ዓለማችን የሙቀት መጠንናቸው ከ50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆኑ ሞቃታማ ቀናትን እያስተናገደች ነው

ዓለማችን የሙቀት መጠንናቸው ከ50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆኑ ሞቃታማ ቀናትን እያስተናገደች ነው

በየዓመቱ የሙቀት መጠናቸው ከ50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆኑ ሞቃታማ ቀናት ከእአአ 1980ዎቹ ጀምሮ በሁለት እጥፍ መጨመራቸውን የቢቢሲ ጥናት አመላከተ።

በርካታ የዓለም ክፍል ከፍተኛ ሙቀት መመዝገቡ ለሰው ልጆችን ጤና እና የኑሮ ዘዬ ፈተና ሆኗል።

ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ከ50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሙቀት የተመዘገበባቸው ቀናት ጭማሪ አሳይቷል።

ኃይል ለማመንጨት ሲባል ጋዝ እና ከሰል ማቃጠል የሙቀት መጠን ለመጨመሩ ዋነኛ ምክንያት ናቸው በማለት የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪው ዶክተር ፍሬድሪክ ኦቶ ያስረዳሉ።

የዓለም ሙቀት ሲጨምር፤ የከፍተኛ ሙቀት መከሰት አይቀሬ ነው። ከፍተኛ ሙቀት ለሰው ልጆች እና ለተፈጥሮ ከፍተኛ አደጋን ይደቅናል። የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ ሕንጻዎች እና መንገዶችም በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ የአገልግሎት እድሜያቸው ያጠረ ይሆናል።

ከ50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሙቀት በመካከለኛው ምስራቅ እና በባህረ ሰላጤው ቀጠና ሲመዘገበ አዲስ ነገር አይደለም። በጣሊያን 48.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዲሁም በካናዳ 49.6 ዲግሪሴንቲ ሲመዘገብ ግን አዲስ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ኃይል ለማመንጨት ጥቅም ላይ የሚውሉትን የከሰል እና ነዳጅ መጠን መቀነስ የማይቻል ከሆነ ከፍተኛ ሙቀት በተቀረው የዓለም ክፍል መከሰቱ አይቀርም።

የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሲሃን ሊ፤ የሰው ልጅ ከተደቀነበት ፈተና እራሱን ለማዳን ልቀቶችን ለመቀነስ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ አለበት ይላሉ።

የቢቢሲ ጥናት እንዳለመላከተው ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት የአየር ሙቀት መጠን በ0.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ጨምሯል።

ከፍተኛ የሙቀት ጭማሪ ከተመዘገበባቸው የዓለማችን አካባቢዎች መካከል ምስራቅ አውሮፓ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚል ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች የሙቀት መጠን ከ1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። አርክቲክ እና መካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በኋላ ጭማሪ ታይቷል።

በአሁኑ ወቅት ያለው የዓለም ሙቀት በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ እአአ በ2100 ወደ 1.2 ቢሊዮን ሕዝብ ሙቀትን ተከትሎ ለሚመጡ የጤና እክሎች ይጋለጣሉ። ድርቅ እና እሳት በተደጋጋሚ ይከሰታሉ።

ሼይክ ካዜም አል ካቢ ስንዴ አምራች ገበሬ ናቸው። ኑሯቸው በመካከለኛው ኢራቅ ነው።

ሼይክ ካዜም በአንድ ወቅት የእርሻ መሬታቸው ለም ነበር። በምርታቸው ከእርሳቸው አልፎ ለጎረቤቶቻቸው ቀለብ ይሰፍሩ እንደነበረ ያስታውሳሉ። ዛሬ ላይ ግን የእርሻ መሬታቸው እየደረቀ መሄዱን ይናገራሉ።

"ይህ መሬት አረንጓዴ ነበር። አሁን ግን ሁሉም ነገር ተቀይሯል። አሁን በረሃ ሆኗል" በማለት ሼይክ ካዜም ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት ሼይክ ካዜም በሚኖሩበት አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች በእርሻ ሥራ መቀጠል ባለመቻላቸው የተሻለ ሕይወት እና ሥራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተሰደዋል።

"ወንድሜ ተለይቶኛል፤ ጓደኞቼ እና ታማኝ ጎረቤቶቼን አጥቻለሁ። ያለንን በሙሉ ከእኔ ጋር ይካፈሉ ነበር። አሁን አጠገቤ ማንም የለም። ከባዶ መሬት ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጫለሁ" ይላሉ።