ኢትዮጵያ አይኤምኤፍን አዲስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ስምምነት ጠየቀች

ብርና ዶላር

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) አዲስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ኤክስቴንድድ ክሬዲት ፋሲሊቲ) ስምምነት መጠየቋን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት የተራዘመው የብድር አቅርቦት ጊዜው ያለቀ ቢሆንም የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት (ኤከስቴንድድ ፈንድ ፋሲሊቲ) የተባለው የተቋሙ የድጋፍ ማዕቀፍ ቀጥሏል ተብሏል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ የተራዘመ የብድር አቅርቦት እና የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት በተባሉ ማዕቀፎች በኩል በአውሮፓውያኑ 2019፣ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ማፅደቁ የሚታወስ ነው።

አገሪቷ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ኤክስቴንድድ ክሬዲት ፋሲሊቲ) ማዕቀፍ ውስጥም ቃል ከተገባላት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስካሁን የተቀበለችው ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ሳታገኝ ነው ጊዜው ያበቃው።

ኢትዮጵያም የተራዘመው የብደር አቅርቦት በአዲስ ስምምነት እንዲቀጥልና የተፈጸመውን እንዲተካና ተመሳሳይም የገንዘብ መጠን እንዲሆን ተስፋ ተደርጎበታል።

አዲሱ የተራዘመው የብድር አቅርቦት የቀድሞውን በመተካት በድህነት ቅነሳና የእድገት ፕሮግራሞች (PRGT)ን እንድታገኝም ጠይቃለች ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስቴርም በመግለጫው የተራዘመ የብድር አቅርቦት እና የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት ማዕቀፎች በኩል በኩል ለኢትዮጵያ የማሻሻያ ሂደት ያበረከተውን ድጋፍም እውቅና ሰጥቷል።

አገሪቷ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምን ጨምሮ ለሌሎች ተቋማትና አገራት ያላትን ዕዳ ለማሸጋሸጝ የአበዳሪዎች ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የመጀመሪያውን የአበዳሪዎች ኮሚቴ ስብሰባ መስከረም 12/2014 ዓ.ም ተካሂዷል።

የአበዳሪዎቹ ኮሚቴ የጋራ ሊቀመንበሮች የሆኑት ፈረንሳይና እና ቻይና ሲሆኑ ኮሚቴውን ለማቋቋም ያደረጉትን ያላሰለሰ ጥረት እንዲሁም አገሪቷ በስብሰባው ላይ ተገኝታ ጥያቄዋን እንድታቀርብ ለተመቻቸላት እድል ሚኒስቴሩ አመስግኗል።

ኢትዮጵያ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) ያለባትን 30 በሊዮን ዶላር እዳ ማቃለያ በጊዜው ታሳካ ዘንድ በአበዳሪዎች ኮሚቴ የተወሰዱ አስፈላጊ እርምጃዎችን በበጎ መልኩ እንደምታያቸው አስታውቃለች።

በዚህ ማዕቀፍ መሰረት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የደቀቀውን የዓለም ኢኮኖሚ እንዲያገግም በተለይም ለሚያድጉ አገራት የብድር እፎይታ ጊዜ የሰጡ ሲሆን ከዚህም ኢትዮጵያ አንዷ ተጠቃሚ ናት።

የአበዳሪዎች ኮሚቴ የአገሪቱ የእዳ ሽግሽግ በአገሪቱ ካለው የምጣኔ ሀብት ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲሁም በመሠረታዊነት የማክሮ ኢኮኖሚውን መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያደረገውን ጥረት አገሪቱ ደስተኛ መሆኗም ተገልጿል።

በተለይም እርምጃዎቹ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከተፈጠረው ምጣኔ ሀብታዊ ተግዳሮቶች የመፍትሄ እፎይታን እንደሚሰጥና አገሪቷ ለልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ይውል ዘንድ የገንዝብ ፍሰት ቦታን በመፍጠር እንዲሁም የአገሪቱን የእዳ መጠንም ለማሸጋሸግ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

አገሪቷ የእዳዋንም ሽግሽግ ሁኔታ ዝርዝሮችን ለማጠናቀቅ ከአበዳሪዎቿ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ብሏል።

የሃገር በቀሉን የኢኮኖሚ ማሻሸያ እየደገፈ ያለው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አገሪቷ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጫና እንድታገግም የሚያደርገውን የምጣኔ ሀብት ድጋፍ እንዲሁም ለተጋላጭ ማኅበረሰቦች አቅርቦትም ቀጣይ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም ሚኒስቴሩ አፅንኦት ሰጥቷል።

ተቋሙ የገንዘብ እና እና የፋይናንስ ዘርፍ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን የሚደግፍ የቴክኒክ ድጋፍ የኢኮኖሚያችንን አፈፃፀም በማጠናከር ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ተብሏል።

ከጥቂት አመታት በፊት የሃገር በቀል የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ እየተገበረች ሲሆን ይህም የተረጋጋ የእድገት ጎዳና የማይናወጥ ምጣኔ ሀብት እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

ማሻሻያውም የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር፣ ዘላቂ የእዳ አስተዳደር ሥርዓት፣ የግሉ ዘርፍ በተሻለ ሁኔታ የሚሳተፍበት ከባቢ መፍጠር፣ የመንግሥት ልማቶች ድርጅቶች የተሻሻለ አፈፃፀም፣ የተሻሻለ የወጪ ንግድ እንዲሁም ገቢን መጨመርና ወጪዎችን ማስተካከል መቻሉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ዋነኛ አበዳሪ የሚባሉ የገንዘብ ተቋማት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ብድር ለመልቀቅ እያንገራገሩ ነው ተብሏል።

በዋነኝነትም የነዚህ ተቋማት ስጋት ተጨማሪ ብድር ለአገሪቱ መስጠት የበለጠ ጫና ውስጥ ይከታታል እንዲሁም መክፈል አቋሟን የበለጠ ሊያዳክም ይችላል ከሚል ስጋት ጋር የተያያዘ ነው።

የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጰያ ለመስጠት ቃል የገባውን 339 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ የዓለም ባንክ አንድ አካል የሆነው የዓለም አቀፉ የልማት ትብብር ማኅበር (ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት አሶሲየሽን) 3.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የዓለም የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) 2.7 ቢሊዮን ዶላር፣ የኢትዮጵያ ዋነኛ አበዳሪ ቻይና 1.4 ቢሊዮን ዶላርና ሌሎችም አበዳሪዎች ባለፈው አመት እስከ መጋቢት ድረስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን አልተለቀቀም።