ኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻውን ለመሸጥ ለተወዳዳሪዎች ክፍት አደረገ

kids playing with a phone

የፎቶው ባለመብት, Justin Sullivan

ኢትዮ-ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል የማዛወር አካል የሆነው 40 በመቶ የሚሆነውን የአክስዮን ድርሻ ለመሸጥ ለተወዳዳሪዎች ክፍት ማድረጉን በዛሬው ዕለት የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የኦፕሬሽን፣ የመሰረተ ልማት አስተዳደርና የቀጣይ ትውልድ ቴክኖሎጂ አቅሞችን በተመለከተ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች በማምጣት እሴት መጨመር የሚችሉ ፍላጎት ያላቸውን ተጫራቾች እንደጋበዘም ተጠቁሟል።

በከፊል ወደ ግል የማዛወር የሃሳብ መጠየቂያም እንዳወጣም የተገለጸ ሲሆን ይህም በከፊል ወደ ግል የማዛወር የሚመለከቱ መመሪያዎችና ዝርዝር መረጃዎች ሃሳብ የሚቀርብበት ሂደት እና የብቃት መስፈርት ጨምሮ በሰነዱ ተመላክቷል ተብሏል።

ይህ የሃሳብ መጠየቂያ ለሚመለከታቸው ሁሉ ክፍት ሲሆን ከዚህ በፊት የፍላጎት መግለጫ በማቅረብ ፍላጎታቸውን ለገለጹ ኩባንያዎች ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የሃሳብ መጠየቂያውን ለማግኘት ፍላጎት ያለው ወገን የማይመለስ 20 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መክፈልም እንደሚገባውም ተመላክቷል።

ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢትዮቴሌኮም ገቢው ትርፋማ ከሚባሉ ድርጅቶች አንዱ ቢሆንም ከሌሎች የቀጠናው ኩባንያዎች ጋር ሲወዳዳር ዝቅተኛ ነበር ይላሉ በዘርፉ ያሉ ተንታኞች።

ኢትዮጵያ ኢትዮቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ድርሻ ለመሸጥ የወሰነችው በዋነኝነት ያላትን ከፍተኛ ዕዳ ለመክፈል እንደሆነ ተንታኞች የሚናገሩ ሲሆን፤ በተጨማሪነት የቴሌኮምን ተደራሽነት ለመጨመርና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንደሆነም ይጠቀሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም አካል ሆኖ የግል ኢኮኖሚ ሚናን ለመጨመር፣ የመንግሥት ልማት ውጤታማነት ለማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጎልበት፣ ላካፒታል ያላቸውን ተደራሽነት እና የአገልግሎታቸውን ጥራት ለማሻሻልም ወደ ግል የማዛወሩ አዋጅ እንደወጣም የገንዘብ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫ አመላክቷል።

በውጭ ኩባንያዎች ከሚያዙት ሁለቱ የቴሌኮም ፈቃዶች በተጨማሪ ዋነኛው የአገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮቴሌኮምም በሩን ለባለሀብቶች ከፍቷል።

በዚህም በመንግሥት ብቸኛ ባለቤትነት ሥር የቆየው ተቋሙ 40 በመቶ ድርሻውን ለውጪ ባለሀብቶች፣ 5 በመቶውን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን መንግሥት እንደሚይዘው ይጠበቃል።

በዓለም ላይ ካሉ አገራት የቴሌኮምን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ከከፈቱት የመጨረሻ ከሚባሉ አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በመታገዝ ከያዘችው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች መካከል አንዱ በማድረግም ለሦስት ዓመታት ያህል የቴሌኮምን ድርሻን ለመሸጥ በሂደት ላይ ነበረች።

እነዚህ አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች የሥራ እድልን ለመጨመር፣ ድህነትን ለመቀነስና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ሁሉን አካታችና ዘለቄታ ባለው መልኩ ለማሳደግ ጠቃሚ እንደሆነም ሲነገር ነበር።

በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የቴሌኮም ፈቃድ የተሰጠው በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት ሲሆን ያሸነፈውም በ850 ሚሊዮን ዶላር ነው።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችንና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ የተካተቱበት ነው።

ጥምረቱ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የቴሌኮም አገልግሎት ከመጪው ጥር 2014 ዓ.ም በኋላ ይጀምራል ተብሏል።

ቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የመጀመሪያውን ፈቃድ ያገኘው የውጭ ተቋም በርካታ ጥቅሞችን ለአገሪቱና ለሕዝቧ ያስገኛል የተባለ ሲሆን በተለይ በየጊዜው እያደገ ከመጣው የሥራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር አንጻር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተነገረ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው የሥራ ዕድልን ይፈጥራል ተብሏል።