የቀድሞ የኦነግ ጦር አዛዥ ጎሊቻ ዴንጌ እንዴት ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ?

ጎሊቻ ዴንጌ

የፎቶው ባለመብት, Oromia Communication Bureau

የምስሉ መግለጫ,

ጎሊቻ ዴንጌ

የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ጦር የደቡብ ዞን አዛዥ ጎሊቻ ዴንጌ ከቡድኑ ተለይቶ ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎለታል።

ጎሊቻ ዴንጌ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘውን እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውን እና መንግሥት ደግሞ አሸባሪ ሲል የሰየመውን የሸኔን አንድ ክንፍ ሲመራ ቆይቷል።

በኢህአዴግ አስተዳደር ወቅት፤ ጎሊቻ ዴንጌ ለ27 ዓመታት በወቅቱ ከነበረው የአገሪቱ አስተዳር ጋር የትጥቅ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራል።

ይህ የታጣቂው ቡድን አዛዥ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሲያካሄድ የቆየውን የትጥቅ ትግል ጉዞውን በመተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ መግባቱ ተዘግቧል።

ጎሊቻ ዴንጌ የትጥቅ ትግል አቁሞ እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጣ?

ጎሊቻ ዴንጌ የትጥቅ ትግሉን አቁሞ ወደ ወደ ሰላማዊ ህይወት የተመለሰው በሁለት ምክንያት እንደሆነ ይናገራል። ይህም በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት እና በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከህወሓት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱ ድርጅቱን ጥሎ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነው ይናገራል።

የኦሮሞ ነጻነት ጦር ደቡብ ዞን አመራርነት ከተነሳ ሦስት ዓመታት እንደተቆጠሩ የሚናገረው ጎሊቻ፤ ከቡድኑ ጫናዎች ይደርሱበት እንደነበረ ይናገራል።

የጠቅላይ ሚኒስርት ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የኦነግ ሠራዊት አገር ቤት ሲገባ "እኔ የቁም እስረኛ ነበርኩ" የሚለው ጎሊቻ፤ በቡድኑ ተገዶ ለመገናኛ ብዙኃን ይናገር እንደነበረ ጭምር ለቢቢሲ ተናግሯል።

የደረሰብኝ ጫና ላለፉት 27 ዓመታት ከነበርኩበት የትጥቅ ትግል እንድወጣ አድርጎኛል የሚለው ጎሊቻ፤ "አካሄድ ላይ አልተግባባንም። ከፍተኛ ጫና በእኔ ላይ አሳድረዋል። የግድያ ሙከራም አድርገውብኛል። አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው ትግል እና አመራር ትክክል አይደለም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ይህ መታደስ አለበት ብዬ ስናገር ነበር" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

ጎሊቻ ከሚመራው ጦር ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የቦረና አገር ሽማግሌዎች እንዲያሸማግሏቸው ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ይናገራል።

የኦሮሞ ነጻነት ጦር ምን ይላል?

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን በበኩሉ ጎሊቻ ዴንጌ በጤና እክል ምክንያት ከጦር አዛዥነቱ ከተነሳ ከአንድ ዓመት በላይ መሆኑን በመጥቀስ የጎሊቻ ምክትል የነበረው ግለሰብ የደቡብ ዞን እንዲመራ መሾሙን ቡድኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ቡድኑ ከዚህ በተጨማሪም ጎሊቻ ዴንጌ የጤና መሻሻል ካሳየ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ሥራው እንዲመለስ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ሳይቀበል ቀርቷል ብሏል።

"ሐምሌ ወር ላይ በተካሄደው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር - የኦሮሞ ነጻነት ጦር አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ከተቀሩት የጦር አመራሮች ጋር አለመግባባትን እንደ ምክንያት በማንሳት በጉባኤው ሳይገኝ ቀርቷል" ይላል መግለጫው።

የምስሉ መግለጫ,

ጎሊቻ ዴንጌ ለሶስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የትጥቅ ትግል አካሂዷል።

ጎሊቻ አዲስ አበባ መግባቱን ተከትሎ የቀድሞው የኦነግ ጦር ከፍተኛ አመራር የሰላማዊ ትግል ለማካሄደ መወሰኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ጎሊቻም በጉዳዩ ላይ "ትልቁ ድርጅት ኦነግ በሰላማዊ ትግል አምኖ በሰላም ወደ አገር ቤት አገር ገብቷል። ታላላቅ የኦሮሞ ታጋዮችም በሰላማዊ ትግል አምነው ወደ አገር ተመልሰዋል። ጎሊቻም በሰላማዊ ትግል አምኖ ወደ አገር ቢገባ ምን ክፋት አለው?" ሲል ይጠይቃል።

ከህወሐት ጋር አብሮ የመስራት ስምምነት

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "አሸባሪ ድርጅቶች" ተብለው የተፈረጁት የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ሸኔ) እና ህወሓት የኢትዮጵያን መንግሥት ለመውጋት ከስምምነት መድረሳቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

በህወሓት የበላይነት ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ያስተዳድር በነበረበት ወቅት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አሸባሪ ድርጅት ተብሎ ተፈርጆ ነበር። በዚህም ከፓርቲው እና ከጦሩ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በርካቶች የተለያየ ጉዳት ሲደርስባቸው እንደቆየ የቡድኑ አባላት ይናገራሉ።

ይህን ተከትሎ ፓርቲው፤ በህወሓት ብዙ ጉዳት እንደደረሰበት ሲገልጽ ቆይቷል።

ጎሊቻ ዴንጌ "ምንም እንኳ በቡድኑ የአመራርነት ቦታ ላይ ባልሆንም ጦሩ ከህወሓት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱን አጥብቄ ስቃወም ነበር" ይላል።

"ለ27 ዓመታት ህወሓት የኦሮሞ ሕዝብን ሲጎዳ፣ ሲገድል ቆይቷል። በርካታ የኦሮሞ ወጣቶችን ገድሏል። ኦህዴድ ጠላት ነው ብለን ረግመናል፤ ዛሬ ላይ ከህወሓት ጋር ሆነን የዐቢይ መንግሥትን እንገለብጣለን የተባለውን ተወያይተን የተወሰነ አይደለም። ጦሩንም ሕዝቡንም አላወያዩም። በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ተቀባይነት የለውም" በማለት ጎሊቻ ይናገራል።

ጎሊቻ ከአሁን በኋላ ምን አይነት ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንደሚኖረው ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ "ምንም የማደርገው ነገር የለም። ከትጥቅ ትግል ውስጥ ወጥቻለሁ። ልክ እንደ አንድ የኦሮሞ ልጅ መኖር ነው የምፈልገው። ከዚህ ውጪ የትጥቅ ትግል በቅቶኛል" ብሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ጦር በአሁኑ ጊዜ በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በሚገኙ አካባቢዎች በስፋት ይንቀሳቀሳል።

ይህ ቡድን በሚንቀሳቀስባቸው ስፍራዎች የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ ንጹሃን ዜጎችን በመግደል በተደጋጋሚ ይወቀሳል። የጉጂ እና የቦረና አባ ገዳዎችም "ሸኔ የኦሮሞ ጠላት ነው" ሲሉ አውጀዋል።

በትግል ስሙ ጃል መሮ ተብሎ የሚታወቀው ኩምሳ ድሪባ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከጥቂት ወራት በፊት ባካሄደው ጉባኤ ላይ የጦሩ ዋና አዛዥ ተደርጎ ስለመመረጡ ድርጅቱ አስታውቆ ነበር።

መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው ታጣቂ ቡድን በተለያዩ ጊዜያት በሚንሳቀስባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች ላይ በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ይከሰሳል።