢ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል ተባለ

የአገር ውስጥ ምንጮች እንዳሉት ግለሰቡ በታሊባን ጥቃት አይደርስብኝም ብሎ ያምን ነበር።
የምስሉ መግለጫ,

የአገር ውስጥ ምንጮች እንዳሉት ግለሰቡ በታሊባን ጥቃት አይደርስብኝም ብሎ ያምን ነበር።

በአፍጋኒስታን ከካቡል 150 ኪሎሜትር በሚርቀው ፓንጅሺር ሸለቆ በታሊባንና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል በነበረ ውጊያ ቢያንስ 20 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ አረጋገጠ።

በአካባቢው የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የተቋረጠ በመሆኑ ዘገባ ለመስራት አስቸጋሪ ቢሆንም ታሊባን ቀደም ሲል ከዚህ ድርጊቱ ለመቆጠብ የገባውን ቃል በተጻረረ መልኩ ግድያ መፈፀሙን ቢቢሲ ማስረጃዎች አግኝቷል።

በፓንጅሺር አቧራማ መንገድ ዳርቻ የተቀረፀ ምሥል አንድ ግለሰብ ወታደራዊ ትጥቅ ለብሶ በታሊባን ተዋጊዎች ተከቦ ያሳያል።

ወዲያውኑም ተኩስ ተከፍቶ ግለሰቡ መሬት ላይ ሲወድቅ ይታያል፤ ነገር ግን የተገደለው ግለሰብ የጦሩ አባል ይሁን አይሁን ግልፅ አይደለም። ምክንያቱም በአካባቢውም የትግል ትጥቅ መልበስ የተለመደ ነው።

በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ላይ አንድ ሌላ ሰው፤ ግለሰቡ ሰላማዊ ሰው እንደሆነ ሲወተውት ይታያል።

ቢቢሲ በፓንጂሺር ቢያንስ 20 ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መገደላቸውን አረጋግጧል። ከሟቾቹ መካከል አንደኛው የሱቅ ሠራተኛ እና የሁለት ልጆች አባት የሆነው አብዱል ሳሚ ነው።

የአገር ውስጥ ምንጮች እንዳሉት ታሊባኖች ወደ አካባቢው ሲገሰግሱ ግለሰቡ " እኔ ደሃና የትንሽ ሱቅ ባለቤት ነኝ እንዲሁም በጦርነቱ ምንም ያደረኩት ነገር የለም" ሲል አልሸሸም ነበር።

ነገር ግን እንዳሰበው አልሆነም። 'ለተቃዋሚዎች ሲም ካርድ ሸጠሃል' በሚል ታሰረ። ከቀናት በኋላ ደግሞ አስክሬኑ በቤቱ አቅራቢያ ተጥሎ ተገኘ።

አስክሬኑን የተመለከቱ የዐይን እማኞች ድብደባ እንደተፈፀመበት የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሩት ተናግረዋል።

ባለፈው ወር ታሊባን ሥልጣን ላይ ሲወጣ የቀረው አንድ ክልል ነበር።

የፓንጂሽር ሸለቆ በአፍጋኒስታን ለተቃዋሚዎች የትግል ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።

አካባቢው በተቃዋሚው ኮማንደር አሕመድ ሻህ መስኡድ ሥር እያለ የሶቭየት ኃይሎችንና ታሊባንን ከአካባቢው አስወጥቶ ነበር።

በዙሪያው ያለው ተራራ አካባቢውን ለመያዝ ለሚሞክር ማንኛውም ኃይል ፈታኝ ነው።

የመስኡድ ወንድ ልጅ አሕመድ፤ ታሊባን አፍጋኒስታንን ለሁለተኛ ጊዜ ሲይዝ ታሊባንን ለመዋጋት የተደረገውን እንቅስቃሴ መርቷል። ይሁን እንጅ ባለፈው ሳምንት ታጣቂ ቡድኑ ተዋጊዎቻቸው ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ የሚያሳይ ምሥል በማጋራት ድል ማድረጋቸውን አውጀዋል።

ተቃዋሚ ኃይሎችም ከአሕመድ መስኡድ ጋር በመሰለፍ ታሊባንን ለመዋጋት ቃል የገቡ ሲሆን መስኡድም በታሊባን ላይ 'ብሔራዊ አመፅ' ጥሪ አቅርቧል።

ታሊባኖች ሌሎችን የአፍጋኒስታን ቦታዎች ሲቆጣጠሩ ትኩረታቸውን ወደ ፓንጂሺር አድርገዋል። ታሊባኖች ወደ አካባቢው ሲገቡ ነዋሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው እንዲመለከቷቸው ይነግሯቸው ነበር።

"ነዋሪዎች መውጣት አለባቸው፤ የእለት ሥራቸውንም ማከናወን አለባቸው" ሲሉ ቃል አቀባዩ ማላቪ አብዱላህ ራህማኒ ተናግረዋል።

" ነጋዴ ከሆኑ ወደ ንግዳቸው፣ አርሶ አደርም ከሆኑ ወደ እርሻቸው መሄድ ይችላሉ። እኛ እዚህ ያለነው እነርሱንና ቤተሰባቸውን ለመጠበቅ ነው" ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ይሁን እንጅ ከአካባቢው የወጣ ተንቀሳቃሽ ምሥል ለወትሮው ሰዎች የሚተራመሱበት የገበያ ቦታ ጭር ብሎ ያሳያል።

ሰዎችም አካባቢውን ለቀው ለመውጣት ተሽከርካሪዎችን ተሰልፈው ሲጠባበቁ ታይቷል።

በአካባቢው የምግብና የመድሃኒት እጥረት እንዳለም ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል።

ታሊባን ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ አድርጓል መባሉን ሀሰት ነው ብሏል፤ ነገር ግን በቁጥር አነስተኛ የሆኑትን የሃዛራ ሕዝቦች አባላት ጭፍጨፋ እና የሴት ፖሊስ የግድያ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ ታሊባን የበቀል እርምጃ ላለመውሰድ የገባው ቃል መሬት ላይ ከሚፈፅመው ነገር እንደሚለይ ተጨማሪ ማሳያ ሆኗል።

"እንደዚህ ዓይነት ሪፖርቶች ቀደም ሲል በመላው አፍጋኒስታን በሰነድነው ማስረጃ ውስጥ የወደቁ ይመስላል" ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዎች ባልደረባ ፓትሪሽያ ግሮስማን ተናግረዋል።

" ታሊባን ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ላይ ወደ ካቡል ሲገባ ተመሳሳይ ሪፖርቶች ነበሩን። የቀድሞ የደህንነት ሠራተኞች ፣ የቀድሞ የመንግሥት አባላት እና ሰላማዊ ሰዎች በአብዛኛው በበቀል እርምጃ እንደተገደሉ መረጃ ማሰባሰብ ችለናል ። ይህ ምንም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ነው የሚያሳየው" ብለዋል ፓትርሽያ።