ኤርትራውያን የፖለቲካ እስረኞች ለ20 ዓመታት አልታዩም

ኤርትራውያን የፖለቲካ እስረኞች

የፎቶው ባለመብት, Amnesty International

የመብት ተሟጋቹ አለም አቀፉ ድርጅት አምነስቲ ለሁለት አስርት አመታት ያልታዩትን 21 ኤርትራውያን የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈቱ ለመጠየቅ ዘመቻ እያካሄደ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2001 የኤርትራ መንግሥት የአገሪቱን ነፃ ሚዲያ ዘግቶ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በአደባባይ የተቹ 11 ፖለቲከኞችን እና የፖለቲካ ተሃድሶን ከሚሹ ፖለቲከኞች የተላከ ግልፅ ደብዳቤን ያሳተሙ 10 ጋዜጠኞችን አሰረ።

የኤርትራ መንግሥት በቁጥጥር ስር የዋሉት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ስለሆኑ ነው ይላል።

እስረኞቹ እስካሁን ድረስ ክስ ያልቀረበባቸው ሲሆን ያሉበትም አይታወቅም።

የአምነስቲም የትዊተር ዘመቻም ያሉበትን በሚጠይቅ መልኩም እየተካሄደ ይገኛል።

በቅርቡም ለሃያ ዓመታት ያህል ያለ ፍርድ የታሰረው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በአስቸኳይ እንዲፈታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት አጣሪ እንዳሉት ዳዊት ይስሃቅ በባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ክስ አልተመሰረተበትም እንዲሁም ጠበቃውንም አግኝቶ አያውቅም።

የሰብዓዊ መብት አጣሪዋ ዳዊት ይስሃቅ በህይወት አለ የሚለው ጉዳይ ላይ ፍራቻ እንዳለ ገልፀው የኤርትራ ባለሥልጣናት የጋዜጠኛውን በህይወት መኖር ማስረጃ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል።

ከጋዜጠኛው እስር ጋር በተያያዘም ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (አርኤስኤፍ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ክሱን ስዊድን ለሚገኘው ዐቃቤ ሕህግ ከወራት በፊት አቅርቧል።

ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተጨማሪ ሰባት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ቡድኑ ወንጅሏቸዋል።

ባለሥልጣናቱ ጠንከር ያለ ምርመራ እንዲከፈትባቸው፣ ጋዜጠኛውን በማገት፣ በማንገላታትና ያለበትንም ደብዛ በማጥፋት ክስ ይመሰርትባቸዋል ብሎም እንደሚያንም ቡድኑ በወቅቱ በድረ-ገፁ አስፍሯል

ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘችበት ከአውሮፓውያኑ 1993 ጀምሮ ምርጫ አላደረገችም። ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ለ28 ዓመታት ያህል በስልጣን ላይ ቆይተዋል።

አምነስቲ ከዚህ ቀደም በኤርትራ ያለውን የከፋ የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ ሪፖርቶችን አቅርቧል። በእነዚህም ሪፖርት መሰረት ጨካኝ፣ ኢሰብዓዊና፣ ከሰውነት ዝቅ ባደረገ መልኩ እንደተያዙም ያሳያል።

በሌሎች አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን እና የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ቤተሰብ አባላትም በቀጣዮቹ 12 ወራት በዓለም ዙሪያ ዓውደ ርዕይ የማድረግ እቅድ አላቸው። ይህም ስለ ታሳሪዎቹ በዓለም ዘንድ ትኩረት ለመሳብ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2022 በለንደን ሃውስ ኦፍ ኮመን እና በኤድንብራ በሚገኘው የስኮትላንድ ፓርላማ እና በተለያዩ የአምነስቲ ቅርንጫፍ ቢሮዎችም ለዕይታዎች ይቀርባል ተብሏል።