ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ለሁለተኛ ዙር ምርጫ የጀርመን መንግሥትን ድጋፍ ማግኘታቸው ተገለጸ

ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ለሁለተኛ ዙር የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ኃላፊነት እንዲመሩ የጀርመን መንግሥት ድጋፍ ማግኘታቸው ተዘገበ።

የጀርመን ጤና ሚንስትር ጀንስ ሳፕሃን የዶ/ር ቴድሮስን ዳግም መመረጥ ጀርመን እንደምትደግፍ ገልጸው ሌሎች አገራትም ለቀድሞው የኢትዮጵያ ጤና ሚንስትር ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

"አጋር አገራት ዋና ኃላፊ ቴድሮስን እንዲያጩ እንጋብዛለን" ሲሉ የጀርመን ጤና ሚንስትር ጀንስ ሳፕሃን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ለጋሽ ከሆኑ አገራት አንዷ የሆነችውን የጀርመን ድጋፍ ማግኘታቸው ዳግም የመመረጥ እድላቸውን ከፍ ያደርጋል ተብሏል።

ዶ/ር ቴድሮስ ምንም እንኳን በይፋ ለሁለተኛ ዙር እንደሚወዳደሩ ይፋ ባያደርጉም ሮይተርስ የዜና ወኪል ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመምራት እጩ ሆነው መቅረባቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

አገራት በቀጣይ የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመራ ግለሰብ የሚጠቁሙበት ጊዜ በዚህ ሳምንት ይጠናቀቃል።

የጀመርን መንግሥት ለዶ/ር ቴድሮስ ሁለተኛ ዙር መመረጥ ድጋፉን ይስጥ እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዶ/ር ቴድሮስ ዳግም መመረጥን የሚቃወሙም አልጠፉም።

"ወንጀለኛ ነው"

የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በአንድ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ". . . የህወሓት አባል ወንጀለኛ ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ጀነራሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም አቀፍ ተልዕኮ ዕድላቸውን ተጠቅመው የህወሓት ቡድንን ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ጀነራል ብርሃኑ፤ ዶ/ር ቴድሮስ የህወሓት ቡድንን ለመርዳት በርካታ ጥረቶችን ማድረጋቸውን እንዲሁም ጎረቤት አገራት ጦርነቱን እንዲያወግዙ ቅስቀሳ አድርገዋል ሲሉ ከሰው ነበር።

ዶ/ር ቴድሮስ ከዚህ ቀደም በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት እንደሚያሳስባቸው ተናግረው ነበር።

ዶ/ር ቴድሮስ የፈረንጆች 2020 መጠናቀቅን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ላይ "ኮቪድ አልበቃ ብሎ እኔ ደግሞ የግል ህመም አለብኝ። ስለ አገሬ እጨነቃለሁ" ብለዋል።

"አገሬ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ናት። በእናት አገሬ ኢትዮጵያ፣ በትውልድ ቀዬዬ ትግራይ እየተካሄደ ያለው አስከፊ ጦርነት ያስጨንቀኛል" ሲሉ ተደምጠዋል።

አያይዘውም ታናሽ ወንድማቸውን ጨምሮ ሌሎች የቤተሰብ አባሎች የት እንዳሉ እንደማያውቁ ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል።

"የግንኙነት መስመሮች ስለተቋረጡ ታናሽ ወንድሜንና ዘመዶቼን አላገኘኋቸውም። ወንድሜና ዘመዶቼ የማኅበረሰቡ አካል ናቸው። ስለ ታናሽ ወንድሜና ስለ ዘመዶቼ ብቻ ልጨነቅ አልችልም። የምጨነቀው ስለመላው አገሪቱ ነው" ብለዋል።

"ወረርሽኙን መቆጣጠር አልቻሉም"

ከሳምንታት በፊት ኤድስ ሔልዝኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) የተባለው የዓለማችን ግዙፉ ኤችአይቪ ላይ የሚሠራ ድርጅት ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመመራት በሁለተኛ ዙር መመረጥ የለባቸውም ብሎ ነበር።

ኤኤችኤፍ ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19ን የሕዝብ የጤና አደጋ በማለት በፍጥነት አልፈረጀም እንዲሁም ኮቪድ-19ን "ወረርሽኝ" ብሎ ለመፈረጅ ዘግይቷል የሚል ትችት ሰንዝሯል።

ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ-19 መነሻ ግልጽነት አለመኖሩ እና ለወረርሽኙ ክትባቶችን በፍጥነት አለማጽደቅ ድርጅቱ ዶ/ር ቴድሮስን ከተቸባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ጋር በተያያዘ በትራምፕ አስተዳደር ወቅት አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅትን "ለቻይና እጅጉን የወገነ ድርጅት ነው" ስትል ቆይታለች።

ይህ የትራምፕ አስተዳደር አቋም በአሜሪካው ዎል ስትሪት ጆርናል የትናንት ርዕሰ አንቀጽ ላይ ተንጸባርቋል።

ዎል ስትሪት ጆርናል የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን "በጣም ፍጹም ያልሆነ" ሲሉ የጠሩትን የዓለም ጤና ድርጅትን ለማሻሻል ቃል መግባታቸውን አስታውሶ፤ ዶ/ር ቴድሮስን በሌላ በመተካት የለውጥ ሥራው መጀመር አለበት ሲል አስነብቧል።

ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር ሚንስትር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ቴድሮስ እአአ 2017 ላይ ነበር የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ተብለው የተሾሙት።

የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ምርጫ የሚከናወነው እንዴት ነው?

የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ዕጩዎቻቸውን እስከ ዓ. ም. መስከረም 13/ 2014 ድረስ ለዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ያቀርባሉ።

ቦርዱ ከአባል አገራቱ የቀረቡለትን ዕጩዎች በሙሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት አምስት ዕጩዎችን ይዘረዝራል።

ቦርዱ በመቀጠል ከአምስቱ ዕጩዎች የመጨረሻዎቹን ሦስት ዕጩዎች ለማጠቃለያው ምርጫ ይፋ ያደርጋል።

በመጨረሻም የዓለም ጤና ድርጅት ጉባኤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ይመርጣል።

ከዚያ በኋላ ደግሞ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመራው ግለሰብ ግንቦት ወር ላይ ይፋ ይሆናል።