"የአማራ ብቻ ሳይሆን የጋምቤላ፣ የሲዳማና ደቡብ ክልል ልዩ ኃይሎች ቤንሻንጉል ጉሙዝ ገብተዋል"

የአማራ ልዩ ኃይል

የፎቶው ባለመብት, Bulen Woreda Communication

ከሰሞኑ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ቡለን ወረዳ መግባቱን የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን አስታውቋል።

ከአማራ ክልል በተጨማሪ የጋምቤላ፣ የሲዳማ እንዲሁም የደቡብ ክልል ልዩ ኃይሎች ወደ አካባቢው መግባታቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ የሰላም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

እነዚህ ኃይሎች በክልሉ በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ስር ሆነው የሰላም ማስከበር ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን አቶ አብዮት ተናግረዋል።

በተለይም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ክልሉ ከመግባቱ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን አስመልክተው የጸጥታ ኃላፊው "ከአማራ ክልል ጋር ሰፊ አስተዳደራዊ ወሰን እንጋራለን፣ የተለያዩ ሥራዎችን በጋራ እናከናውናለን። በተጨማሪም ወንድማማች ሕዝቦች ነን። ስለዚህ በሰላምም ሆነ በልማት ሥራዎች ላይ በመቀናጀት እንሰራለን" በማለት አስረድተዋል።

በየትኛውም ክልል ያለ የልዩ ኃይል በኮማንድ ፖስቱ ስር ሆኖ ሊሳተፍ እንደሚችል የሚገልጹት አቶ አብዮት ይህ የሆነውም አካባቢው የሕዳሴው ግድብ መገኛ በመሆኑም ነው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኃላፊው እንደ ምክንያት የሚያነሱት "ህወሓት በሱዳን በኩል ሰርጎ እየገባ በዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽመበት ብሎም የሕዳሴ ግድቡን ለማጥቃት የሚሞክርበት አካባቢ በመሆኑ የሁላችንንም ትብብር የሚፈልግ አካባቢ ነው" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የመተከል ዞን በኮማንድ ፖስት የሚመራ እንደመሆኑ የኃይል ስምሪት በሚያስፈልግበት ጊዜ ከክልሉ ጸጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ እንዳይሰራ የሚከለክል ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በመተከል ዞን ውስጥ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።

በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለመቆጣጠር ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉና በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) ተቋቁሞ እየሰራ ቢሆንም አሁን ድረስ ጥቃቱ እንደቀጠለ ነው።

በቅርቡም ከሱዳን በኩል ወደ ክልሉ ሰርገው በመግባት ጥቃት ሊፈጽሙ ነበር የተባሉ ታጣቂዎች በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንደተወሰደባቸው መዘገቡ ይታወሳል።

በክልሉ ውስጥ መረጋጋት ለማምጣት ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የልዩ ኃይል አባላት መሰማራታቸውን የገለጹት ኃላፊው ጉዳዩ ከጸጥታ ጋር ስለሚያያዝ የሠራዊቱን ቁጥርና እንቅስቃሴ መግለጽ እንደማይችሉ አስረድተዋል።

ከሰሞኑ የክልሉ መንግስት እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልሎች የልዩ ኃይል አባላት፣ ከሚሊሺያ አባላትና ከግል ታጣቂዎች ጋር በመሆን "የጥፋት ቡድን" ብለው በጠሩት ታጣቂ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ክልሉ አስታውቋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂ የነበረው ኃይል ጋር ሰላማዊ ድርድር ለመፍጠር ቢሞከርም በአሁኑ ወቅት የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱት ጭምር ወደ ጫካ መግባታቸውን ከሰሞኑ በክልሉ መንግሥት ተገልጿል።

"ምንም እንኳን ቡድኑ በፈጠረው የጸጥታ ችግርና ጥቃት በሰው ህይወት፣ በአካል በንብረት ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም የክልሉ መንግሥት ችግሩን በሰላማዊ መንገድና በውይይት ለመፍታት ከፍተኛ የሆነ የበጀት፣ የጊዜ፣ የሰው ኃይል በመመደብ ለወራት የዘለቀ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል" በማለት ክልሉ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

የክልሉ መንግሥት በመተከልና ካማሺ ዞኖች ከሚንቀሳቀሰው የታጣቂ ቡድኑ አባላት መካከል የተወሰኑት የቀረበውን ሰላማዊ ድርድር በመቀበላቸው የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ክልሉ አመልክቷል።

የክልሉ መንግሥት ታጣቂውን ቡድን "ጸረ- ሰላም ኃይልና የህወሓት ተላላኪ" በሚል ከመጥራት ውጪ በስም አልጠቀሰውም።

ከዚህ ቀደም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥትና ታጣቂው በጉሙዝ ሕዝብ ዴሞከራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ቡድን በክልሉ በተደጋጋሚ በንፁሃን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆም የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።