ጄነራሉ በሱዳን ለተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ፖለቲከኞችን ተጠያቂ አደረጉ

ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ

ማክሰኞ ዕለት ለተፈጸመው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተጠያቂዎቹ ፖለቲከኞች ናቸው ሲሉ የገዢው የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወቀሱ።

"ፖለቲከኞች ሕዝቡን ረስተው ዋነኛ ትኩረታቸው በስልጣን ላይ ለመቆየት በሚደረገው ትግል ላይ ስላደረጉ ለመፈንቅለ መንግሥት መከራው ዋነኛ ምክንያት ናቸው" ሲሉ ሄሜቲ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ መናገራቸውን ተዘገበ።

ጨምረውም "ይህም በዜጎች መካከል ደስተኛ ያለመሆን ስሜትን ፈጥሯል" ሲሉ ለአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ካላቸው ጥቂት መኮንኖች መካከል ቀዳሚው የሆኑት ጄነራል ዳጎሎ የአገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሚሊሻን የሚመሩ ሲሆን የቀድሞው መሪ አል ባሽር የቅርብ አጋር ነበሩ።

የሚመሩት ኃይልም በአገሪቱ ምዕራብ ክፍል ውስጥ በሚገኘው የዳርፉር አካባቢ ተፈጽመዋል በተባሉ ከባድ ጭፍጨፋዎች ሲከሰስ ቆይቷል።

ጄነራሉ ጨምውም የኦማር ሐሰን አል ባሽር መንግሥት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የሚመሩት ሠራዊት በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ማክሸፉን ተናግረዋል።

አል በባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሱዳን ውስጥ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች እንደነበሩ ሪፖርት ተደርጓል።

የመንግሥት ግልብጣ ሙከራውን ተከትሎ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ድርጊቱን ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ጋር ግንኙነት ያለቸው "የመጥፎ አላማ ኃይሎች" መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አል ማሐዲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት በዝቅተኛ የማዕረግ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወታደሮች ሥልጣን ለመያዝ ያደረጉትን ሙከራ ማክሸፉ ለአገሪቱ የሽግግር ሂደት ያለውን ታማኝነት ያሳያል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ጨምረውም የመንግሥት ግልበጣ ሴራው ተሳታፊዎች ቁልፍ ቦታዎችን በቁጥጥራቸው ስር በማስገባት ሥልጣን መያዛቸውን ለማሳወቅ ከጫፍ ደርሰው ነበር ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

በዚህም የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ በአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ ውስጥ ያሉ ቴክኒሻኖችን በመያዝ ያዘጋጁትን መግለጫ ከወታደራዊ ሙዚቃ ጋር እንዲተላለፍ ለማድረግ ሙከራ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።

በዚህም ሲቪሉን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን አብደላ ሐምዶክ ያዙ ሲሆን ከሠራዊቱ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ከፍተኛውን ቦታ ይዘዋል።

የሱዳን መንግሥት ዜና ወኪል ሱና የአገሪቱን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጠቅሶ እንደዘገበው ከተሞከራው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑን አመልክቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እየተዳከመ የመጣው ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን የሚያስረክቡበት ወቅት ለማስተጓጎል ነው ሲሉ ተቺዎች ይናገራሉ።

በሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ኃያሉ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ለሲቪሎች ሥልጣኑን በመጪው ኅዳር እንዲያስተላልፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለታል።